Friday, September 28, 2012

የትችት ባሕላችንን ብንተቸውስ?
ከግሪክ፣ የኤሶጵ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይተረካል፡፡ አንድ ሰውዬ እና ልጁ፣ አህያቸውን አስከትለው ወደገበያ ሲሄዱ የተመለከታቸው የአገሩ ሰው፣ ‹‹እናንት ሞኞች፣ አህያው እኮ የተፈጠረው ሊጋለብ ነው›› ይላቸዋል፡፡ አባት ልጁን አህያው ላይ ጭኖ ትንሽ እንደተጓዙ የሆኑ ሰዎች ይመለከቱ እና ‹‹ምን ዓይነት የተረገመ ልጅ ቢሆን ነው አባቱን በእግሩ እያስኬደ እሱ የሚጋልበው?›› አሉ፡፡ አባት ልጁን አስወርዶ ራሱ መጋለብ ቀጠለ፤ ጥቂትም ሳይጓዙ ግን ‹‹ምን ዓይነት ክፉ አባት ነው ልጁን በእግሩ እያስኳተነ እሱ አህያ የሚጋልብ?›› ብለው የሚተቹ ሰዎች አለፉ፡፡ ግራ የተጋባው አባት ልጁን ከኋላው ጭኖ አህያውን ለሁለት ይጋልቡት ጀመር፡፡ ይህንን የተመለከቱ ሰዎች ‹‹ምን ዓይነት ጭካኔ ነው፣ አንድ አህያ ለሁለት የሚያስጋልባችሁ?›› አሏቸው፡፡ ግራ የተጋቡት አባትና ልጅ በመጨረሻ አህያውን ለሁለት ተሸክመውት ገበያ በመግባት የገበያተኛው መሳለቂያ ለመሆን በቅተዋል፡፡

የተረቱ ሞራል፣ ሁሉንም ማስደሰት እንደማይቻል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉንም የሚያስማማ መፍትሄ ባይገኝም ቅሉ ለትችቱ መፍትሄ ለመስጠት ባደረጉት መፍጨርጨር አባት እና ልጅም በፈረቃ ጋልበዋል፣ አህያውም አርፏል፡፡ የሚቀበሉትን ትችት ማወቅ እና አለማወቅ፣ ብሎም ለትችቱ ሁነኛውን መፍትሄ መፍጠር የተተቺው ድርሻ ቢሆንም ‹ትችት› ግን የማይቀር እና ሊቀር የማይገባው ነው፡፡

አሁን የራሳችንን ትችት ባሕል ወደመተቸት እናልፋለን፤ የትችት ባሕላችንን ከመተቸታችን በፊት ግን ለቃሉ ትርጉም በማበጀት ብንጀምር መልካም ነው፡፡ ‹ትችት› የሚለው ቃል ከመነሻው አሉታዊነት እንዳለበት የሚከራከሩ አሉ፡፡ እነዚህ ተከራካሪዎች ‹ሂስ› የሚለው ቃል የተሻለ አስማሚ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሁለቱ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት ማስታረቅ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስላልሆነ - ሳይስማሙ እንዲኖሩ እንተዋቸውና ‹ትችት› በዚህ ጽሑፍ ውስጥ እንዲኖረው ስለሚፈለገው ትርጉም እንነጋገር፡፡

‹ትችት› በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ‹‹በሆነ ርዕሰ ጉዳይ፣ ሐሳብ፣ ፍልስፍና፣ ድርጊት ወይም የሥራ ውጤት ላይ የሚሰነዘር፣ በምክንያት ላይ የተመሰረተ የተቃርኖ ወይም የነቀፌታ አስተያየት ነው፡፡››

በአገራችን ለትችት የተነወሩ (አይነኬ) በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከነዚህ ጉዳዮች መካከል ለጠቅላላ የትችት ባሕላችን ጉብጠት ምሳሌ ይሆናሉ በሚል በጥንቃቄ የመረጥኳቸውን ጉዳዮች እያነሳሁ ለማቅናት እደረድራለሁ፡፡ ትችቴ ያልተስማማው የመልስ ምት ቢጽፍ በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ለማስፈር ከወዲሁ ቃል እገባለሁ፡፡

እምነትን መተቸት

የብዙዎቹ ሃይማኖቶች መሠረት እምነት መሆኑ ይታወቃል፤ እምነት ደግሞ ብዙውን ጊዜ የሚቆመው በማስረጃ ሳይሆን በእምነት በራሱ ነው፡፡ የእምነት እና የሃይማኖትዋጋ ባልሰለጠኑ አገራት ከፍተኛ ነው፤ ይህንን የሚያሳዬ በተለያዩ ጥናቶች ሲኖሩ፥ እንደምሳሌም፣ ኢ-አማኒዎች በአውሮፓ አገራት እስከ 60 በመቶ ቢደርሱም ከሰሃራ በታች በሆኑ የአፍሪካ አገራት ግን ከ1 በመቶ በታች ናቸው፤ በኢትዮጵያም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ የእምነት ዋጋ፣ በትችት ባሕላችን ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ቅዱስ መጽሐፍቶችን እና አምልኮተ ስርዓቶችን የማይመረመሩ፣ የማይገመገሙ እና የማይሻሩ ሆነው እንዲቀሩ በማድረጉ ዛሬም ድረስ በድሮ ጋሪ እየተጎተቱ ለመኖር የሚያስገድድ ሁኔታ እንዲፈጠር መንስኤ ሆኗል፡፡ ይህ ከትችት ባሕላችንጋ ምን ያገናኘዋል የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እምነት አጥባቂ የሆኑ አገራት ሕገመንግስታቸው ላይ የሚኖራቸው አመለካከት እና ቅዱስ መጽሐፍታቸው ላይ የሚኖራቸው አቋም እምብዛም እንደማይራራቅ ይሰማኛል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ድርሻ የያዙት ክርስትና (በተለይም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ) እና እስልምናን ብንመለከታቸው ከሌላው ዓለም ትንሽ ለየት ያለ ገጽታ አላቸው፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎችም ከባሕሉ ጋር ተቀላቅለው፣ አንዳንድ ባሕላዊ ወጎች እንደሀይማኖቱ ቀኖና፣ አንዳንድ የሀይማኖት ስርዓቶችም እንደባሕሉ መሰረት ሆነው ቆመዋል፡፡ በውጤቱም ሁለቱንም መንካት የማይቻልበት ድባብ ፈጥሯል፡፡

እንደምሳሌ አንድ ጠቅሰን እንለፍ፡፡ ሕዝብ በሚበዛባቸው የመኖሪያ ስፍራዎች ቤተክርስትያኖች እና መስኪዶች ተመስርተዋል፡፡ ሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የሆነ ድምጽ በሌሊት ያወጣሉ፣የአምልኮ መዝሙር/መንዙማቸውን ካሴት ለማስተዋወቅ ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ በከፍተኛ ድምጽ እያስጮሁ ያስተዋውቃሉ… ይህ እውነት በሁሉም ሰው የሚታወቅ ገሀድ ቢሆንም እልባት ይደረግለት በሚል፣ ለመንግስት አቤቱታ የሚቀርብበት ፊርማ የሚያሰባስቡ ወገኖች ቢፈጠሩ ውጤቱ ምን የሚሆን ይመስላችኋል? ተቆርቋሪ ነን የሚሉትና የሚቃወሙት ወገኖች በምክንያት ማስረጃ ለመበላለጥ እና ለማሸነፍ የሚደራደሩ ወይስ ቤተ ሃይማኖቴ ተደፈረብኝ በሚል ጦርነት የሚካፈቱ?

ብሔር ነክ ትችቶች

ብሔር ነክ አስተያየቶችን መሰንዘር በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከነውርም የከፋ ነውርም እየሆነ መጥቷል፡፡ አንዱ በሌላው ላይ በአነጋገር ዘዬው (ሌላው ቀርቶ በአንድ ቋንቋ አሜሪካዊው በእንግሊዛዊው ወይም በተቃራኒው) መቀለድ የተለመደ ነው፡፡ ወደእኛ አገር ሲመጣ ግን ዘረኝነት፣ ጥላቻ እና ጭቆና የሚል ባጅ ይለጠፍበታል፡፡ ቀልድ እንዲህ የሚያስፈርጅ ከሆነ መሠረታዊ የሆነ ትችት ምን ሊያስከትል እንደሚችል ማሰብ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

‹‹የሃማሴን እና አጎራባች ነዋሪዎች/ተወላጆች አንበጣ (‹‹ክረምት አግቢ››) ይመገባሉ፤›› ብሎ የሆነውን ሆነ ቢል በማሕበራዊ የስነምግባር ሕግ የሚያስቀስፍ ወንጀል ነው፡፡ ከወዲያኛውም ሆነ ከተናጋሪው ወገን እነዚህን እንስሳት መብላት ምንድን ነው ጥፋቱ? ወይም እነዚህን መብላቱ እንዲህ ዓይነት ችግር ያስከስታል እያሉ ለትችቱ መመከቻም ሆነ ትችቱን ለማቅረቢያ ምክንያት መደርደርን ከግምት ውስጥ የሚያስገባ ማግኘት ዘበት ነው፡፡ ለሚበሉት አለመብላቱ እንደሚያስገርም ሁሉ ለማይበሉት ደግሞ ያስፀይፋል፤ በመጨረሻም የማይበለት በቁጥር ስለሚበዙ ነገሩንም ንግግሩንም የማነወር አቅም ያካብታሉ፡፡በተመሳሳይ የዚህ አይነት የብሔር ነክ ትችቶች እና ተያያዥ ጉዳዬች ማንሳት ጉዳዬን ከሚፈጽሙት በላይ ዘረኛ እና ሃጥያተኛ ያደርጋል፡፡

ቤተ ፖለቲካን መተቸት

ከተቃዋሚ እስከ ገዢው ፓርቲ ድረስ ቤተ ፖለቲካን መተቸት ከመፈረጅ አንስቶ እስከ መፈጀት ድረስ የሚያደርስ ቅጣት ያስከትላል፡፡ የገዢው ፓርቲ በአንድ በኩል ሥራዬ፣ ፖሊሲዬ፣ አመራሮቼ፣ አስተዳደሬ፣አመራሬ ፍፁም ነው የሚመስል ክርክር ሲከራከር፣ ተቃዋሚዎች በእኩል ድምፅ ሥራህ፣ ፖሊሲህ፣ አመራሮችህ፣ አስተዳደርህ፣ አመራርህ ፍፁም የተሳሳተ ነው የሚመስል ምላሸ ያሰማሉ፡፡ የገዢው ፓርቲ ባሕርይ ከጥንት ነገሥታቶቻችን ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ነው፤ ንጉሥ አይሳሳትም፡፡ እንዲያው ገዢው ይሳሳታል ያሉት አምላክን ከተቃወሙት አይተናነሱም እና ቅጣት ይገባቸዋል፡፡ ይህንን የሚያውቅ ገዢውን አይተችም፡፡

ተቃዋሚዎችን ያየን እንደሆነም ተመሳሳይ ድራማ በግልባጭ እናያለን፡፡ ተቃዋሚዎች ለመቃወም ብቻ የተፈጠሩ እስከሚመስል ድረስ(ያሉበት የፖለቲካ ምህዳር ጥያቄ እንዳለ ሆኖ) አንድም የራሳቸውን ፖሊሲ ወይም የረባ የፖሊሲ ትንታኔ ሰርተው ሲያሳን አያስተዋልም፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ‹‹እሺ ገዢው ፓርቲ ከተሳሳተ ምንድን ነበር ማድረግ የነበረበት?›› ተብለው ቢጠየቁ ጠያቂያቸውን ጨዋ ከሆኑ‹‹ተቃዋሚዎችን መተቸት ትግሉን ይጎዳዋል›› በሚል በአብዛኛው ደሞ ‹‹አንተማ ወያኔ ነህ›› የሚል ፍረጃ ሊያከናንቡት ይችላሉ፡፡

ታሪክን መተቸት

ነገሥታቱ ዜጎቻቸውን የኔ የሆኑ እና የኔ ያልሆኑ በማለት ተከፋፍለዋቸው እንደሆነ መረጃ የለኝም፡፡ የዛሬ ኢትዮጵያውያን ግን ነገሥታቱን የኔ የሆኑ እና የኔ ያልሆኑ በማለት ሊከፋፈሏቸው ይሞክራሉ፡፡ በተከፋፈሉት መሠረትም ‹‹አፄ ዮሓንስማ ትክክል ነበሩ፣ ምኒልክ አበላሹት እንጂ… የለም አፄ ቴዎድሮስ ናቸው ያበላሹት፤›› እየተባባሉ የኔ ያሉትን ይቀባሉ፣ የኔ ያላሉትን ደግሞ ያራክሳሉ፡፡ የአገራችን ታሪክ ከነገሥታቱ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ የአገሪቱን ታሪክም እንዲሁ በማጥላላትና በማወደስ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርጉታል፡፡

ችግሩ ያለው ትችቱ መሠረት ላይ ነው፡፡ የትችቱ መሰረት (አመክንዮ) ሥራ ወይም የሥራ ውጤት ሳይሆን የግል ዝንባሌ (ምርጫ)፣ ወይም የግል ጎሣ ሆኖ ተደጋግሞ ይስተዋላል፡፡ በሌላ በኩል የዘመኑን ሁኔታ እና የዘመኑን ልሂቃን ዕውቀት ከግንዛቤ ውስጥ ባላስገባ (ወይም በዚህ ዘመን መለኪያ) ታሪክን መገምገም የራሱ የሆነ ድክመት ያለበት ሲሆን፣ አንንዶቻችን ታሪካችንን እና ባለታሪኮቻችንን የምንተቸው በተሳሳተ መለኪያ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በታሪክ ረገድ በዚህ ወቅት ያለው ትልቁ ችግር ባብዛኛው በተሳሳተ መንገድ መተቸት ሲሆን፡፡ ለሚዛናዊው አተቻቸትም ቢሆን በምላሹ ለጦርነት የማይዘጋጁ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡

የታሪክ አባቶችን ስንዘክር/ስንወቅስ ግዴታ በፍፅምና መሆን አለበት የሚል መመሪያ የለም፡፡ የታሪክ ፋይዳው ለመማሪያ እንጂ ለመፈራረጂያ አይደለም በሚለው ከተስማማን፣ ለምሳሌ በአንድነት ጉዳይ ሊዘከሩ/ሊወቀሱ የሚገባቸው ካሉን በጉዳዩ ብቻ መዘከር/መውቀስ ብቻ ሲቻል፣ የዛሬ ሰው ለአንድነት በሚሰጠው ዋጋ መዝኖ ‹ያ ንጉሥ› ለአንድነት ስለሠራ/ስላልሠራ በሚል ንጉሡ በሕይወት ዘመኑ ተሳስቶ የማያውቅ/ትክክል ሆኖ የማያውቅ አድርጎ ታሪክን በተሳሳተ መንገድ በመጻፍ ሌላ የታሪክ ተጠያቂ ከመሆን አያድንም፡፡

ግለሰቦችን እና ክስተቶችን መተቸት

በግለሰቦች ጉዳይ የትችት ባሕላችን መጀመሪያ የውዳሴ ብቻ ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የርግማን ብቻ የማይሆንበት ዕድል የለም፡፡ ‹‹ቀድሞ ማመስገን ቆይቶ ለማማት አይመችም›› የሚለው አባባልም ያመሰገኑትን ሲያጠፋ መውቀስን ለማነወር የተፈጠረ ቃል ይመስላል፡፡ ፍፁም ሰው በሌለበት ዓለም ወይ ፈፅሞ ማመስገን ወይም ፈፅሞ መውቀስ ብቻ ናቸው አማራጮቹ፡፡

ፍፁም ቅዱስ የማድረግ እና የማርከስ ሥራ ባሕላችን ላይ በሰፊው እንደሚታይ ከላይ የተጠቀሰው አባባል አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በባሕላችን አንድን ግለሰብ በመልካም እና ተወዳጅነት ዘመኑ ስህተቱን የመንገር ልምድ የለም፤ ማወደስ ብቻ የበዛበት ቆይታ ይኖረውና አንድ ትልቅ ስህተት ሲሰራ የተወደደበት እና የተወደሰበት መልካም ሥራ ሁሉ ቀርቶ ርግማኑ ብቻ ይወራል፤ በዚህ ወቅት የሱን መልካም የሚጠቅስ ሰው ቢኖር ከማስረገም በተጨማሪ የእኩይ ስራው ተባባሪ የሆነ ያክል ሁሉ ሊቆጠር ይችላል፡፡

አቶ ልደቱ አያሌውንና ምርጫ 97ትን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን፡፡ በተለይ በምርጫ 97 ተከስቶ የነበረውን የተቃዋሚ ጎራ በመክፈል ትልቁን ሚና እንደተጫወቱ የተነገረላቸው አቶ ልደቱ (በርግጥ በቅስቀሳው ወቅትም ትልቁን ሚና ተጫውተው ነበር፤) ከምርጫው በፊት ከአምልኮ ባልተናነሰ ተወድሰው፣ ከምርጫው በኋላ ደግሞ ከስይጣን ባልተናነሰ ተወግዘዋል፡፡ አትሌቶቻችን ብዙ ጊዜ ይህንን ተጋፍጠውታል፡፡ በአሁኑ ሰአት ቴዲ አፍሮን መተቸትም ቤተ ክርስትያን የማቃጠል ያህል እነደሚሆን አይተናል፡፡ሟች ጠ/ሚር መለስ ዜናዊን በአሁኑ ሰዓት መተቸት የሚያስቀስፍ ሃጥያት ሆኖ የተቆጠረ ሲሆን፣ በተቃዋሚዎች ሰፈር ደግሞ ማወደስ ሊያስነቅፍ ይችላል፡፡

የአመክኗዊ ትችት ዋጋችን (የAppeal to Popularity ጥገኝነት)

በክርክር ባሕላችን ውስጥ የተከራካሪው ብዛት፣ እና የደጋፊው ብዛት እንጂ የመከራከሪያ ነጥቡ ዋጋ አነስተኛ ነው፡፡ ምንም እንኳን ይህ ዓይነቱ ነገር በሌላውም ዓለምም ሊኖር የሚችል ቢሆንም በአገራችን የጎላ ነው ብሎ መሟገት ይቻላል፤ ለዚህ እንደምክንያት የማስቀምጠው የዘመናዊ ትምህርት ተዳራሽነት እና የክርክር ባሕላችን አለመዳበሩን ነው፡፡ የሆነ ሆኖ በአገራችን ትችት አሰጣጥ ልምድ መሰረት መከራከሪያ ነጥቡ (አመክንዮው ወይም the logical reasoning) ቢያመዝንም ብዙ የሐሳቡ ደጋፊ ከሌለ ተከራካሪው ተሸናፊ ነው፡፡ ተሸናፊነት ደግሞ በሐሳቡ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን (ምናልባትም እስከመገለል) የሚያደርስ ማሕበራዊ ቅጣት አለው፡፡

እንደውም አብዛኛውን ጊዜ ‹‹ድፍን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያምንበትን ነገር ትክዳለህ/ጃለሽ እንዴ?›› የሚል ሙግት ሊገጥማችሁ ይችላል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ጥርሰት የፈላስፋ ምሁራን Appeal to Popularity ይሉታል፡፡ ብዙሐኑ በነፈሰበት መንፈስ፡፡

በአገራችን፣ ሰዎች የሐሳብ ልዩነታቸውን እንደጥንካሬ በሚቆጥሩበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሆነ እምነት መከተል፣ ወይም የሆነ ሐሳብ መደገፍ ከሕይወት የመቀጠፍ አደጋ ይጋርጣል፡፡ ብዙሐኑ የሚደግፉትን መደገፍ ወይም መቃወም ትቶ የራስን አቋም መያዝ ቢያንስ በጥርጣሬ ዓይን ውስጥ ይጥላል፣ ሲከፋም ‹‹መሃል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይሞታል››… እንዲሉ ያደርጋል፡፡ አንድን ግለሰብ፣ ወይም ክስተት መተቸት የግለሰቡ ጠላት ወይም የክስተቱ ተቃዋሚ እንደሆነ እንጂ ለግለሰቡ መሻሻል ወይም ለክስተቱ ማጠናከሪያ የሚሆን ሐሳብ አዋጪ አድርጎ አያጽፍም፡፡

በጥቅሉ በባሕላችን ተቃራኒ ሐሳቦችን አቻችሎ የማየት እና የመረዳት ቅን ልቦና ይጎድላል፤የሥልጣኔ ዋና መንገዱም ይሄው ብቻ ስለሆነ ግን ትችት ለዘላለም ይኑር!!!

No comments:

Post a Comment