Friday, November 30, 2012

የጉዞ ማስታወሻ የቀሰቀሰው የጉዞ ማስታወሻ ከታሪካችን ታሪክ ምጸቶችና ቁጭቶች ጋር!


በፍቅር ለይኩን

የበፍቄ የጉዞማስታወሻ4 ዓመታት በፊት ከአንድ አማርኛን አቀላጥፎ መናገርና መፃፍ ከሚችል በእጅጉ ካስደነቀኝ ሰው ጋር ወደ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተጉዤ ነበር፡፡ ይህ ሰው ለሁለተኛው ድግሪ ማሟያ የሚሆነውን የምርምር ጽሑፍ የመጀመሪያዎቹ የሙስሊም እምነት ተከታዮች በነቢዩ መሀመድ ትዕዛዝ ወደ አክሱም ግዛት ያደረጉትን ስደት ዋቢ በማድረግ፡-

አክሱማውያን በወቅቱ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር የነበራቸውን ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ግንኙነቶችን በተመለከተ ለመመረቂያ የሚሆነውን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ከአሜሪካዋ የሜኔሶታ ግዛት ከመጣ አንድ አሜሪካዊ ነጭ ጎልማሳ ጋር የኢትዮጵያችንን የጥንታዊ፣ የማእከላዊና የቅድመ ዘመናዊ ታሪክና ሥልጣኔ እምብርት የሆኑትን ሰሜናዊ ከተሞቻችንን አብረን ተጉዘን ለማየት ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡

ምንም እንኳን በአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ Department of History and Heritage Management/በታሪክና በቅርስ አስተዳደር የትምህር ክፍል፡- ታሪክ፣ አርኪዮሎጂና ቅርስን ባጠናም ስለ ታሪካችንም ሆነ ስለ ቅርሶቻችን በዓይን አይተን፣ በእጆቻችን ዳሰን ምስክርነት ለመስጠት ትምህርቱ ተግባራዊ ድጋፍ የታገዘ ባለመሆኑ ከቃል የዘለለ እውቀት ለማግኘት አልታደልንም ነበር፡፡ አሁንም ድረስ በአብዛኛው በቃል ትምህርት ላይ የተደገፈው የዩኒቨርስቲው የትምህርት ሥርዓት ለዚህ ዕድል እንድንበቃ ሁኔታዎችን የሚያመቻች አይደለም እናም እውቀታችን ፊደል ዘመምነት ሚያጠቃው ነበር ብል ብዙም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡

ይህ አሜሪካዊ የጉዞ ወጪዬን በሙሉ ሸፍኖልኝ በመጽሐፍ ብቻ ማውቃቸውን የትናንት ታሪኮቻችን፣ ዓለምን ጉድ ያሰኘውን ሥልጣኔያችንና ቅርሶቻችንን ሕያዋን ምስክሮችን በዓይኔ ለማየት በመቻሌ ራሴን እንደ ትልቅ ዕድለኛ ነበር የቆጠርኩት በወቅቱ፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው እንኳን አክሱምን፣ ላሊበላንና ጎንደርን ቀርቶ በዚህ በቅርባችን የሚገኙትን ታሪካዊ ቦታዎችና ቅርሶቻችንን ስለ መጎብኘት ማውራት የቅንጦት ያህል እንዳይቆጠርብኝ በሚል አንዳች አሉታዊ ስሜት ውሰጤን ተጫነው፡፡

ትዝ ይለኛል ከጉዞዬ መለስ በኋላ ከመቀሌ ከተማ የመጣችውን የክፍል ጓደኛዬን ስለ አክሱም ቆይታዬ ስነግራት፡- ‹‹ኦ ታድለህ!›› አለችኝ ለካ እሷም ከምትኖርበት ከመቀሌ ከተማ በሁለት መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ብቻ የምትገኘውን አክሱምን ጎብኝታው አታውቅም ኖሯል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአብዛኛው የአቅም ጉዳይ ሲሆን ሲብስ ደግሞ አንዳንዶቻችን ዋንኛ ምክንያት የሆነው ስንፍና ይመስለኛል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ የተመቻቸ አጋጣሚና አቅምም እያላቸው ማንነታቸውን፣ የትናንት ታሪካቸውንና ቅርሶቻቸውን ከመጎብኘት ይልቅ ለአንድ ምሽት መዝናኛ በሺህ የሚቆጠር ገንዘብ የሚመነዝሩትን፣ የአገራቸው ታሪክና ቅርስ ለማወቅ ካላቸው ጉጉት ይልቅ ስለ አውሮፓ ከተሞች፣ የእግር ኳስ ክለቦችና ተጨዋቾቻው የጫማ ቁጥራቸውና ስለሚበሉት ምግባቸው ሳይቀር ሰፋ ያለ መረጃ ያላቸውን የሸገርን ዘመናዊዎችን ሳስብ ወይ ጉድ ለማለት እገደዳለሁ፡፡ ለማንኛውም የበፍቄ የጉዞ ማታወሻ የሰሜን የአገራችንን ክፍል ቆይታ ትዝታዬን ቢቀሰቅስብኝ እኔም የሰሜኑ ጉዞዬ ያጫረብኝን ስሜቴንና ገጠመኜን ለዞን ኝ አንባቢዎች ለማጋራት ስል ብዕሬን አነሳሁ፡፡  

የሰሜን ኢትዮጵያ ጉብኝታችን ላሊበላን፣ ባህር ዳርን፣ ጎንደርንና የትግራይን ዋና ዋና ታሪካዊ ከተሞችንና የቱሪስት መስህቦቻችንና ቅርሶቻችንን ያካተተ ነበር፡፡ በዚህ ጉብኝቴ አስደናቂ ገጠመኞቼ መካከልም ለዛሬ አንዱን ላካፍላችሁ ወደድሁ፡፡ ምናልባት ወደፊት የጉዞ ማስታወሻዬን መለስ ብዬ በመመልከት ስለ ጉዞዬ ገጠመኝና ስለሳደረብኝ ስሜት በሰፊው እተርከው ይሆናል፡፡

በትግራይ ቆይታችን የአክሱምን ሀውልቶች፣ የታሪካዊውን፣ ለአፍሪካውያንንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል የለኮሰውን የአድዋን ሰንሰለታማ ተራሮችንና በዛ ትንግርተኛ ተራራ ላይ አባቶቻችን ጎሳ፣ ሃይማኖት፣ ዘር፣ ወገን ሳይለዩ… ወንድ ሴት፣ ቄስ፣ መነኩሴ፣ ሼኽ አንድ ሆነው ለጋራ ቤታቸው፣ ለጋራ እናታቸው ነፃነት፣ አንድነትና ህልውና በደማቸውና በአጥንታቸው ስለ እማማ ኢትዮጵያ ፍቅር የከፈሉት መስዋእትነት በደም ደምቆና አሸብርቆ ሕያው ሆኖ ከሚታይበት የአድዋ ተራራ ላይ ዓይኖቼ ተሰክተው የትላንትናዋንና የዛሬዋን ኢትዮጵያን እያነጻጸርኩ ከታሪክ ጋር ሙግት የገጠምኩበት ትውስታዬ ዛሬም በኅሊናዬ ነፍስና ሥጋ ነስቶ ሕያው ሆኖ አለ፡፡

የአድዋ የአፍታ ቆይታችንን በኋላ በመንገዳችን ላይ የጎበኘናቸው ሽሬ፣ ሀውዜን፣ የሃ፣ አዲግራትና ደብረ ዳሞ በውስጤ የተዉት ትዝታና ናፍቆት አሁንም ድረስ ሕያው ነው፡፡ በአዲግራት ያገኘናቸው ስለ አክሱማዊው አልነጃሺ ከአባቶቻቸው የተቀበሉትን አፈ ታሪክ የተረኩልን የአዲግራት አልነጃሺ መስጊድ ኢማሞች፣ ሼኽዎችና የዕድሜ ባለጸጋዎች ፍቅራቸውና ልዩ የሆነ ኢትዮጵያዊው መስተንግዶአቸው በልቤ  በማይደበዝዝ ቀለም ታትሞ በውስጤ አለ፡፡ አሁን በጉዞአችን ወቅት በሽሬ ከተማ የተከራየነውን መኪና አቁመን ለጥቂት ደቂቃዎች ባደረግነው ቆይታ ያጋጠመኝን ላውጋችኹ፡፡

ድህነት ክፉኛ ያጎበጣት በምትመስለው በሽሬ ከተማ ላይ ባደረግነው ቆይታችን በጭቃና በድንጋዮች በተሠሩት አብዛኛው ቤቶቿ መካከል እንደ ነገሩ በቆመ የጸጉር ማስተካከያ ቤት አናት ላይ ‹‹ቴዲ ካፍሮ ጽጉር ቤት›› የሚል ስያሜ አየሁና ዓይኔም ቀልቤም ወደዚሁ የጸጉር ቤት ስያሜ ተሳበ፡፡ እናም ለአፍታ ቴዲን፣ የቴዲ አፍሮን የ1997ቱ እና የሚሊንየሙ ዋዜማ ዜማዎቹን፣ የትግራይን ሕዝብ እንወክለዋለን የሚሉትን ፖለቲከኞቻችንና የትግራይ ሕዝብን እያፈራረቅኹ በዓይነ ኅሊናዬ ለመቃኘት ሞከርኩ፡፡

‹‹በአስራ ሰባት መርፌ በጠቀመው ቁንጣ፣
ለለውጥ ያጎፈረው ወንበር ላይ ሲወጣ፣
… አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ፡፡

ሁላችንም ለእርቅ፣ ለእማማ ኢትዮጵያችን ሰላምና ብልጽግና እጅ ለእጅ እንያያዝ፣ ቂም በቀል ይቅር፣  ለሕዝብ ፍቅር ራሱን አሳልፎ የሰጠ ኢትዮጵያዊው ማንዴላ ማን ይሆን… በሚሉና በመሳሰሉ የቴዲ የዜማዎቹ ግጥሞች ኃይለ ቃል ውስጣቸው በበገነ በአንዳድ አፍቃሪ ኢህአዴግ ጥርስ ውስጥ የገባው ቴዲ አፍሮ በትግራይዋ ድህነትና ጉስቁልና በተጫናት ሽሬ ከተማ ያለ ምንም ተቃውሞና ከልካይ ስሙ በትግሪኛ ቋንቋ እንደነገሩ ተወላግደው በተፃፉ የአማርኛ ፊደላት ከፍ ብሎ ተሰቅሎ ማየቴ የጥላቻ፣ የመራርነትና የጽንፈኝነት አባዜ ወዲህና ወዲያ የሚያላጋውን አገሬን ፖለቲካና ፖለቲከኞች እንደታዘባቸው አስገደደኝ፡፡

በአምቻና በጋብቻ የተሳሰረውን፣ የሃይማኖት ልዩነት ድንበር ያልገታው በሐዘንና በደስታ የማይለያየውን፣ የእማማ ኢትዮጵያ የሀገሩ ፍቅር ስሜት በማይበጠስ የፍቅር ሰንሰለት ያስተሳሰረውን የወገኔን የአንድነት ስሜትና መስዋእትንት ከጉራ እስከ ጉንደት፣ ከዶጋሊ እስከ አድዋ፣ ከመቀሌ እስከ ማይጨው፣ ከምጽዋ እስከ ቀይ ባህር በታሪክ መነጽር ወለል ብሎ ታየኝ፡፡

ለእማማ ኢትዮጵያ ነፃነትና አንድነት በጀግኖቻችን ደም የቀላው ቀይ ባሕር አዲስ በተፃፈ ተረት ተረት የአብሲኒያዋ ቅኝ ግዛት ስር ወድቆ ነበር የሚለው የታሪክ ምጸት በኅሊናዬ ገዝፎ ሲታየኝ በደርግ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያንና ኤርትራን ለማሸማገል ተልከው የነበሩት ነፍሰ ኄር አቡነ ፊሊጶስ በእንባ በተቀላቀለበት ድምፅ በሲቃ ሆነው የተናገሩት ቃላቶቻቸው በአዕምሮዬ አቃጨለብኝ፡-

‹‹…እውን አንተ ቀይ ባሕር የአገራችን ጠረፍ እንዳልነበርክና ስለ አንተም የአገራቸው አንድነትና ነፃነት እያንገበገባቸው የሺህዎች ጀግኖች ደም በአንተ ካልፈሰሰማ ታሪክ ይፍረደና…›› በማለት ዕንባቸውን ወደ ባህሩ የረጩበት ጎምዛዛው የታሪካችን ሙሾና እንጉርጉሮ በጆሮዬ ተሰማኝ፡፡

ይህ የአቡኑ ደምፅ በዳሞ ተራራ ከእኔ ጋር ነበር፡፡ በስደት ወደ አክሱም በመጡት ከዘጠኙ ቅዱሳን መካከል አንዱ የሆኑት ሶርያዊው አባ ሚካኤል/በአክሱማውያን አጠራር አባ አረጋዊ በደብረ ዳሞ ተራራ ጫፍ ላይ በገደሙት ድንቅና ታሪካዊ በሆነው በደብረ ዳሞ ገዳም ባደረግነው ቆይታ ስለ ገዳሙ ታሪክና ስለ አባ አረጋዊ ያጫወቱን አባት በገለፃቸው መካከል ከተቀመጡበት ድንጋይ በሩቅ ያለውን ተራራ አሻግረው እያዩ ልጆቼ ያ የሚታያችሁ የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ነው አሉን የተቆራረጠ በሚመስልና ሽምግልና በተጫነው ድምፀት፡፡

በእኚህ አረጋዊ መነኩሴ በንግግራቸው ውስጥ አድማሱን ታኮ በርቀት ድብዝዝ ብሎ በሚታየው ተራራ ላይ የተተከለው ዓይናቸው ለኤርትራና ለኤርትራውያን ያላቸውን ናፍቆትና ስስት በሚገባ የሚያጋልጥ ነበር፡፡ ዘመናት ያላስረጁት በፍቅር የጸና፣ በደም የደመቀ የአንድነታችን አሻራ፣ የእነዚህ ሁለት ሕዝቦች የጋራ ታሪክ ከግዙፉ የታሪካችን ማህደር ደምቆና ጎልቶ ቢታየኝ ዓይኖቼ ዕንባ አቆረዘዙ፣ እኔም ከደብረ ዳሞ ባሻገር በእኚህ መነኩሴ ልብ ያልተረሳችው፣ በታሪክና በአባቴ ትዝታና ትርክት ውስጥ በውስጤ የገዘፈችው ኤርትራ/አስመራ በዓይነ ኅሊናዬ ታየችኝ፡፡

የሽሬው የቴዲ ካፍሮ ጸጉር ቤት ማስታወቂያ፣ ዳህላክ ከሚለው ዜማው፣ ከሁለቱ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በታሪክና በባህል በተሳሰሩ የዛሬዎቹ ሁለት ሕዝቦች ተራ በተራ በአዕምሮዬን ጓዳ መፈራረቅ ያዙ፡፡ ኅሊናዬ ከግዙፉ ታሪካችን መካከል በደም የተመረቀውን በጎሳና በዘር መለያየት የጠየመውን የታሪካችንን ታሪክ ጉድ፣ ጉዳንዳንጉድ ማመላለስ ጀመርኩ፡፡ እናም የተሳፈርንበት የመለያየት፣ የጎሰኝነት ባቡር ማብቂያው የት ሊሆን እንደሚችል ሳስብ ውስጤን የሐዘን ደመና ሸፈነው፡፡

በአንድ ወቅት ፕ/ር መስፍን በአንድ ጽሑፋቸው እንዳሉት፡- ‹‹ባቡሩ በዘረኝነት፣ በጎሳ፣ የጥፋት፣ በመለያየትና በጥላቻ እንዲህ ባለ አስፈሪ ፍጥነት መምዘግዘግና ሊያደርሰው ያለው ጥፋት ሲታሰበኝ እኔም እ-ግ-ዚ-ኦ እ…ማ…ማ…ዬ…፣ እ-ግ-ዚ-ኦ…ኦ…ኦ…ኦ ኢ-ት-ዮ-ጵ-ያ…ያ…ያ…ያ፣ እናት አገሬ… ለማለት ወደድኹ በለሆሳስ፡፡

የበፍቄ የሰሜን ኢትዮጵያ ቆይታው ከአራት ዓመታት በፊት የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ቆይታዬን ቢያስታውሰኝ ትውስታዬን ከታሪካችን ታሪክ በመነሳት እንዲህ ልተርከውና ዛሬያችንን በትናንት የታሪካችን መስታወት እጅግ በጣም በጥቂቱ እንዲህ ልፈታትሸው ሞከርኩ፡፡ እናም በዛች በትንሽዋ የሽሬ ከተማ ከፍ ብሎ የተሰቀለው የቴዲ ካፍሮ ጸጉር ቤት በርካታ የአሳብ ግትልትሎችን በውስጤ አመጣብኝ፡፡

ከያኒው እንደዘፈነውና እንደተመኘልን በቅን ኅሊና፣ በበጎነት፣ በሕዝብ ስለ ሕዝብ ፍቅር የተጋ ንጉሥና መሪ ማየት ሳንታደል በጥላቻና በመረጋጋም አባዜ ተጠላልፎ የወደቀውን ትውልዴን፣ የዘመኑን መሪዎቻችንና ፖለቲከኞቻችንን ሳስብ መጨረሻችን ምን ይሆን አልኩ በልቤ፣ ከልቤ!?

ይቅር እንባባል፣ ቂም በቀል ይቅር በሚል መንፈስ እርቅን፣ ፍቅርን ለአገሩና ለሕዝቡ የሰበከው የወጣቱ ከያኒ ዜማ ዛሬም ተግባራዊ የሆነ ምላሽን ያገኘ አልመሰለም፡፡ ዛሬም እርስ በርሳቸው የሚካሰሱ፣ የአንዱ ውድቀት ጮቤ የሚያስረግጠው፣ ለበቀልና ለጥፋት የተሳሉ ሠይፎች ቁጥራቸው እየተበራከተ ነው፡፡

ዛሬ ዛሬ የእርቅ፣ የፍቅርና የሰላም መዝገብ ናቸው ተብለው በሚታሰቡት የሃይማኖት ተቋማት እንኳን የምናየውና የምንሰማው ጉድ ጆሮን ጭው የሚያደረግ እየሆነ ነው፡፡ ለአብነትም ያህል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እያየነውና እየሰማነው ያለው ነገር ከመስገረም አልፎ ምን ዓይነት ጉድ ነው በሚል እጃችንን አፋችን ላይ እንድንጭን እያደረገን ነው፡፡

የኢትዮጵያው ሲኖዶስ፣ ሕጋዊውና ስደተኛው ሲኖዶስ፣ ገለልተኛ… በሚል መለያየትና እንዲያም ሲል የትግሬ፣ የአማራ፣ የጎንደሬ… አብያተ ክርስቲያናት በሚል በአገር ቤትና በውጭው ዓለም እንደ አሜባ ተከፋፍለው በዓይነ ቁራኛ የሚተያዩትን ቤተ አምልኮቻችንንና አገልጋዮቻቸውን ማሰብ ነፍስን በጣሙን የሚያደክምና የሚፈትን ነው፡፡

እርስ በርሳቸው ተከፋፍለው ያሉ የሃይማኖት አባቶች ለራሳቸውም ሆነ ለሕዝባቸው የሰላም ሰባኪና ፍቅር መስዋእት ሊሆኑ ቀርቶ በእኔ ልሾም፣ አሁን ተራው የወሎ፣ የጎጃሜ፣ የኦሮሞ …ወዘተ በሚል በጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ተዘፍቀው አደባባዮቻቸው የብዙዎች ድኾችና ፍቅርን እውነተኛ ፍርድንና ፍትህን ያጡ የበርካታ ራሄሎችና መጻጉዎች እንባዎች የሚፈሱባቸው የግፍና የወዮታ አደባባይ ወደ መሆን ተለውጠዋል፡፡

እርቅን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ሰላምን የሚሰብኩ ማንዴላዎች ገና በአገራችን የፖለቲካ ሰማይ ላይ ከፍ ብለው ደምቀው ለመታየት አልቻሉም፣ እናም መለያየቱ ጎሰኝነቱ ዘርኝነቱ ከቤተ መንግሥት እስከ ቤተ ክህነቱና መስጊዱ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ የሕዝብ ብሶትና ጩኸት ማሰማት ያለባቸው ስለ እውነት፣ ፍቅርና ፍትህ መቆም ያለባቸው ከያኒዎቻችንም ያልበላንን ሲያኩልን የሚውሉ ላም ባልዋለብ ኩበት ለቃሚዎች ሆነው የጥበብን ንጹህ ነፍስያ ክፉኛ እያጎደፏትና እያሳደፏት ነው፡፡

ለአብነትም ያህል በቅርቡ የጠቅላይ ሚ/ሩን ሞት ተከትሎ እንደ ንዋይ ደበበ ያሉ አቀንቃኞች አቶ መለስን ከሙሴ ጋር ሲያነፃፅሩና ከፈጣሪ ዘንድ ልክ እንደ ሙሴ ሕዝቤን ግዛ ተብሎ የሙሴ በትር የተሰጠው ነቢይ አድርገው በመቁጠር ሲያቀነቅኑላቸው ኅሊናቸውን ትንሽ ስቅቅ አላላቸውም፡፡ ለመሆኑ ንዋይና መሰሎቹ የሊቀ ነቢያትን የሙሴን ታሪክና የአመራር ጥበብ (Exraordinary Leadership Wisdom and Skill) በሚገባ ያውቁት ይሆን ወይስ… ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን፡፡

በፈጣሪው ዘንድ እጅግ ትሑት የሚል ምስክርነትን ያገኘውና የእስራኤልን አምላክ ያሕዌን ፊት ለፊት የማነጋገር ልዩ ክብርንና ዕድልን የተጎናጸፈው ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ከ430 ዓመታት የግብፅ ባርነት ያወጣ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን እንደ ነፍሱ የሚወድ፣ ለሕዝብ ተፈጥሮ፣ ለሕዝቡ ኖሮ፣ ለሕዝቡ መስዋእት ሆኖ ያለፈ ከሰውም ከአምላክም ዘንድ ምስክርነት የተሰጠው መሪ ነበር፡፡

ይህ የዓለማችን ታላላቅና ጥበበኛ መሪዎች ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰደው ሙሴ በአንድ ወቅት ፈጣሪውን ይህን ሕዝብ በምድረ በዳ ከምታስቀረው እኔን ለዘላለም ከሕይወት መጽሐፍ ደምስሰኝ በማለት ለሚመራው ሕዝብ ያለውን ፍፁም ፍቅርና ክብር በተግባር የሳየ ታላቅ መሪ ነበር፡፡ ሙሴ በሕዝቡ ፍቅርና ክብር ራሱን የዘነጋ በመንፈሳዊው ሆነ በዓለማዊው የመሪነት ሞዴል ሆኖ የሚጠቀስ መሪ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት ልዩ የሆነ የአመራር ጥበብና የሕዝብ ፍቅረ የነበረውን ሙሴን ልናወዳድር ብንፈቅድ አቶ መለስና የትግል ጓዶቻቸው ውድና ብርቅ የሆነውን የወጣትነት ወርቃማ ዘመናቸውን በጊዜው ከነበራቸው ምቾትና ወደፊትም ከትምህርታቸው በኋላ ሊገጥማቸው የሚችለውን ከፍተኛ ቦታ እንደምንም በመቁጠር ዱር ቤቴ ብለው ወደ በረሃ የከተሙበት ቆራጥ የትግል መንፈሳቸው ከሙሴ ጋር ሊያመሳስላቸው ይችል ይሆናል ብለን እናስብ እንችል ይሆናል፡፡

በተረፈ ግን ሕዝቡን ከራሱ በላይ በመውደድ ነፍሱን እንኳን ለመስጠት ወደኋላ ያላላውን ሙሴን ‹‹ሥልጣን ወይም ሞት!›› በማለት ማን ወንድ ነው ከወንበሬ የሚነቀንቀኝ የሚል ኃይልን ከሙሴ አመራር ጥበብ ጋር ማወዳደር እብደት ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህ ምርጫ 1997ትን ተከትሎ የሆነውን የንጹሐን ኢትዮጵያውያንን እልቂት፣ ስደትና መከራ ብቻ ማስታወስ ከበቂ በላይ ነው፡፡

በሰሜኑ ጉዞዬ ትዝታ ተነስቶ ውሉ የጠፋ ወደ ሚመስለው ፖለቲካችን የተንደረደረው ጽሑፌ ለዛሬ በዚህ ልቋጨው ወደድሁ፡፡ ወደ ፊት ብንኖርና እግዚአብሔሩ ቢፈቅድ በቀጣይ የጉዞ ማስታወሻዬን ቀኘት በማድረግ በታሪክ፣ በቱባ ባህል፣ ሺህ ዘመናት በሚቆጠርላቸው ቅርሶች ስለ ተዋቡት፣ ትንግርታዊው ሰሜኑ የኢትዮጵያችን የጉዞ ማስታወሻዬ ሌሎች ገጠመኞቼን አንስቼ ጥቂት ለማለት እወዳለሁ፡፡

ሰላም ! ሻሎም!

No comments:

Post a Comment