Monday, September 24, 2012

ይቅርታ የሚገባው የኢትዮጵያ ሕዝብ!


እነሆ ኢትዮጵያ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትሯን አግኝታለች፡፡ አንድ መሪ ሲሞት ያለምንም ጦርነት እና ገሀድ የወጣ ሽኩቻ ምክትሉ ሲታካው በአገራችን የታየው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ይህ ግን የሚኩራሩበት ችሮታ ሳይሆን ሊታዘዙለት የሚገባ  ሕገ መንግስታዊ መርሕ ነው፡፡ መጪው መሪ ያለፈውን ዘመን ትንሽዋን ስኬት የማክበጃ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ባሕል ቀጭተው ወደ ተግባራዊ ለውጦች በመግባት ለውጡ የእውነት መሆኑን ለማሳየት ጊዜው አሁን ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ይህ አይደለም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሕመም እና ሞት ተከትሎ የነበሩትን ዘገባዎች ይመለከታል፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ መታመማቸው በወሬ ደረጃ መናፈስ ከጀመረ በኋላ ሚዲያዎቻችን በተቃራኒ ጽንፎች ሲወዘወዙ ከርመዋል፡፡ በመጀመሪያ ላይ ስለጉዳዩ የተጠየቁት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮው አቶ ሽመልስ ከማል፥ ‹‹ወሬው የኢሳት ነው፤›› ብለው አጣጥለውት (ወይም ዋሽተው) ነበር፡፡ እኚህ የመንግስት ተጠሪ “የነበሩ” ሰው፣ ሕዝብ የመንግስት ጉዳዮችን የማወቅ ሕገመንግስታዊ መብቱን በመግፈፍ፣ አውቀው - በማን አለብኝነት፣ አሊያም በስህተት የተናገሩትን ተናግረዋል፤ ነገር ግን በጥቂት ቀናት ውስጥ አለቃቸው አቶ በረከት ስምኦን ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀለል ያለ ሕመም›› እንደገጠማቸው ተናግረዋል፡፡


ስለዚህ አቶ ሽመልስ ከማል ለሰሩት ስህተት (ወይም ለሕዝብ ላደረሱት የተሳሳተ መረጃ) የኢትዮጵያ ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው፡፡

ያንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት የአቶ መለስን ሞት አረጋግጫለሁ አለ፤ ቀጥሎም በግለሰብ ደረጃ ክርክሩ ቀጥሎ ከርሞ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንም በበኩሉ አቶ መለስ መሞታቸውን ምንጮቼ ነግረውኛል አለ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የመንግስት ባለስልጣናት በየፊናው አቶ መለስ በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው የሚል ምንም ዜና በየፊናው በመርጨት ሕዝቡን በጥርጣሬና ስጋት መስክ ውስጥ እንዲወዛገብ ፈረዱበት፡፡ከዚያም አልፎ ለእያንዳንዱ አሉባልታ ምላሽ አንሰጥም ሲሉም ተደመጡ፡፡

በሌላ በኩል የግል ፕሬስ ናቸው በሚል የመንግስት አፍ የሆኑትን ቴሌቪዥን እና ሬድዮኖችን በአማራጭነት እንዲተኩ ተስፋ የምንጥልባቸው ጋዜጦች የራሳቸውን መረጃ አወጡ፡፡ ‘ውስጥ አዋቂ’ ነኝ የሚለው ፎርቹን ‹‹መለስ ወደከተማ ተመለሱ›› በሚል ተሽሏቸው አዲስ አበባ መግባታቸውን ሲያትት፣ ሌላኛው ውስጥ አዋቂ ሪፖርተርም በበኩሉ፣ ‹‹መለስ ተሽሏቸው›› በሕመም ፈቃዳቸው መዝናናት ላይ መሆናቸውን እና አሜሪካን  አገር እንደሚገኙም ዘገበ፡፡ ትንሽ ቆየት ብሎም፣ አዲስ አድማስ ሁነኛ ባለስልጣን ነገሩኝ ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተመንግስት ያለው መኖሪያቸው ውስጥ ሆነው ከአራት የቅርብ ሰዎች ጋር ስራ መጀመራቸውን - ሁሉም በፊት ገጾቻቸው ላይ አስነበቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞተዋል ተብሎ በዳያስፖራዎች በተነገረበት ጊዜ አለመሞታቸውን ማረጋገጫ አልተገኘም፡፡ ነገር ግን አገር ውስጥ ገብተዋል፣ እና ተሸሏቸዋል ሲባል የነበረው በሙሉ ውሸት አሊያም በትህትና ለመናገር የመረጥን እንደሆነ ደግሞ ስህተት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ጉዳዩ አከራካሪ ቢሆንም አንዳንዶች ከመንግስት አካላት ሆነ ተብሎ የተነዛ የማዘናጊያ የሐሰት ወሬ እንደነበር ለመናገር ሞክረዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱን ስህተት እያጣሩ ሕዝብ ዘንድ ማድረስ የመገናኛ ብዙሐኑ ተቀዳሚ ተግባር እንደመሆኑ ላሰራጩት የተሳሳተ ዜና ተጠያቂ ከመሆን አይተርፉም፥ከዚህም በተጨማሪ ይህ አይነቱ ትልቅ ሞያዊ ግድፈት የመገናኛ ብዙሐኑንም ሆነ የጋዜጠኞቹን የወደፊት ተአማኒነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይጥለዋል፡፡


ስለዚህ ፎርቹን(ምንም እንኳን በዚህ ሳምንት ዕትሙ በጉልህ መግለጽ ሲገባው አድበስብሶ ለማለፍ ቢሞክርም)፣ ሪፖርተር እና አዲስ አድማስ ጋዜጦች የተሳሳተ መረጃ ለሰጡት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን አክብሮት በይቅርታ መግለፅ አለባቸው፡፡


የመለስ ሞት በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ከተረጋገጠ በኋላ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ፡፡ ሕዝቡ የደረሰበትን የፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነት፣ የኢኮኖሚ በደል እና ሌሎችንም ከቁብ ሳይቆጥር እንደ ሰው ሐዘኑን አሳየ፡፡ በመሰረቱ የሕዝቡ ስሜት የሚነግረን አንድ ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ሕዝብ በአመለካከት ልዩነት እና በበደል ውስጥ ሆኖም ቢሆን የመሪዎቹን ክፉ እንደማይመኝ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ግን የሕዝቡን ኢትዮጲያዊ የሐዘን ስሜት ተከትሎ የመንግስት ባለስልጣናትና መገናኛ ብዙሐን ስሜት የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ማድረጋቸው ነው፡፡

በዋነኝነት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተንቀሳቀሱ ያልተጨበጡ (አልፎ አልፎም የሟቹን ክብር የሚያዋርዱ ንግግሮችን ከጎዳና ተዳዳሪዎች ሳይቀር) እያተቀበሉ እና እያናፈሱ፣ አቶ መለስን ምንም እንከን የማይገኝላቸው ልዕለሰብዕ፣ ፓርቲያቸውን ደግሞ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው ብቸኛ ፓርቲ እንደሆነ ለማስመስከር ሲጥሩ ከርመዋል፡፡

የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች እና በተለያዩ የገጠር አውራጃዎች የሚኖሩ ሰዎች በአለቆች እና ቀበሌ ሊቀመንበሮች በተጻፉ ደብዳቤዎች ቅስቀሳ ለቅሶ እየደገሱ እና ለቅሶ እየደረሱ በቴሌቪዥን እንዲተላለፉ ተደረገ፡፡ ይህም ከገዢው ፓርቲ ፕሮፓጋንዳነት ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም፤ ከዚያም በላይ ያደረሰው ኢኮኖሚያዊ ብክነት(በቤላ ጽሁፍ በደንብ የሚወራበት ሃሳብ ቢሆንም) አልተሰላም፡፡ ይህ ሁኔታ የሚያስመሰክረው ነገር ቢኖር ባለስልጣናቱ ለአገሪቱ ኃብት አጠቃቀም ዙሪያ ምንም ዓይነት ኃላፊነት እንደማይሰማቸው ሆነው መገኘታቸውን  ነው፡፡

ስለዚህ የመንግስት መገናኛ ብዙሐን፣ ለቅሶ ድረሱ የሚል ደብዳቤ የጻፉ ኃላፊዎች እና ሊቀመንበሮች፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሁለት ሳምንት ብሔራዊ ሐዘን ያወጁ ባለስልጣናት እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ሕዝብን በሚዲያ እንደሚደሰኩሩት የሚያከብሩት ከሆነ ንፁሕ ሐዘኑን ለፕሮፓጋንዳቸው ፍጆታ ማዋላቸውን አምነው ይቅርታ ይጠይቁ!!!


No comments:

Post a Comment