Wednesday, August 15, 2012

የያዘን አባዜያለፈ ታሪክን መመርመርና ማወቅ አሁን ለምንኖርበት ነባራዊ ሁኔታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ ታሪኩ ምንም ሆነ ምን እንዳለና እንደነበረ ለትውልድ መተላለፍ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ባለፈች አንዲት ሰከንድ ውስጥ የተፈጠረች ክስተት እንኳን ከታሪክነት ትመደባለች፡፡  ከግለሰብ ጀምሮ  አገራትም ጭምር የራሳቸው የሆነ ታሪክ ይኖራቸዋል፡፡ በተለምዶ ግን ታሪክ ስንል ቶሎ ብሎ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው የአገር ታሪክ እንደመሆኑ መጠን እኔም የማወራው ስለ አገር ታሪክ እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡

ግራ ገብቶናል!

በርግጥ ሁሉም ዓይነት ታሪኮች ተያያዥነት አላቸው፡፡ ስለግለሰቦች ሳናወራ ስለአገር እናውራ ማለት አንችልም፡፡ በብዛት የአገር ታሪክን የያዙ ፅሁፎች አገሪቷን ሲያስተዳድሩ በነበሩ መሪዎች የቆይታ ዘመን ተከፋፍለው በጊዜው የነበሩ መሪዎች እና የቤተሰብ ታሪክን ጨምሮ አገሪቷን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚካዊ ሁኔታ በዝርዝር ያካትታሉ፡፡ እስካሁን እንደተመለከትኩት ከሆነ ከሚፅፈው ሰው አኳታሪክን በደጋፊ፣ በተቃዋሚ/ጠላት እና በምሁራን የሚፃፍ ብለን በሦስት ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡ በአሁኑ ሰዓት በደጋፊና በተቃዋሚ ተፅፈው የምናገኛቸው ታሪክ የሚተርኩ መጽሐፍቶች ቁጥራቸው ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መሄዱ አሳስቦኛል፡፡ በዛው ልክ ግራ የተጋባንበትና የትኛውን ተቀብለን ‹ታሪካችን› አድርገን እንደምንወስድ ያላወቅንበት ሁኔታ ያለና ወደፊትም በዚሁ መቀጠሉ አይቀሬ ይመስለኛል፡፡

በጣም አስፈላጊውና ልናውቀው የሚገባን ታሪክ ምርምር ተደርጎ በዘርፉ ምሁራን የተጻፉትን መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ነገር ግን የዚህ ዓይነት መጽሐፍቶችን በሚፈለገው መጠን ማግኘት ተአምር ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ኃላፊነትን ወስዶና ታሪክን ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚሰራ አካልም ያለን አይመስለኝም፡፡ ስለዚህም አሉን የምንላቸው የታሪክ ድርሳናት ዘመኑን ወይም መሪውን በመውደድ ወይም በመጥላት ተመርኩዘው እና በሁለት ጎራ ተከፍለው ፅንፍ በመያዝ የተፃፉ ናቸው ብንል ስህተት የማይሆን ነው፡፡

የንጉስ አገዛዝ በነበረት ጊዜ ብንመለከት ጸሐፍያኖቹ ራሳቸው የንጉሡ ጸሐፊ ወይም ወዳጅ ይሆኑና ስለንጉሱና አገዛዛቸው መልካምነት ከመናገር እና ከመጻፍ ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖራቸውም፡፡ በደርግ ዘመን ሳንሱርን በመጠቀም አገዛዙን አስመልክቶ ተችቶ ወይም ተቃውሞ መፃፍ በሕግ የተከለከለ ነበር፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ እንደተፈለገ መጻፍ እንደሚቻል በመርህ ደረጃ ይነገርና ተግባር ላይ ግን ተፈፃሚ አይሆንም፡፡ በሁሉም ጊዜያቶች የተጻፉ ታሪኮች ግን ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው ነገር አለ፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል ካለፈው ወቅት ጋር ሲነፃፀር የራሳቸውን አገዛዝ የተለየና አዳዲስ ለውጦች የታየበት እንደሆነ ያለፈው ግን ትክክል እንዳልነበረ መናገር እና መፃፍ የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡ ይህ ተግባር ታሪክን ከማጥፋት ባሻገር አንድ ታሪክ ያለውን ሕዝብ በጎራ ከፋፍሎ ከአንድ በላይ ታሪክ በማስተማር ትክክለኛውን ታሪክ መረዳት እንዳይችል ያደርጋል፡፡

‹ነግ በኔ›

ያለፉት አልፈዋል ከመውቀስ በስቀተር ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ አሁን ያለው የኢሕአዴግ መንግስት ግን አትኩሮት ሰጥቶ በተቻለ መጠን በገለልተኛ ወገን የአገራችን ታሪክ የሚፃፍበት ሁኔታ ቢጀመር መልካም እንደሆነ ተገንዝቦ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ግራ በመጋባት ያለውን ትውልድ መታደግ አለበት፡፡ እስካሁን እየሰራቸው ያሉ ነገሮች ግን ከዚህ በተቃራኒ ናቸው፡፡ የቀድሞ ታሪካችንን በራሱ እይታ በመመልከትና የራሱ ድምዳሜዎችን የኛም እንዲሆኑ ነው የሚደረገው፡፡ መቼም የቀድሞ መሪዎቻችን በጊዜያቸው ሙሉ መጥፎ ነገር ሲያደርጉ ነበር ማለት የሚያስኬድ ነገር አይደለም፡፡ እንዲያውም ያኔ ፈተናው በበዛበት ወቅት በብዙ ነገር ተፈትነው ለኢትዮጵያ አገራችን ከማንም በላይ መስዋእትነት የከፈሉ፣ ታግለውና ተከራክረው አገራችንን ያቆዩልን መሪዎች ነበሩን፡፡ ነገር ግን ይህን መልካም ሥራቸውን ማውራት አሁን ያለውን መንግስት እንደመቃወም የሚቆጠርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ እነዚህ ታሪኮች እና ተዋናዮቻቸው የሚዘከሩበትና የሚከበሩበት የድል በዓላት አከባበር ድምቀት ከጊዜ ወደጊዜ ቀንሷል፡፡ በዚሁ ከቀጠለ እንዲያውም ሳይረሳም አይቀርም፡፡

ይህ ታሪክን የመቅበር ወይም የመበረዝ ሥራ በዚህ ወቅት አገር ከሚመራ መንግስት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ› የሚለው የቴዲ አፍሮ ዘፈን በትክክል ይገልፀዋል፡፡ የኋላችንን የምንጥል ከሆነ እኛም ያልኖርን ጊዜ ታሪካችን እንደማይኖር መታወቅ አለበት፡፡ ትላንት ጠላት ወይም አሸባሪ ሲባል የነበረው አሁን መሪውን እንደጨበጠው ሁሉ ዛሬ አሸባሪ ወይም ጠላት የሚባለው ነገ መሪውን እንደሚይዝ ሳይዘነጋ የህዝብ የሆነን ታሪክ ለትውልድ እንዲተላለፍ የማድረግ ሥራ ቢሠራ መልካም ነው፡፡

ሙዚየም ወይስ የኢሕአዴግ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ?

ከመጽሐፍት በተጨማሪም በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ምስክርነት፣ ስዕላዊ መግለጫዎች፣ ቪዲዮና ኦዲዮዎች፣ ፎቶግራፎች እና ሌሎች መሰል ነገሮችም ታሪክን እንድናቅ የሚረዱ ነገሮች ሲሆኑ ሙዚየም መጽሐፍትን ጨምሮ ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች ሁሉንም በአንድነት ልናገኝ የምንችልበት ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ ይህን በማሰብ የዞን ዘጠኝ ኢ-መደበኛ የጦማሪዎች ቡድን በደርግ ዘመን በ‹‹ቀይ ሽብር›› ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰራውን መታሰቢያ ሙዚየም ጉብኝት አድርገናል፡፡

ፎቶግራፎች፣ የተለያዩ ደብዳቤዎች፣ መጽሔቶችና የሕትመት ውጤቶች፣ አልባሳቶች፣ ይጠቀሙባቸው የነበሩ መሳሪያዎች እና ሌሎችም በሙዚየሙ የተካተቱ ሲሆን በያንዳንዱ ግርጌ መግለጫ ተፅፎባቸዋል፡፡ መግለጫዎቹን ስናነብ የታዘብነውና ያስገረመን ነገር በአብዛኛዎቹ መግለጫዎች የኢሕአዴግ መንግስት በደርግ ላይ ያለውን አመለካከት እና ትንታኔዎች የሚያሳዩ ጽሑፎች መሆናቸው ነበር፡፡ በኢቲቪ ከሚቀርቡት የደርግን መንግስት የሚያወግዙ ዶክመንተሪዎች ላይ ከምንሰማቸው ንባቦች ጋር ወይም በተመሳሳይ ርዕስ በኢሕአዴግ ከሚዘጋጁ የፎቶግራፍ አውደርዕይ ጋር ልዩነት የለውም፡፡ ኢቲቪን በአንድ ህንፃ ማየቱ ታዲያ ምኑን ሙዚየም ሆነው? ውሳኔውን ለተመልካች ወይም ለአንባቢ ትቶ በወቅቱ የነበረውን ነገር ብቻ መግለፅ ከባድ ነገር ሆኖ ነውን? እንግዲህ ነገ የሚመጣው ደግሞ ይህን ሙዚየም እንዴት እንደሚቀይረው እና ምን ዓይነት መግለጫዎች እንደሚጽፍበት ማሰብ ነው፡፡

ታሪካችን ግን በእንዲህ ያለ ሁኔታ ገዢዎቻችን በተለያዩ ቁጥር መቀያየር እና የነሱን ሐሳብ የሚያንፀባርቅ ሳይሆን ትክክለኛው ታሪክ ተጠንቶ ተመሳሳይ የሆነና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ እና ውዥንብር የማያስነሳ መሆን ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለማንኛውም በኛ በኩል አንድ እና ትክክለኛ ታሪክ እንዲኖረን ማድረግ የምንችለውን እናድርግ፡፡

No comments:

Post a Comment