Tuesday, October 2, 2012

ቀዩ መስመር
የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከፓርላማ ንግግሮቻቸው ባንዱ ‹ቀይ መስመር› ሲሉ የገለፁት መስመር ነበር፡፡ ያ ቀይ መስመር ዛሬ ስሙ በቀጥታ ባይነሳም በአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትርም እንደሚታወቅ ለቪኦኤ የእንግሊዝኛው አገልግሎት የሰጡት ቃለ ምልልስ ያሳብቃል፡፡ ቀዩ መስመር ለኛ የማይታየን ነገር ግን ለገዢዎቻችን ብቻ የሚታያቸው፣ እኛ ሳይገባን ፍርድ ቤቱ ገብቶት የሚፈርድበት እውነት ሆኖ አልገለጥልህ ቢለኝ ይህን ጻፍኩ፡፡

ደርግ ስሙ የገነነበትን ጭቆና ኢሕአዴግ አጠናክሮታል፡፡ በጊዜው ‹‹አስገንጣይ፣ አሸባሪ፣ ድልድይ አፍራሽና ነጭ ለባሽ›› እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት አሁን ባለተራ ሆነው ሌሎችን እነርሱ ይጠሩበት በነበረው ስም ለመጥራት በቅተዋል፡፡ በዚህ አያያዝ ደርግ እነርሱን ከፈጠረ እነርሱም በበኩላቸው ሌላ ጨቋኝ/አምባገነን ለመፍጠር እየተጉ ነው ያስብላል፡፡

እስከዛሬ ብለነው፣ ብለነው የነበረውን ለአዲሱ አመራር (‹‹አዲስ›› ካለ) መድገም ሳይኖርብን አይቀርም፡፡እናም እንጠይቃለን?ለምን በወረቀት ላይ ያለውን ዲሞክራሲ መሬት ላይ አታወርዱትም? ለስንት ዓመታትስ አንድ ፓርቲ ለስልጣኑን ለማስጠበቅ ብቻ እንዲህ ይተጋል? ለምንስ ዜጎች ወደ ፍርሐት ጥግ ተገደው ይወሰዳሉ? ለምንስ መብቶቻቸው ይሸራረፋሉ? ለምንስ ነገሮች ከሕግ ይልቅ በባለስልጣን ይሁንታ ይከናወናሉ? (ይህ ከ80ሚሊዮን ሕዝብ ሲቀነስ 5 ሚሊዮን /የፓርቲ አባላት/ ሕዝብ ጥያቄ ነው! መቼም የፓርቲ አባላት እዛው የመጠየቅ እድል አላቸው ብዬ ነው::)

‹‹ደርግ ያለ ወያኔ አይኖርም›› ይባል የነበረው አባባል ዛሬም ራሱን ደግሞ፣ ዛሬ ኢሕአዴግዎችም በተራቸው ግንቦት ሰባትን፣ አርበኞች ግንባርን፣ ኦብነግንና ሌሎችንም ፈጥረው፣ ያለነርሱ የማይኖሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡የግንቦት ሰባት እና መሰል ድርጅቶች መኖር የጋዜጠኞች ማሰሪያ ሰበብ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማስፈራሪያ እና የሚዲያዎች ማጥፊያ ሰበብ ሆኗል፡፡

እነዚህ መራር እውነቶች ኢትዮጵያውያንን ከአገራችን ሌላ አገር ሊያስመኘን ከጀመረ ቆየ፡፡ በአገራችን እንዳሰብነውና እንደፈቀድነው መኖር ዘበት እየሆነብን እንደሆነ የውጭም የውስጥም ቡድኖች ምስክርነት አያሻንም፤ ኑሯችን ይነግረናልና፡፡ ሕግ ሲሻል በመመሪያ ሲብስ በባለስለጣን ይጣሳል፣ ዜጎች እንደሁለተኛ ዜጋ ይገፋሉ፣ መብት ከወረቀት ላይ በቀር የለም፤ መብት ጠያቂዎች ስለምን ሌላ ታርጋ ይለጠፍባቸዋል?

 ምንም እንኳን የጥላቻ ፖለቲካ ያራምዳሉ እያለ ገዢው ፓርቲ ቢከሳቸውም አገር እያስተዳደርኩ ነው ከሚለው መንግስት ይልቅ ሰላማዊ ትግል የሚያካሂዱት ተቃዋሚዎች ኃላፊነት ይሰማቸዋል፡፡ ቢያንስ እነርሱ ነፍጥ አንግተው ድልድይ እናፍርስ ከማለት ይልቅ፣ በመገፋት ውስጥም ቢሆን በሐሳብ ለመሸናነፍ እየታገሉ ነውና፡፡

ዛሬ ላይ እየለማች ነው የምትባለው አገራችን በደርግ 17 ዓመታት የአገዛዝ ዘመን (የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ችግር ቢኖርበትም፣ ባይኖርበትም) እንዳትለማ ጋሬጣ የሆነበት፣ ትግራይን እንገነጥላለን ያሉ ለደርግ የሥራ ጊዜ ዕድል ወይም ፋታ እንኳን መስጠት ያልቻሉ የዛሬዋ ገዢዎችም የተጠያቂዎች ድርሻ አላቸው፡፡ ለአገራችን የድህነት አረንቋ ውስጥ መውደቅ ተወቃሹ የደርግ ርዕዮተ ዓለም ብቻ ሳይሆን፣ ደርግ መሥራት የሚችለውን እንዳይሠራ፣ መነጋገርም ይቻል አይቻል እንዲያሳይ ዕድል ያልፈቀዱለት እነዚህኞቹን ተዋጊ አካላትም ጭምር ነው፡፡

በትግል ወቅት፣ በድልድይ አፍራሽነት፣ በሕዝብ ተቋማት ዝርፊያ እና የሰብዓዊ እርዳታን ለመሳሪያ ግዢ በማዋል፤ በነፃነት ትግል ስም በጦርነት አድምቶና ደምቶ በተራው ከሚጨቁነው ያለጦርነት በመግባባት ሰላማዊ ትግል የሚያካሂደው ተቃዋሚ ኃይል በብዙ መስፈርት ብረት ካነሱት የተሻለ ኃላፊነት እንደሚሰማው ያሳያል፡፡ እነዚህ ዜጎች ምንም እንኳን የየራሳቸው ድክመት ቢኖርባቸውም፣ ያለግድያ ሊመጣ የሚችለውን ለውጥን ተመኝተዋል፡፡ ከነሱ በባሰ ለውጥን አመጣን የሚሉት ካስፈለገ ብረት ማንሳት ወይም ሕጉን ያለአግባብ መጠቀም ይቀናቸዋል፡፡

አለማየሁ ገላጋይ ፍትሕ ጋዜጣ ላይ ባሰፈረው በአንድ ጽሑፉ እንዳለው ‹‹ክብደቱን የማያውቀው ኢህአዴግ ለእስክሪብቶ ታንክ ያዝልሀል፡፡›› ሐሳብን በሐሳብ የመመከት አቅም ማጣት ሐሳብን በማፈን፣ ሌሎችን መቀጣጫ በማድረግ፣ የአሸባሪነት ወይም ሌላ ታርጋ በመለጠፍ ዜጎችን ማሳቀቅ ሕጋዊ ዕውቅና በተሰጠበት አገር መነጋገርን ከባድ ያደርገዋል፡፡ እንደኔ እንደኔ፣ ተነጋግሮ መተማመን የማይችል፣ ወይም ዱላ የሚቀናው አንድም ሐሳብ የለውም፣ አሊያም ሐሳቡ እንደማያሳምን ራሱም ያውቀዋል፡፡ዲሞክራሲ በሌለበት ለምን ስሙ ይነሳል?

መንግስታችን እርሱ ሲፈልገው ካልሆነ በስተቀር የማያከብረውን ሕገ-መንግስት መብት አላችሁ ብሎ ማሳመን ከባድ ሥራ ይመስለኛል፡፡ ከሕገመንግስቱም ባሻገር አገራችን የተፈራረመቻቸው ዓለምአቀፍ ድንጋጌዎችና ስምምነቶች መብታችንንን ደጋግመው ያስታውሱናል፤ እኛም ወግ ደረሰን ብለን ስንጠቀምባቸው ከበስተኋላችን የማናውቀው ታርጋ ተለጥፎብን እናገኛለን፡፡ በዚህ ጊዜ እና ‹‹አይደለሁም›› ብንልም (ከመንግስት ያወቀ ቡዳ ነው እንዲል መሐመድ ሰልማን ‹‹ፒያሳ፤ መሐሙድ ጋ ጠብቂኝ›› ባሰኘው መጣጥፉ) ‹‹አዋቂዎቹ›› ነህ ብለዋልና ‹‹መግባት ወይም መውጣት››፣ አልያም ‹‹ጥምር አገልጋይ›› መሆን የሚባል ቁርጥ ምርጫ ይሰጡናል፡፡

አሁን ደግሞ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም የቀድሞ አለቃቸው ቃና በሚመስል መልኩ፣ሁለት ኮፍያ አድርገን እንደምንጫወት ይነግሩን ጀምረዋል፡፡ የአንድ ዜጋ መብቱን ተጠቅሞ መጻፍ፥ መጻፍ ሳይሆን አሸባሪነት መሆኑ አሁንም ከቀጠለ ዴሞክራሲ ከስሙ በቀር በተግባር የታለ ለሚል ጠያቂ መልሱ ምንድነው የሚሆነው?

ቀዩ መስመር በጨቋኝ በኩል ሲታይና በተጨቋኝ በኩል ሲታይ ቦታው የተለያየ ነው፡፡ ለጨቋኝ፤ ስልጣኑን፣ ገመናውን፣ ባዶነቱን፣ ሙስናውን የሚሳብቅበት፣ ይህም ሥራውን ተአማኒነት አሳጥቶ ስልጣን የሚነሳው መስሎ ከታየውና፤ ያገባኛል ባዮች ተደማጭነትን ካገኙ ያ ‹ቀይ መስመር› ማለፍ ነው፡፡

ለተጨቋኝ፤ መብቱ - ሕገመንግስቱ ላይ የተቀመጠለት፣ ገደቡ - አገሩ እንጂ ባለስልጣን ወይም ፓርቲ አይደለም፡፡ ያገሩንም ጥቅም አሳልፎ አይሰጥም፡፡ የአገራችን ሕጎች ሆን ተብለው ለብዙ ትርጉም ተጋላጭ እንዲሆኑ ተደርጓል፣ በስህተት ያልተደረጉ ካሉም በስህተት እንዲተረጎሙ ይደረጋሉ እንጂ ተቃዋሚዎችን ከማስከሰስ አይመለሱም፡፡ ይህ ደግሞ ሆነ ተብሎ - ለስልጣን ጥብቅና ሲባል የተደረገ እንጂ፣ የቃላት ድህነት ኖሮብን የተፈጠረ እንከን አይደለም፡፡

የሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 9፣ የሕገ መንግሥት የበላይነት በሚለው ስር ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ፡- ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውምይላል (መስመር የኔ)፡፡ በሕገ መንግሥቱ ከላይ የተጠቀሰውን ይዘን አንቀጽ 10 ደግሞ ስለ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲህ ይላል፡-
1.   ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው፣
2.   የዜጎች እና የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡

በዚህ ሐሳባችንን ካጠናከርን ዘንዳ አንቀጽ 29 የአመለካከት እና ሐሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብት ስር ደግሞ፡-
1.   ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፡፡ (የእኔ አስተያየት፡- እውነታው ስንይዝ እንፈረጃለን የሚለው ነው)
2.   ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፡፡ ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሁፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል፡፡ (የእኔ አስተያየት፡- አለ ብለው ቢተነፍሱ እንደማስረጃ ተቆጥሮባቸው የተለጠጠ ትርጉም ባለው ‹እንዳበጁሽ› በሆነው ሕጋችን ዜጎች ለስደትና ለእስር ተዳርገዋል)

መብቴን በቴሌቪዥን ብቻ ማየት አልፈልግም ወረቀት ላይ የተጻፈው ብቻውን ምንም አያደርግልኝም የምንፈልገው መብታችን ወደመሬት ይወርድ ዘንድ ተግባራዊ እንዲሆንና ሕግ እንዲከበር ነው፡፡ እናስቀጥላለን የተባለው ‹ልማት› ይቀጥል፣ ፍረጃውና ዜጎችን ማግለሉ ግን አያግባባንምና ይቁምልን፡፡ መቼም የማንግባባበትን ቀይ መስመር ማስመሩ የተሻለ ጨቋኝ ለመሆን መጣጣር ካልሆነ በቀር የትም አያደርሰንም፡፡

No comments:

Post a Comment