Wednesday, November 21, 2012

የሰሞኑ ጦማሮች እፍታ
በጦማር ድርቅ እንደተመታን ያወቅኩት (በርግጥ በፍቃዱም በባለፈው ሳምንት ጠቅሶታል) ይህን  የዚህ ሰሞን የጦማሮች እፍታ ለማጠናቀር ስሰናዳ ነው፡፡ ሌላው ችግር ጦማሮቹ መከፈት አለመቻላቸው ነው፡፡ በአብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ የታገዱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም እንዳስተዋልኩት ከሆነ ብዙዎቹ ጦማሮች በሳምንት ውስጥ አዲስ ነገር ይዘው የመውጣታቸው አጋጣሚ ጥቂት ነው፡፡ እንግዲህ በነዚህ ፈተናዎች መካከል አልፌ ያገኘኋቸው ጦማሮች የሚከተሉትን ይመስላሉ፡፡

“ኢትዮጵያ፡አስታውሳለሁ!” የሚል ጦማር ያስነበበን የፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም የሆነው አልማርያም የጦማር ገፅ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ በዚህ ጦማራቸው በሃገራችን በ1997ዓ.ም ተካሂዶ የነበረውን የምርጫ ውጤት ተጭበርብሯል ብለው ተቃሟቸውን ለመግለፅ በወጡ ንፁሃን ዜጎች ላይ የደረሰውን የሞትና የመቁሰል አደጋ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በወቅቱ ይህን ጉዳይ ለማጣራት በመንግስት የተቋቋመው ኮሚሽን የሞቱት ቁጥር 193 እንደሆነ እና 763 ደግሞ እንደቆሰሉ ቢያሳውቅም ኮሚሽኑ እንዲያጣራ የተደረገው ከግንቦት 29-ሰኔ 1 1997ዓ.ም እና ከጥቅምት 22-23 1998ዓ.ም ድረስ ያለውን ብቻ በመሆኑ የተገለፀው ቁጥር ትክክለኛውን አሃዝ ማሳየት እንደማይችልም ፕሮፌሰሩ በፅሁፋቸው ይልፃሉ፡፡ በተጨማሪም የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትንና ለእስር የተዳረጉ የሚያስታውሷቸውን ኢትዮጲያውያን ዝርዝር አካተዋል፡፡ ከአመት በፊት ፍትህ በማጣቱ እራን ለማቃጠል የተገደደው የኔሰው ገብሬም በፕሮፌሰሩ ታውሷል፡፡ ሙሉውን ለማግኘት ይህን ተጫኑ፡፡


“በጋዜጠኝነት እና በሽብር መካከል” በሚል ርዕስ <አሸባሪ> የሚል ክስ ቀርቦባቸው ስለነበሩ ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኖች ያስነበበን አለማየሁ ፋንታው ወልደማርያም ራሴላስ በተሰኘው ጦማር  ነው፡፡ ፀሃፊው ዶ/ር ሲሳይ አለማየሁ የተባሉ ፊንላንድ የሚገኝ ዩንቨርስቲ አስተማሪ ፌስ ቡክ ላይ በሰጡት አስተያየት ላይ ተንተርሰው የተሰጡ የተለያዩ አስተያየቶችን፣ ስለ ጋዜጠኞቹ መፈታት እና ሶማሌ አካባቢ ስለሚገኘው የነዳጅ ፋብሪካ ለመዘገብ መጡ መባሉን አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግስት ስለሰጠው ማብራሪያ በስፋት የሚያወራ ሲሆን በመጨረሻም ፀሃፊው በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠ/ሚኒስቴር አቶ መለስ “ጋዜጠኝነት ይኼ ከሆነ፤ ሽብርተኝነት ምን እንደሆነ አላውቅም” ማለታቸውን አስታውሶ እሱ ደሞ “ሽብርተኝነት ይኼ ከሆነ፤ጋዜጠኝነት ምን እንደሆነ አላውቅም” በማለት ፅሁፉን ይጨርሳል፡፡ ሙሉውን ለማግኘት ይህን ተጫኑ፡፡


ፊንፊኔ የተባለ ጦማር ባለፈው ሃሙስ “የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አዲስ አባላት” በሚል ርዕስ መቀመጫው ጄኔቫ ለሆነው ምክር ቤት  ከተመረጡት አሥራ ስምንት ሃገሮች ብቃት ያላቸውና መመዘኛውን የሚያሟሉት አንድ ሦስተኛ ብቻ መሆናቸውን የመብቶች ተሟጋቾቹ መግለፃቸውን እና ከተሟጋቾቹ አንዱ የሆነው ሂዩማን ራይትስ ዋች ከተመረጡት ሃገሮች መካከል ኢትዮጵያን አንስቶ በሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ከሚታወቁ ሃገሮች አንዷ እንደሆነች ማመልከቱን ይናገራል፡፡ ዝርዝሩን እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡

ይኸው ጦማር ባሳለፍነው አሁድ “የጀርመኑ ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮውን ዘጋ!” በሚል ርዕስ በጀርመናዊው የኖቤል (ሽልማት) ተሸላሚ በእውቁ ደራሲ ኤንሪሽ ቦል ስም የተመሠረተው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በኢትዮጵያ ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶችን ለማበረታታት ሲያደርግ የቆየውን እንቅስቃሴ  በዘርፉ ማለትም ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች  ላይ ሃገራችን ባወጣቻችው ገደቦች ምክንያት አቋርጦ ለመውጣት መገደዱን አስነብቦናል፡፡

ሚኒሊክ ሳልሳዊ የተባለው ጦማር ደግሞ በባለፈው ሰኞ “የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ (ሸንጎ) ከፍተኛ አመራር ካውንስል መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ፤ ውሳኔዎችን አስተላለፈ” የሚል ወሬ አስነብቦ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ (ሸንጎ) ከፍተኛ አመራር ካውንስል መደበኛ ስብሰባውን አካሂዶ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና የሸንጎውን ድርጅታዊ ሁኔታ በሰፊው መገምገሙን እና ከፈላጭ ቆራጩ የአቶ መለሰ ዜናዊ ሞት በኋላም ያለውን እውነታ፤በገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ እየታየ ያለውን ውስጣዊ ሁኔታና በሀገሪቱና በሕዝቧ ላይ እያስቀጠለው ያለውን ፖሊሲውን በመመርመር፤  የሸንጎውን አጠቃላይ ወቅታዊ የትግል አቅጣጫ ማፅደቁን በጦማሩ ላይ የተገለፀ ሲሆን የሸንጎው ከፍተኛ አመራር ካውንስል  ካፀደቃቸውን ዝርዝር ጉዳዮች አንዱ
“የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት እና የፀጥታ ኃይሎች እጅግ አሰችጋሪ በሆነ የፖለቲካ ሁኔታ ውሰጥ በህጋዊነት በመንቀሳቀስ ላይ
በሚገኙት ታቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በተለይም ደግሞ በመኢአድ እና በመድረክ አባላት ላይ የሚወሰዱትን ቀጣይ የማስፈራራት፣የማሰር፣ የድብደባ፣ የንብረት ነጠቃ አና በሀሰት ክስ በመወንጀል የኢሰብአዊ እስራትና ማሰቃየትን ሸነጎው መርምሯል። በተለይም ደግሞ በቅርቡ በመኢአድ አባላት ላይ በመላ ሃገሪቱ የተከፈተውን የጥቃት ዘመቻ እንዲሁም የመድረክ እና የመድረክ አባል ድርጅቶች አመራር አባላትን በግፍ በእስር ማሰቃየት መቀጠሉን አስተውሏል። ምክርቤቱ ይህን ቀጣይ የመብት ረገጣ በጥብቅ እያወገዘ ጥቃት እየደረሰባቸው ካሉት ድርጅቶችና አባሎቻቸው ጋር ሸንጎው ያለውን የትግል አንድነት ገልጿል።”
ሲሆን እዚህ ላይ ሙሉ መግለጫውን እዚህ ማግኘት ይቻላል፡፡

የአቤ ቶኪቻው የእሁድ ጦማር ደግሞ “ዜና ኮሚክ፤ ሰዎችን ያሰሩት፤ የመኪና ታርጋዎችን ፈቱ!” ይለናል፡፡ ነገሩ የሆነው ባሳለፍነው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት አካባቢ ነው፡፡ በወቅቱ በቅርቡ በአሸባሪነት ተጠርጥረው የታሰሩት ሙስሊሞችን ለማየት አካባቢው በበርካታ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተሞልቶ እንዲሁም መኪኖችም በብዛት የነበሩ እና ባካባቢው የነበሩ ትራፊኮችም የመኪናዎቹን ታርጋ ሲያነሱ እንደነበር ይነግረናል-አቤ ቶኪቸው፡፡ሰዉም እንዲህ አለ ይለናልታርጋ ከምትፈቱ የታሰሩትን ፍቱ!”፡፡ ትራፊኮቹ ታርጋ ሲሰበስቡ ከሚታዩበት ፎቶ ጋር ሙሉው እዚህ አለ፡፡ 

በመጨረሻ የማየው በዚሁ በዞን9 ጦማር ላይ ባሳለፍነው ሳምንት ለንባብ የበቁትን አራት ጦማሮች ይሆናል፡፡

የመጀመሪያው በዚሁ ጦማር በዞን9 አባላት “ወጣት ሴት የመሆን ጣጣ” እና “ወጣት ወንድ የመሆን ጣጣ” በሚል በተከታታይ ለወጡ ጦማሮች ምላሽ የተሰጠበት “ስለ ወንድና ሴት የመጻፍ ጣጣ” ሚለው የውብሸት ታደለ ፅሁፍ ነው፡፡ ውብሸት በሁለቱ ፅሁፎች ላይ የታዘባቸውን ጉዳዮችና የሱንም ሃሳብ ጨምሮ ያካፈለበት ፅሁፍ ነው፡፡ ሙሉውን ፅሁፍ ለማግኘት ይህን ይጫኑ፡፡

የትምህርት ጥራት ነገር -ክፍል 2” በናትናኤል ፈለቀ የተፃፈው እና ከባለፈው ሳምንት ካስነበበን የቀጠለ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የትምህርት ጥራቱን የሚገዳደሩትን ችግሮች እና መፍትሄ የሚላቸውን የጠቆመበት በተጨማሪም መንግስት ለትምህርት መስክ እየሰጠ ስላለው ትኩረት፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጎልቶ ስለሚታየው የማሰብና የማስተማር ነፃነት አለመኖር፣ ስለትምህርት ጥራት እና ተማሪዎች ተመርቀው ከወጡ በኋላ ስላለው ስራ የማግኘት ፈተና የዳሰሰበት ሲሆን ከተለያየ ቦታ ካገኛቸው የቁጥር መረጃዎችን ጋር በማስደገፍ ነባራዊውን ሁኔታ ያስቃኘበትም ነው፡፡ ሙሉው ጦማር እዚህ ላይ ይገኛል፡፡


ሌላው ዘላለም ክብረት “የዩንቨርስቲው ምህዳር” በሚል አርዕስት ያስነበበን ይገኝበታል፡፡ ዘላለም በዚህ ጦማሩ በመንግስት ዩንቨርስቲዎች የሚታዩትን ‹ትምህርታዊ› ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን እና አሉታዊ ተፅኖአቸውን በጥሩ ሁኔታ ያስቃኘበት ፅሁፍ ነው፡፡ ሙሉውን ፅሁፍ ለማግኘት ይህይጫኑ፡፡

ሰኞ ለት ለንባብ የበቃው የበፍቃዱ ሃይሉ “ስለለውጥ” በተሰኛ አብይ አርዕስት  በተከታታይ ሊያስነብበን ካቀደው ውስጥ ‘ኢሕአዴግ ሥልጣኑን በምርጫ ይለቃል?’ የሚለውን የመጀመሪያው ክፍል ፅሁፍ ሲሆን በጦማሩ ውስጥ ኢህአዴግ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ስልጣኑን ለመልቀቅ የሚቸገርበትን ምክንያቶች በዝርዝር ያካተተ እና ችግሮቹን እንዴት መቅረፍ እንደሚችልም መፍትሄ አሳቦችን አመላክቷል፡፡ በፍቃዱ በዚህ ጦማሩ ጉዳዩን ብትንትን አድርጎ በማቅረብ ያሉትን አማራጮች በአሳማኝ ምክንያቶች አስደግፎ ያቀረበበት ነው፡፡ ሙሉው ጦማር እዚህ ላይ ይገኛል፡፡ 

No comments:

Post a Comment