Tuesday, November 13, 2012

ስለ ወንድና ሴት የመጻፍ ጣጣይህ አጭር ጽሑፍ በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ "ወጣት ሴት የመሆን ጣጣ" በሚል ጽሑፍና ለዚህ ጽሑፍ ምላሽ በተሰጠ "ወጣት ወንድ የመሆን ጣጣ" በሚል ጽሑፍ አነሳሽነት የቀረበ ነው።

ስለስርዓተ ጾታ የሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች በተለያዩ የልማድ ማነቆዎች የታሰሩ ናቸው። ከመጀመሪያው ዙር የፌሚኒስቶች ንቅናቄ በኋላ የተፋፋመው የስርዓተ ጾታ ጉዳይ የአብርሆት ዘመን ፍልስፍናን ኋላ ቀር ሊያስብለን በሚያስችል ደረጃ ግሩም ሐሳቦች የቀረቡበት ነው። ከግሪክ ፈላስፋዎች ጀምሮ አብዛኞቹ የቅድመ ፌሚኒዝም ፈላስፋዎች ስርዓተ ጾታን በተመለከተ የጻፉት ሐሳብ ከሰው ልጅ ልማድ መላቀቅ ያልቻለ ነው። ይህን አስተሳሰብ በአግባቡ ለመቃኘትና ክርክሮቻችንን አዲስ መልክ ለመስጠት የፌሚኒስቶችን ሐሳብ መዳሰስና የቅርብ ጊዜ ፀረ-ፌሚኒዝም አስተሳሰቦችን መፈተሽ ያስፈልጋል። በበኩሌ በዞን ዘጠኝ አባላት የተነሱት ነጥቦች የአገራችን የከተማ ወጣቶች ከስርዓተ-ጾታ አንፃር ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ በመግለጽ በኩል በቂ ናቸው ብዬ ባምንም ሁኔታውን በመተርጎምና በመተንተን በኩል ግን ውስንነቶቻቸውን ታዝቤያለሁ። ስለዚህም ጽሑፎቹ ትኩረት የነፈጓቸውን ወይም የዘነጓቸውን ጉዳዮች በአጭሩ በማቅረብ የክርክሩ ሂደት ቅርፅ እንዲይዝ ለማገዝ ጥቂት ነጥቦችን ማንሳት ፈለግሁ። በጉዳዩ ላይ በቀጣይ ሰፋ ያለ ሐሳብ ለማቅረብ ስላሰብኩ ለጊዜው የማነሳቸው ነጥቦች ውሱንና በቀረቡት ጽሑፎች ዙሪያ ያጠነጠኑ ናቸው። 

ጾታዊ ማንነት (Essentialism)

ማንኛውንም ነገር በሁለት ተቃራኒ ጎራ የመክፈል ልማድ (Dichotomy) በስርዓተ ፆታ ጉዳይም የተጠናወተን አባዜ ነው። በራሳችን አዕምሮ ውስጥ የፈጠርናቸው የማንነት ተቃራኒ ምድቦች የራሳቸው ሕልውና እንዳላቸው የመውሰድ አስተሳሰብ ለምድቦቹ ሥነ-ሕይወታዊ ዳራ እንድንሰጣቸው አድርጎናል። ስለዚህም በክርክሮቻችን ውስጥ ሴትና ወንድ እንደ ቋሚ ማንነቶች (Essences) የሚቆጠሩበትና ማንኛውንም ግለሰብ ከሁለት ተቃራኒ የማንነት ቅርጫቶች ውስጥ በአንዱ ለመጨመር የምናደርገው ጥረት ሊፈተሽ ይገባዋል። ይህ አስተሳሰብ በግለሰቦች መካከል ያለውን ልዩነት የዘነጋና የግለሰብ ባህርይ የሚቀዳው ከሁለቱ ተቃራኒ "የተፈጥሮ" ቡድኖች መሃል ካንዱ እንደሆነ ታሳቢ የሚያደርግ ነው። የፌሚኒስቶች ንቅናቄ በጥልቀት የፈተሸው አንዱ እውነታ ይህ ነው። ይህም የፌሚኒስቶች ሙግት "ማንነት" የምንለውን ጉዳይ በእጅጉ የፈተነና "የተቃራኒ ጾታ" የፍቅር ግንኙነትን ታሪካዊ መሠረት ያናወጠ ነው። ይህን ጉዳይ በአግባቡ ለማጤን እንዲቀየሩ የፈለግናቸውን የወንድና የሴት ባህርያት ማሰብ በቂ ነው። እነዚህ ባህርያት ከተቀየሩ ወንድና ሴት የሚባሉ ማንነቶች ከየት ይመጣሉ? ይህን ጥያቄ በስነ-ህይወታዊ ትንታኔ ለመመለስ መሞከር ስርዓተ-ፆታችን ካለበት እንዳይንቀሳቀስ መፍቀድ ነው። ዋናው ነጥብ ግን በሁለቱም ጽሑፎች ላይ ይህ ጉዳይ በልማድ ዕይታ ሙሉ ለሙሉ እንደተሸፈነ መታዘቤ ነው። ይህን ስል አሮጌው የጾታ ስርዓት በቋንቋችን ላይ የፈጠረውን ውሱንነት ዘንግቼ አይደለም።


የእኛ ወጣቶች

በጽሑፎቹ ላይ የተነሱት ነጥቦች የአገራችንን የከተማ ወጣቶች ለይተው የሚመለከቱ ናቸው። ዕይታው ስርዓተ ጾታን የባሕል ውጤት እንደሆነ ከመቁጠር የሚመነጭ ነው። ይህ ሐሳብ በራሱ ችግር አለበት ብዬ አላምንም። Simone de Beauvoir የተባለችው ዕውቅ ፌሚኒስት የስርዓተ ጾታን ባሕላዊ መሠረት በተመለከተ ሰፊና አሳማኝ ሐሳቦች አቅርባለች። ጥያቄው የሚመነጨው ግን የወጣቶቹ መለያ ባሕርያትን በተመለከተ በዞን ዘጠኝ ጸሐፊዎች የቀረቡት ነጥቦች በእኛ ባሕል ውስጥ ብቻ የሚገኙ አለመሆናቸውን ስናስተውል ነው። ለምሳሌ ሴቶች በሬስቶራንቶች መጋ’በዝን ፋሽን እንዳደረጉት የሚኮንን ሐሳብ አለ። በሌላ መልኩ ወንዶች ሐሳቦቿን የምትገልጽላቸው ሴትን እንደሚርቁ ተቀምጧል። እነዚህ እውነታዎች በሌላው ዓለምም የሚታዩና ዓለም አቀፋዊ መሠረት ያላቸው ናቸው።

ጆን ግሬይ "Men are from Mars, Women are from Venus” በሚለው መጽሐፉ ሴቶች ለግንኙነት ትኩረት ስለሚሰጡና ሌሎችን ማገዝ ዋና እሴታቸው ስለሆነ ከወንድ  ገንዘብም ሆነ ሐሳብ መቀበላቸውን እንደመረዳዳት እንጅ እንደጥገኝነት እንደማይቆጥሩት፤ በተቃራኒው ግን ወንዶች ሌሎችን ስለማገዝም ሆነ ስለግንኙነት ግድ ስለሌላቸው ከሌላ ሰው (ከሴቶች) የሚመጣን ሐሳብም ሆነ ገንዘብ መቀበል የዝቅተኝነት (የጥገኝነት) ስሜት እንደሚፈጥርባቸው ይገልፃል። የሴቶችን የሞራል ዕድገት በተለዬ መልኩ ያጠናችው ካሮል ጊሊጋንም ከግሬይ ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ የሴቶች የሞራል ዕይታ ስለሌሎች መኖርን ቅድሚያ እንደሚሰጥ ታብራራለች። በሌላ በኩል Chris Haywood እና Mairtin Mac an Ghaill የተባሉ ጸሐፊዎች "Men and Masculinities" በሚለው መጽሐፋቸው ወንድ ልጅ በአምራችነትና በቁስ አቅርቦት የተወጠረ መሆኑን እያስተዛዘኑ ጽፈዋል። ስለዚህም በዞን ዘጠኝ ጸሐፊያን እንደተሞከረው የወጣቶቹን ባሕርያት ከባሕላችን አንፃር መመልከት ከእናቶቻችን ንግግርና ፍላጎት ጀርባ ያለውን ትልቅ ኃይል ካለማስተዋል ይመነጫል። ባሕሉ የትልቁ ኃይል እጅ እንጅ ራሱ ትልቁ ኃይል አለመሆኑን ልንዘነጋ አይገባም። ይህን ሐሳብ ባንቀበለው እንኳን ቢያንስ የዚህን ኃይል መኖር ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል።

የተዘነጋ ልጅነት

የስርዓተ ጾታ መሠረት የሚጣለው በአብዛኛው በልጅነት የዕድሜ ዘመን ወቅት እንደሆነ ሳይኮአናሊስቶችና ሶሲዮሎጅስቶች ያብራራሉ። እናቶች የልጅ አሳዳጊነትን ሚና በብቸኝነት እየተጫወቱ መሆናቸው ሴት ልጆች የእናታቸውን ሚናና ባሕርይ በቀላሉ እንዲወርሱና ወንድ ልጆች ግን ማንነትን ፍለጋ ወደ ውጭ ለማማተር ክፍት እንደሚሆንላቸው ያስረዳሉ። ይህ ሂደት የትውልድ መተካት (Reproduction) ሚና ለሴቶች ብቻ የቁስ ማምረት (Production) ሚና ደግሞ ለወንዶች ብቻ እንዲሰጥ አድርጓል። ስለዚህም የወጣቶቹ ባሕርይ በአጭር የወጣትነት ጊዜ የመጣ ነው ለማለት የሚያስችል ምክንያት አይታየኝም። ማኅበረሰቡ ከወጣቶቹ የሚጠብቃቸውም ነገሮች ሆኑ መመሳሰልን የሚሰብከው ስርዓት በድንገት የመጣ አይደለም። ወላጆች ከልጆቻቸው የሴትነትን ወይም የወንድነትን መለያዎች የሚጠብቁት እንደዛ እንዲሆኑ አድርገው ስላሳደጓቸው ነው። መቼም ያልዘሩትን ለማጨድ አይመኙም። ለዚህ ነው ትኩረታችን ልጅነትን ዘንግቶ ከወጣትነት መጣበቅ የለበትም የምለው።
    
ብሶት ወለድ ዕይታ

ሌላው ከጽሑፎቹ የታዘብኩት ነገር ወደ መፍትሄ የማያደርሱ ብሶት ወለድ ትንታኔዎች መሆናቸውን ነው። ውስብስቡን ኋላ ቀር የጾታ ስርዓት ለመቀየር በአመዛኙ ኃላፊነቱን ለራሳቸው ለወጣቶቹ የሚተው ይመስላሉ። ከዚያም ሲያልፉ ወደ ባሕላችን ክንዳቸውን ያዞራሉ። ይህ አካሄድ ሩቅ የሚያስኬድ አይደለም። ወንድ አምላክ በሚመለክበትና ቋንቋዎች በፆታ ስልት በተቃኙበት (ለሕይወት አልባ ነገሮች እንኳን የጾታ መለያ በተሰጠበት) ዓለም በትናንሽ የድርጊት ለውጥ የሚመጣ ነገር ቢኖር የመልክ ለውጥ ነው። በዚህ መሐል ስርዓቱ ይበልጥ እየጠነከረና ምክንያታዊ እየመሰለ ይሄዳል። ምክንያታዊ የሚመስልን ስርዓት ለመቀየር ደግሞ አሁን ያለንን የመቀየር ዕድል ያክል ቀላል አይደለም። ስለዚህም ወደ ጠንካራ የፖለቲካ ስትራቴጂ የሚወስዱን ትንታኔዎች ላይ ማተኮር የተሻለ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

በመጨረሻም

በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው በመጻፍ ጥሩ ጅምር ላሳዩን የዞን ዘጠኝ ጸሐፊዎች ለማሕሌት ፋንታሁን፣ ለሶሊያና ሽመልስ፣ ለበፍቃዱ ኃይሉና ለእንዳልካቸው ኃ/ሚካኤል ያለኝን ክብር ገልጨ ሌሎቻችሁ የምትጽፉትን ለማንበብ በመመኘት ባበቃስ?!         

No comments:

Post a Comment