Tuesday, April 25, 2017

#ኢትዮጵያ: እውነትም ዞን 9!

ባለፈው ወር (መጋቢት 28/2009)፣ በዞን ዘጠኝ ጦማርያን ጉዳይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት "የመሠረትኩትን የሽብርተኝነት ክስ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ውድቅ ማድረጉ አግባብ አይደለም" ብሎ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረበው የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ብይን ሲያገኝ፣ ዳኞች የወሰኑት ብይን ላይ ‘ዞን 9 የጦማርያን ስብስብ’ ኢትዮጵያን በሰፊ እስር ቤት መመሰሉ በራሱ ‘የሕዝቡን እምነት ዝቅ ለማድረግ’ ለረዥም ግዜ ወንጀል መሰናዶ የተፈጠረ ሥያሜ እንደሆነ ተናግረዋል።
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ኢትዮጵያ ሰፊ እስር ቤት መሆኗን በከፊል ማስረዳት ነው።
"አርብ-አርብ ይሸበራል… የጦማሪው ልብ"
አርብ አርብ ልቡ የማይሸበር የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ማግኘት ይቸግራል። ያለምክንያት አይደለም። ምክንያታችን እንዲገባችሁ የእኔኑ በማጫወት ልጀምራላችሁ።
ከዞን ዘጠኝ ወዳጆቼ ጋር አንድ ዓመት ከስድስት ወር ታስሬ የተፈታሁት አርብ፣ ሚያዝያ 17, 2006 ተይዤ ነው። በኋላ አርባ ቀን "ታድሼ" የወጣሁት አርብ፣ ሕዳር 2, 2009 ታስሬ ነው። ብቻ የሆነ ነገር የጻፍኩ፣ የሆነ ዲፕሎማት ወይም ጋዜጠኛ ያናገርሁ ሰሞን አርብ እስኪያልፍ ጭንቅ ነው። በሌላ አነጋገር ሁሉም አርብ እስኪያልፍ ጭንቅ ነው። አርብ ቀን ለእስር በፖሊሶች የምትመረጠው ቅዳሜና እሁድ እስረኛውን ፍርድ ቤት ለማቅረብ ስለማይገደዱ ነው። ነገር ግን ሰው በማይኖርበት እሁድ ቀን ለማቅረብ እንዲመቻቸውም ጭምር ነው። ስለዚህ አርብ አርብ እኛን አለማየት ነው።
የሥነ ልቦና ሐኪሞች በፈረንጅ አፍ "Post Traumatic Stress Disorder (PSTD)" ይሉታል። ከሆነ ክፉ ገጠመኝ በኋላ የሚከሰት "የደግሞ ይከሰታል ጭንቅ" የሚያመጣው የሥነ ልቦና መዛባት። እኛ አገር እንደችግራችን የሥነ ልቦና ሕክምና ማግኘት የተለመደ አይደለም። ነገር ግን የPSTD ተጠቂ መሆናችንን መጠርጠራችን አልቀረም።
ከመታሰራችን በፊት የብዙአየሁ “ሳላይሽ” አልበም ተወድዶ በየታክሲው፣ በየካፌው ሲጫወት ነበር። ዛሬ ግን የብዙአየሁ ዘፈኖች ለማሕሌት ፋንታሁን የእስር ነጋሪት ናቸው። የእርሱ ዘፈን በተከፈበት ታክሲ እንድትሔድ፣ የእርሱ ዘፈን የተከፈተበት ካፌ ውስጥ እንድትቀመጥ ከተፈለገ ዘፈኑ መዘጋት አለበት። አለበለዚያ አትችልም።
ናትናኤል ፈለቀ የታሰረ ዕለት ከቢሮው በሆኑ ፀጉረ ልውጥ እንግዶች ትፈለጋለህ ተብሎ ነው። ዛሬም ድረስ፣ ቢሮው በር ላይ ፀጉረ ልውጥ ሰዎች በተከሰቱ ቁጥር ከመደንገጥ አርፎ አያውቅም። በተለይ "ናትናኤልን ፈልገን ነው" ካሉ የልብ ደላቂው አካል አታሞውን ይመታል።
ከአዋሽ 7 መልስ በወዳጆቼ ውትወታ የሥነ ልቦና ሐኪም ማየት ጀምሬ ነበር። ምናልባት PSTDው ጎድቶኝ ከሆነ በአፍላነቱ ልድረስበት በሚል ነበር ሐኪም ለማየት የተስማማሁት። ሐኪሜ አንድ ቀን "እስኪ በየቀኑ የሚገጥሙህን የሚያስደነግጡህን ነገሮች ጽፈህ አምጣ" እስከምትለኝ ድረስ በየቀኑ፣ ያን ያክል ጊዜ እየተረበሽኩ እንደምውል አስቤው አላውቅም ነበር። በማግስቱ ልደታ ፍርድ ቤት አንድ ችሎት ለመከታተል ሔድኩኝ። ፍርድ ቤቱጋ አንድ የፖሊስ ፓትሮል መኪና ቆሟል። ፖሊስ ስናይ ማተኮራችን የተለመደ ነው። እነሱን እያሰብኩ ስሻገር ፊትለፊቴ ወደኔ እያዩ የሚያወሩ ፖሊሶች ጋር ዓይን ላይን ተገጣጠምኩ። ልቤ በአስደናቂ ፍጥነት ድርርርርርም እያለ መምታት ጀመረ። አልፌያቸው ስሔድ በሰከንድ ውስጥ ራሴን አረጋጋሁ። የዛኑ ዕለት ተመሳሳይ ነገር ረፋዱ ላይ ተፈጠረ። ይህ የሆነው ከማሕሌት ጋር ከልደታ ፍርድ ቤት ስንወጣ ጊቢ ውስጥ ቆሞ የነበረ የፖሊስ ፓትሮል ከጎናችን ተንቀሳቅሶ አብሮን በመውጣቱ ነው። “አርብ ነው እንዴ ዛሬ?” ተባባልን። የዛኑ ዕለት ምሽት አቤል ዋበላ የጻፈውን የታሰርን ዕለት የነበረውን ውሎ የሚተርክ ጽሑፍ እያነበብኩ እያለ ልክ አሁን የሚሆን ይመስል እፈራለሁ፤ ልቤ ድርድድው፣ ድርድድው ይላል።
ታዲያ ሰፊ የእስርቤት ዞን ውስጥ አይደለንም ማለት ይቻላል? ይህ የኛ የግል ጉዳይ፣ በገዛ ቅብጠታችን ያመጣነው ጦስ የሚመስላቸው ሰዎች እንዳሉ አላጣሁትም። በእርግጥ እኛ እንዲህ ዓይነቱ ሰቀቀን ውስጥ የገባነው ሐሳባችንን በነጻነት በመግለጻችን፣ መብታችንን በመጠየቃችን ብቻ መሆኑን መዘንጋት ተገቢ አይደለም።
ልዩነቱ የዲግሪ ነው እንጂ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህ ፍራቻ አለበት። ብዙኃኑ ኑሮውን መግፋት የሚፈልገው መብቱን እስከጥግ እየጠየቀ አይደለም። ለአካላዊ ነጻነቱ የተወሰኑ መብቶቹን አሳስሯል።
ፍርድ ቤት ፈትቶን፣ በአንፃራዊ የአካላዊ ነጻነት እየተንቀሳቀስን መሆኑን እያወቁ በርካታ ወዳጆቻችን ሸሽተውናል። የሸሹት እኛን አይደለም። እስርን ነው። ከእኛ ጋር መሆናቸው ያለምንም ወንጀል በመንግሥት ዒላማ ውስጥ የሚያስገባቸው ከመሰላቸው፣ መንግሥት ያለወንጀል እንደሚያስር ያምናሉ ማለት ነው። ያለወንጀላቸው ሊታሰሩ እንደሚችሉባት የሚያስቧት አገር ደግሞ "ሰፊ እስር ቤት” ነች።
ወዳጆቻችን ብቻ አይደሉም። ሌሎችም ለጊዜያዊነት የሚያገኙን ሰዎች እንዲሁ ይፈሩናል። “የምትሠራው ሥራ የተባረከ ነው። ግን አገሩ ኢትዮጵያ ነው” ዘወትር የምንሰማው ምክር ነው። አይበሉት እንጂ “አገሩ እስር ቤት ነው” ብለው ማሰባቸውን ማሳያ ነው። ለምሳሌ ከላይ የጠቀስኳት ሐኪሜ ይህንኑ ፈርታ ወደሷ ስሔድ ስልኬን አጥፍቼ እንድሔድ፣ ለሰው እንዳልናገር ደጋግማ ታስጠነቅቀኝ ነበር። ግንኙነታችን የሕክምና እርዳታ የሚፈልግ እና የሚሰጥ ሰው ቢሆንም ያሳስረኛል ብላ ትፈራለች። የምትፈራው እኔን አይደለም። እኔንማ በወዳጅነት ስሜት ስጋቴን የምጋፈጥበትን መንገድ እያስተማረችኝ ነበር። የምትፈራው ያለሰበብ የማሰር ሥልጣን ያለውን የሰፊው እስር ቤት ዋርድያ - መንግሥትን ነው።

Monday, February 6, 2017

የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች ከታሰሩ 1020 ቀናት በኋላ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ

ሚያዚያ 17፣ 2006 የታሰሩት አራት የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ በፍቃዱ ኃይሉና አጥናፉ ብርሃኔ እንዲሁም በሌለችበት ክስ የቀረበባት ሶልያና ሽመልስ ለመጨረሻ ውሳኔ ዛሬ ጥር 30፣ 2009 ለሃምሳ አንደኛ ጊዜ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት ይቀርባሉ::

ጥቅምት 05፣ 2008 የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ችሎት አራቱን ጦማርያን ከቀረበባቸው ክስ በነፃ ያሰናበተ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፤ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ላይ የቀረበበት ክስም ወደ መደበኛው የወንጀል ሕግ ተቀይሮ በዋስትና ከእስር ተፈትቷል:: ነገር ግን ከሳሽ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ "በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር ተሰኝቻለሁ" በማለት በታሕሳስ 04፣ 2008 ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቧል::
በፍቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ሶልያና ሽመልስ ፣ አቤል ዋበላና አጥናፉ ብርሃኔ
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ይግባኝ ተቀብሎ የሁለቱንም ወገን ክርክር ከሰማ በኋላ "የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት" በሚል የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት ከዓመት በላይ የወሰደ ሲሆን ፤ ጥር 19፣ 2009 በዋለው ችሎትም አስፈላጊው ሰነዶች ሁሉ ተሟልተው መቅረባቸውን አረጋግጦ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ጥር 30፣ 2009 ቀጠሮ ይዟል::

በሌላ በኩል ጦማሪ አቤል ዋበላ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የነበረበትን ክስ የቦሌ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ችሎት "ከስራው የታገደበት አግባብ ተገቢ ነው" በሚል ምክንያት ወደ መደበኛ ስራው እንዳይመለስ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ፤ ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉም በድጋሚ በተለያዩ ምክንያቶች በቅርቡ ታስረው የተፈቱ መሆናቸው የሚታወስ ነው:: 

Monday, December 5, 2016

የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች ለ48ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ

አምስቱ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች፣ ሶልያና ሽመልስ (በሌለችበት)፣ በፍቃዱ ኃይሉ (ከእስር ቤት)፣ አጥናፉ ብርሃኔ፣ አቤል ዋበላና ናትናኤል ፈለቀ ነገ ማክሰኞ ሕዳር 27፣ 2009 ለመጨረሻ የይግባኝ ብይን ይቀርባሉ፡፡ ሰባት የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችና ሶስት ጋዜጠኞች ከታሰሩበት ሚያዚያ 17፣ 2006 ጀምሮ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት እየቀረቡ ቆይተው አምስት ተከሳሾች ከሳሽ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ አንስቻለሁ በማለቱ ሐምሌ 01፣ 2007 የተፈቱ ሲሆን አራቱ ተከሳሾች ደግሞ ነፃ ናቸው ተብለው ጥቅምት 5፣ 2008 ከእስር ተለቀዋል፡፡ የዞን ዘጠኝ ጦማሪ የሆነው በፍቃዱ ኃይሉም የቀረበበት ክስ ከፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ጋር የማይገናኝ በመሆኑ በመደበኛው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 257/ሀ መሰረት በጽሁፍ አመፅ የመቀስቀስ መተላለፍን ፈፅሟል፣ ይሄንም ይከላከል ተብሎ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በጥቅምት 10፣ 2008 በተሰጠው ውሳኔ መሰረት በሃያ ሽህ ብር ዋስትና ከእስር መለቀቁ ይታወቃል፡፡

በፍቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ሶልያና ሽመልስ ፣ አቤል ዋበላና አጥናፉ ብርሃኔ

ነገር ግን የፌደራል ማዕከል ዓቃቤ ሕግ በታሕሳስ 04፣ 2008 በተፃፈ ይግባኝ ‹በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር ተሰኝቻለሁ፣ ተከሳሾቹ በነፃ መሰናበት የለባቸውም› በማለት ባቀረበው ይግባኝ መሰረት ላለፍት አስራ ሁለት ወራት በስር ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ያልተሰጠበት በፍቃዱ ኃይሉን ጨምሮ አምስቱ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት በመቅረብ ክሳቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ሲሆን በነገው ዕለትም ለ50ኛ ጊዜ የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔን ለማፅናት ወይም ለመሻር በሚሰየመው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡


በሌላ በኩል ደግሞ ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ጥቅምት 18፣ 2009 አየር ላይ ለዋለው የአሜሪካን ድምፅ (Voice of America) ‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አጥላልተሃል› በሚል አርብ ሕዳር 02፣ 2009 ከመኖሪያ ቤቱ ተይዞ የታሳረ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ እስከ አሁን ድረስ ፍርድ ቤት ያልቀረበ ከመሆኑም በላይ በአሁኑ ወቅትም ‘በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ’ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ ጠበቃም ሆነ የቤተሰብ አባልም መጠየቅ እንደማይችል የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በነገው የፍርድ ሒደትም የመቅረቡ ጉዳይም እንዲሁ አጠያያቂ ነው፡፡

Thursday, October 20, 2016

A year after their release, Zone 9 Bloggers will reappear to Court

Four of the Zone 9 bloggers,  Abel Wabella,  Atnafu Berhane, Befkadu Hailu and Natnael Feleke will reappear to the Federal Supreme Court, tomorrow October21, 2016 for a verdict and Soliana Shimelis’s case will continue to be entertained in absentia.


Natnael Feleke (left top), Befkadu Hailu (right top), Abel Wabella (left bottom), Atnafu Birhane (right bottom) and Soliyana Shimelis (middle)
After their arrest on April 2014, the bloggers were charged with terrorism and the Federal High Court which has a first instance jurisdiction over the case acquitted them. However, the Federal Public Prosecutor appealed against the decision of the lower court and the Federal Supreme Court, a higher court with an appellate jurisdiction over the matter accepts its appeal.

On tomorrow's trial, the court is expected to give a final verdict over the oral argument the defendants and the prosecutor presents in addition to a verdict on the documentary evidences presented against the Bloggers. If the court accepts the prosecutor's appeal, the case will send back to the Federal High Court and the trial will resume while the bloggers rearrested.

On the other hand, one of the bloggers, Befkadu Hailu had still a pending case with the same cause of action under a lenient charge at the Federal High Court and Natnael Feleke also had a pending case in which he is alleged of incitement by talking politics.  

Saturday, October 15, 2016

ሰ.መ.ጉ. 25ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው፤ የዜጎች ድጋፍ ያስፈልገዋል!

(በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ)

በአገራችን ብቸኛው ሰብኣዊ መብት ላይ አተኩሮ የሚሠራው መንግሥታዊ ያልሆነ የሰብኣዊ መብቶች ጉባኤ (ሰ.መ.ጉ.) ከተመሠረተ 25 ዓመታት ሞሉት፡፡ ቀድሞ የኢትዮጵያ ይባል የነበረው ኢ.ሰ.መ.ጉ. በበጀት እጦት ምክንያት በ3 ክልሎች ብቻ ጽሕፈት ቤቶች ስለነበሩት ሰ.መ.ጉ. ለመባል ተገዶ ከርሟል፡፡ ይሁን እንጂ በቅርቡ ለማገገም እያደረገ ባለው ጥረት የጽሕፈት ቤቶቹን ቁጥር 6 አድርሶ የቀድሞ ሥሙን ለማስመለስ እና ሥራውንም በአገሪቱ ክልሎች በሙሉ ለማድረስ እየሞከረ ነው፡፡ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብፅአት ተረፈ ዛሬ (ቅዳሜ፣ ጥቅምት 5፣ 2009) ከወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ ‹በተለይ ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ በርካታ ባለሙያዎቻቸውና መረጃዎቻቸው ልክ ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ የተንቀሳቀሱ በማስመሰል በመነገሩ፣ ተቋሙን ጥለው እንዲሰደዱ በማድረግ ተዳክመው ቆይተዋል፡፡ ሌላው በ2001 የወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅ ተፅዕኖ አሳርፎባቸዋል፡፡ በተለይ በጀት ከውጭ አለማግኘታቸው ጽ/ቤቶቻቸውን እንዲዘጉና በርካታ ሠራተኞቻቸውን እንዲቀንሱ አድርጓቸዋል፡፡›