Monday, December 10, 2012

ስለለውጥ፤ አብዮት ወይስ አዝጋሚ-ለውጥ?
‹‹ለውጥ የማይለወጥ ሕግ ነው፤›› አሮጌውን በአዲስ መተካት ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ የቡድን ሥርዓት ለውጥን ማምጣት ነጠላ ለውጥ እንደማምጣት ቀላል እና ተቆጣጥረው በተፈለገው አቅጣጫ በቀላሉ ማስኬድ የማይችሉት መሆኑ ላይ ነው፡፡ በዚያ ላይ የጊዜ ጉዳይ አለ፤ ለውጡ በቶሎ ነው የሚፈለገው ወይስ ቀስ ብሎ ይደርሳል? በአንድ ዘርፍ ነው ወይስ በብዙ ጎኖች?

በአገራችን የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ እንደሚያስፈልግ የሚስማሙ ሰዎች ቁጥር ጥቂት አይደለም፤ የሥርዓት ለውጥ የማይፈልጉት እንኳን ሥርዓቱ በስም ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚታይበት ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጋሉ፡፡ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ብቻውን ለውጡን እውነተኛ ያሰኘዋል? በሁሉም ረገድ ለውጥ ለማምጣት የትኛው መንገድ ያዋጣል? አብዮታዊ ወይስ ዘመን አመጣሽ (አዝጋሚ ለውጥ)?

‹‹ለእያንዳንዱ ትውልድ አንድ አብዮት›› ያስፈልገዋል ይባላል፡፡ በተለይ የሰሜን አፍሪካ ሕዝቦች ረዥም ዓመት የቆዩ መሪዎቻቸውን በአብዮት ከገረሰሱ ወዲህ ባሉት ሁለት ዓመታት ሌሎች ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ሌሎች አገራትም በአብዮት ምጥ ተይዘዋል፡፡ ኢትዮጵያም ከ1960ዎቹ ወዲህ ልታይ የነበረው ለውጥ ምናልባትም የ1997ቱ የምርጫ ለውጥ ነበር፤ አልተሳካም እንጂ ቢሳካ ኖሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ያህ ነበር፣ ሕዝቡም የሥልጣን ባለቤት ይሆን ነበር፡፡

የምርጫው መክሸፍ የተዳፈነ የአብዮት ስሜት ቀስቅሷል ባይ ነኝ፡፡ ያ የተዳፈነ የአብዮት ስሜት በሰሜን አፍሪካውያውኑ አብዮት ተነቃቅቶ አብዮት ይመጣል በሚል ተስፋ የሚያደርጉ ብቻ ሳይሆን፣ አብዮቱን እንመራለን የሚሉም እንቅስቃሴ ጀማምረዋል - ጥቂቶቹ በማኅበራዊ አውታሮች፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ከባሕር ማዶ፡፡ እኔ ግን አሁን ልጽፍ  የምፈልገው ስለእነዚህ እንቅስቃሴዎች አይደለም፤ ‹‹ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አብዮት ነው ወይስ አዝጋሚ-ለውጥ?›› የሚል ጥያቄ ጠይቄ መልስ አፈላልጋለሁ፤ አብረን እናፈላልግ፡፡

አብዮትም ሆነ አዝጋሚ-ለውጥ ሁለቱም የሽግግር መንገዶች ናቸው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ከራሷም ሆነ ከሌሎች አገራት ተሞክሮ በመነሳት የሚያስፈልጋት አብዮታዊ ለውጥ ነው ወይስ አዝጋሚ /ሒደት የወለደው/ ለውጥ የሚለውን በአፅንኦት ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የአብዮት እና የአዝጋሚ-ለውጥ ለውጦች (‘Revolutionary and Evolutionary changes’) ብዙ ተፈጥሯዊና የማይነጣጠሉ (አብረው የሚጓዙ) ባሕርያት አሏቸው ሆኖም ሁለቱም የየራሳቸው መለያም አያጡም፡፡ የአብዮት ለውጥ ትልቅ እርምጃ ባንዴ የሚራመዱበት፣ ከተሣካ የሚፀና ነገር ግን አስፈሪ እና በተግባር ለመተርጎም የሰው ሕይወት የመክፈል ያክል የሚከብድ፣ ብዙ ጊዜ በአንድ የፖለቲካ ወይም ሌላ ስርዓት ላይ በማመጽ የሚመጣ ነው፡፡ የአዝጋሚ-ለውጥ ለውጥ ግን በአንዴ ጥቂት /የማይስተዋል/ እርምጃ የሚሄዱበት፣ አተገባበሩ አደጋ የሌለው ነገር ግን ለውጡን ለማፅናት የሚከብድ እና ረዥም ጊዜ የሚፈጅም ነው፡፡

የቱ ነው እውነተኛ ለውጥ የሚያመጣው? የቱን ለውጥ ነው ሕዝብ የሚፈልገው? የትኛው ለውጥ ነው ለሕዝብስ የሚያስፈልገው?


ለውጥ በፖለቲካው ላይ ብቻ?

ፖለቲካዊ ለውጥ ያለ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ለውጥ ለማምጣት መጣር ባዶ ጆንያ ያለድጋፍ ለማቆም እንደመሞከር ነው፡፡ ሴት ልጅ ከወንድ እኩል መሥራት ትችላለች ብሎ በማይቀበል ማኅበረሰብ ውስጥ የሴት መሪ በአብዮት በማምጣት ተቀባይነት ማግኘት አይቻልም፤ እረፍት የሚበዛበትን የሥራ ባሕላችንን ነፃ ኤኮኖሚ በማወጅ ብቻ ማሻሻል አይቻልም፣ ሃይማኖት ቁጥር አንድ ተቀባይነት ባለበት አገር ላይ ማርክሲዝማዊ ኢ-አማኒነትን በማወጅ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡

በዓለማችን ከታዩ ትላልቅ አብዮቶች ውስጥ የአውሮጳውያን አብዮት ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ በተለይ የእንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ራሽያ አብዮቶች የመንግስት ስርዓታቸውን ብቻ ሳይሆን የምጣኔ ሀብት፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ እሴቶቻቸውን እና ስርዓቶቻቸውን ለውጠዋል፡፡ ይህም ለውጡን የእውነተኛ ለውጥ አድርጎታል፤ ምክንያቱም ማኅበራዊ ስርዓቶች እና ባሕላዊ እሴቶች ከፖለቲካዊ ስርዓቱ ጋር እንዲዋሀዱ ሆነዋል፡፡ እኛምጋ ስንመጣ መጠየቅ የሚያስፈልገን ተመሳሳይ ጥያቄ ይሄው ነው፡፡ የሚመጣው ለውጥ በአብዮት ከመጣ ማኅበራዊ ስርዓቶቻችን (እነ እድር፣ እቁብ እና ማኅበርን መጥቀስ ይቻላል) ምን ያህል ከሚመጣው ለውጥ፣ ርዕዮተ-ዓለም እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ጋር ለመስማማት ተዘጋጅተዋል? ባሕላዊ እሴቶቻችን (እነ ለቅሶና ሠርግ፣ ወዘተ) ምን ያህል ለመጪው ስርዓት ተገዢ እና ተጣጣሚ ናቸው? እነዚህን ጥያቄዎች መጠየቅ የሚያስፈልገው ምንም እንኳን አንድ ሕዝብ በተወሰኑ ቡድኖች መሪነት አብዮት ማስነሳት ቢችልም፣ አብዮቱ ግን ከለውጥ ይልቅ በተደጋጋሚ እንደታየው የጥቂት ቡደኖችን ዓላማ ለማሳካት ብቻ እንዳይሆን ነው፡፡

የላይኛውን አንቀጽ በሌላ ምሳሌ ለማጠናከር ያክል፤ እንበል - የፖለቲካ ሥርዓቱ ላይ በማበይ (አብዮት በማስነሳት) አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊን በሊበራሊዝም በመተካት ብቻ - የሕዝቡን ‹‹ንጉሥ አይከሰስ፥ ሰማይ አይታረስ›› እምነት እንዴት መንቀል ይቻላል? ጭቆናን ታግለው የጣሉ ሰዎች ራሳቸው መልሰው ጨቋኝ እንዳይሆኑ እንዴት ማድረግ ይቻላል? (ምክንያቱም የስርዓቱ ለውጥ ይህንን አያደርግልንም፤ ለማድረግ ቢፈቅድም እንኳን ሕዝቡ ልብ ውስጥ እንዲዘልቅ መልሶ ዝግመታዊ የለውጥ ጊዜ ይጠይቃል፡፡)

አዝጋሚ-ለውጥ ከፖለቲካዊ ስርዓቶች ይልቅ ማኅበራዊ ስርዓቶችን እና ባሕላዊ እሴቶችን ቀስ በቀስ በማረቅ እና ከዘመኑ ጋር በማጣጣም ረገድ ከአብዮት የተሻለ ሚና ይጫወታል፡፡ በአገራችን ሴት ልጆችን ከማጀት አውጥቶ ትምህርት ቤት መላክ፣ ሙዚቀኝነት እንደአዝማሪነት (እንደባላባት አጫዋችነት) ሳይሆን እንደሙያ ማየት እና የመሳሰሉት እየተሻሻሉ የመጡት በጊዜ ሒደት በአዝጋሚ-ለውጥ ነው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ በየከተማው አደባባዮች ዳር ማታ፣ ማታ ለወሲብ ንግድ የሚቆሙ ሰዎችን እንደተራ/የተለመደ ነገር ማየት እና ሌሎችም አሉታዊ ማኅበረሰባዊ ሚና ያላቸውም ነገሮች ለመለመድ የበቁት በአዝሚ-ለውጥ ሒደት ነው፡፡ እንግዴህ የአዝጋሚ ለውጥ ደካማ ጎንም ይኸው ነው፡፡ አዝጋሚ ለውጥ ማኅበረሰቡ ከሁነቱ ድግግሞሽ እና ከሚያደርጉት ሰዎች መበራከት አንፃር እየተለመደ የሚመጣ የለውጥ ሒደት ነው፡፡ ነገር ግን ለውጡ (ባብዛኛው) ታቅዶና፣ መንገድ ተጠርጎለት የሚመጣ ስላልሆነ ወደአንድ ተፈላጊ የሆነ ግብ ያደርሳል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ ነገር ግን በሲቪክ ማኅበራት የሚመራ ለውጥ ብዙ ጊዜ ማኅበራዊ ለውጦችን አቅጣጫ በማስያዝ የሚከናወን ለውጥ ነው፡፡ ስለዚህ ፖለቲካዊ ስርዓቱ ለውጥ ጎን ለጎን የሲቪክ ማኅበራቱ ስርዓትም ለውጥ ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ስናነሳ ፖለቲካዊ ሥርዓቱ ሲቪክ ማኅበራቱን የሚያይበት ዓይን፣ የሚቆጣጠርበት መንገድ እና የሚያደራጅበት መንገድ ማምጣት በሚችሉት ለውጥ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ስለሚኖረው፥ ዞሮ ዞሮ ማኅበራዊ ለውጦች በፖለቲካዊ ሥርዓቶቹ ለውጥ ላይ ጥገኛ ሁነው እናገኛቸዋለን፡፡

በአዝጋሚ ለውጥ የሚመጣውን ማኅበረሰባዊ እመርታ ከአብዮታዊ አመጣሽ ለውጥ ጋር ኩታ ገጠም ማስኬድ ካልተቻለ በቀር እውነተኛ ለውጥ መመኘት ከንቱ ይሆናል፡፡ ለውጡ ፈጣን እንዲሆን እና ኋላ የቀረችውን አገር ወደፊት የሚያራምድ እንዲሆን ‹አብዮት ያስፈልጋታል› ማለት ይቻላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ እሴቶቿን ከፖለቲካዊ ለውጡ እኩል ለማራመድ ስር የሰደደ ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ ‹አዝጋሚ-ለውጡን› መታገስ አሊያም ምን ያህል አዝጋሚ የሚለውን ለማሻሻል ዘዴ መንደፍ ያስፈልጋል፡፡

አብዮት እንደመጠቀሚያ?

የአብዮት አመጣሽ ለውጥ ዋነኛው ችግሩ፣ ድንገት ፈንድቶ በማይቆጣጠሩት እና በማያገናዝቡት ፍጥነት የሚያመጣው ለውጥ ለጥቂቶች መጠቀሚያ ሊሆን የመቻሉ ነገር ነው፡፡ ነባሩን ጨቋኝ በአዲሱ መተካት፤ የራስን ርዕዮተ-ዓለም፣ እምነት እና ፍልስፍና የሚያራምድ ቡድን በብዙሐኑ ላይ መጫን የአብዮት አመጣሽ ለውጥ ጠንቆች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ አብዮቶች ሲከሽፉ የሚታዩት - ሕዝቡ አብዮቱን እውን ካደረገ በኋላ ወደየግል ኃላፊነቱ ወይም የዕለት እንጀራ ወደማሳደዱ ይመለሳል፤ መሪዎች ግን የፈለጉትን ስርዓት መዘርጋት ይቀጥላሉ፡፡ ስኬታማ ታሪክ አላቸው ከሚባሉት የፈረንሳይ አራት አብዮቶች ውስጥ በተለይ የመጀመሪያው የከሸፈ አብዮት ነበር፡፡ ሌሎቹ ሦስቱም የተደረጉበት የሚፈለገው ለውጥ ላይ፣ በተፈለገው ጊዜ እና መንገድ መድረስ ስላልተቻለ ነው፡፡ አሁን በሰሜን አፍሪካ እየተደረጉ ያሉ አብዮት አመጣሽ ለውጦችም ኪሳራቸው ከወዲሁ ከሕዝባዊ እልቂት እስከ ርዕዮተ-ዓለማዊ ጽንፈኝነት ሲጓዙ የሚስተዋሉበት አጋጣሚ አለ፡፡

ወደኢትዮጵያ መለስ ብለን ያለፉት ሁለት ተከታታይ የአገራችንን ለውጦች እውነት ለውጥ አምጥተው ነበር ወይ ብንልም ተመሳሳይ ምላሾችን እናገኛለን፡፡ የሁለቱም ለውጦች ውጤት ቢያንስ ለሁለት ዐሥርት ዓመታት ፀንቶላቸዋል፡፡ የበፊቱ ንጉሣዊ አምባገነንነትን ገርስሶ በወታደራዊ አምባገነንነት ተካው፤ ሁለተኛው ወታደራዊውን ፈንቅሎ ሕገ-መንግሥታዊ አምባገነንነት የሚሉትን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገደብ አልባ ሥልጣን በመስጠት በሕግ ሽፋን የመግዣ (rule by law) አስከተለ፡፡ ይህ የሚያሳየን ኢትዮጵያ ሦስተኛ ለውጥ ብታካሄድም ጉልቻ ከመቀያየር በላይ ለውጥ ላያመጣ ይችላል የሚለው ጥርጣሬ ተገቢ መሆኑን ነው፡፡

ይህ ማለት ግን አብዮት ጭራሽ ፋይዳ የለውም ማለት አይደለም፡፡ የከሸፈ አብዮትም ቢሆን እንኳን ማኅበረሰቦች ያላቸውን አቅም የሚመዝኑበትን ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ አብዮት ሕዝቦች ራሳቸውን ከጨቋኝ ገዢዎች እና ሥርዓት ነጻ የሚያወጡበት አቋራጭ መንገድ እንደሆነ ይነግራቸዋል፡፡ በዕድሜው የአብዮት ጭላንጭል ያየ ትውልድ ከአብዮታዊ ትግሉ መላቀቅ ይከብደዋል የሚል እምነት አለኝ - ስለዚህ እውን እስኪሆን ደግሞም፣ ደጋግሞም ቢሆን ያስነሳዋል፡፡

አብዮትን ውጤታማ ለማድረግ ከተፈለገ በእውነተኛ የአብዮታዊ ለውጥ ሦስት ደረጃዎች ውስጥ ማለፍ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ የቅድመ አብዮት ዝግጅት፣ የአብዮቱ ፍንዳታ እና ድኅረ አብዮት ደረጃዎች፡፡ የቅድመ አብዮት ዘመን እውቀት የመሸመቻ ዘመን ነው - ሊለወጥ ስለሚችሉት ነገሮች እና እንዴት ሊለወጡ እንደሚችሉ የማንሰላሰያ ጊዜ፤ የድኅረ አብዮቱ መጀመሪያ ብዙ ጊዜ በተስፈኝነት ይሞላል፣ የለውጥ አምጪዎቹ (አብዮተኞቹ) አንደበተ ርቱዕ ንግግሮችን ያደርጋሉ - ነገር ግን ተመራማሪዎች ይሄ ተስፈኝነት ብዙም እንደማይዘልቅ እና ተግባሩ ሲጀመር ተቃዋሚ ፅንፈኞች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ እንደምሳሌም፤ የፈረንሳይ እና የራሺያ አብዮቶች እና በአያቶላህ የተመራው የኢራን አብዮት በጠቅላይ ገዥ አምባገነንነት የተተካው በዚህ ሒደት ነው በማለት፡፡

በግብጽ ለተቀሰቀሰው አብዮት ከዐሥር ዓመት በፊት በየጋዜጣው እና በይነመረብ ላይ የሚታተሙት ሕዝባዊ ተዋስኦዎች የቅድመ-አብዮቱ ምልክቶች ናቸው፣ በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የነዋለልኝ መኮንን የብሔር ጥያቄ እና ‹‹መሬት ላራሹ›› የአብዮቱ ቅድመ-ምልክቶች ናቸው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው ለውጦች የለውጥ አማጪ ነን ባዮቹ ቃል-ኪዳኖች ከፖሊሲ ቀረፃው ስለሚቀድም የተጋነነ (ambitious) ነው፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያ በእንደነዚያ ዓይነት ለውጦች ውስጥ መግባትዋ አይመከርም፤ የተቀረፀ ፖሊሲ ይዞ ቃል ኪዳን የሚገባላትን የመምረጫ ዕድል ያስፈልጋታል ብዬ አምናለሁ፡፡

‹‹አብዮት ራሱ የአዝጋሚ-ለውጥ ሒደት ውጤት ነው››

አብዮት - የቅድመ አብዮት ዝግጅት ውጤት ሲሆን ነው እውነተኛ ለውጥ የሚያመጣው ብለው የሚከራከሩ ምሁራንም አሉ፡፡ ይህ አብዮቱን ራሱን አዝጋሚ ለውጥ እንዲሆን ወይም ከአዝጋሚ ለውጥ ጋር እንዲመሳሰል ያደርገዋል፡፡ አብዮት እንዲፈነዳ /እንዲመጣ/ በፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ ውጥረቶች ውስጥ የቆየ ሕዝብ ያስፈልጋል - ያ ሕዝብ በመጨረሻ የታመቀ ብስጭቱን ሲያፈነዳው እና ለውጥ ሲጠይቅ ለውጥ ይሆናል (አብዮት ይፈነዳል)፡፡ ስለዚህ አብዮትን ማንቀዥቀዥ ወይም ማጣደፍ ወደ ማይፈለግ አቅጣጫ ሊያመራ ወይም ደግሞ ከሽፎ ለውጡ ሊመጣ የሚችልበት ዕድሜ በድጋሚ የ‹‹ቢከሽፍስ?›› ፍርሐት እንዲረዝም ያስገድደዋል፡፡ ስለዚህ የቅድመ አብዮት ሥራ ከአብዮት መቅደም እና መብሰል አለበት የሚለው መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡

ዶ/ር አንድሪው ዋላስ ‘Revolution vs Evolution’ ባሠኙዋት አጭር መጣጥፋቸው ለውጥ እንዴት መምጣት አለበት ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ሲሞክሩ አዝጋሚ ለውጥ ለአብዮታዊ ለውጥ ምቹ ጥርጊያ ይፈጥራል ቢሆንም አብዮቶች አንድን ማኅበረሰብ ወደፊት ያራምዳሉ ከሚለው የጋራ ግንዛቤ በተቃራኒ ሁሉም አብዮቶች ተራማጅ ማኅበረሰብ በመፍጠሩ ረገድ ይሳካላቸዋል እንድንል ታሪክ አይፈቅድልንም በማለት በቀስታ (safely) እንድንጫወተው ይመክራሉ፡፡ እንደ ዶክተሩ ድምዳሜ ‹‹…አብዮተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደስልጣን ሲመጡ ቀድሞ የነበረውን ጽንፈኝነት፣ ቁጥጥር፣ ፍረጃ እና በመጨረሻም ሌሎች አብዮቶች ሁሉ የሚከተሉት ዓይነት እንደሆነውና በፈረንሳይ የመጀመሪያው አብዮት እንዳየነው ዓይነት መልሶ ግንባታ ይጀምራሉ፡፡ ይህ አካሔድ ግን [እናውቅልሃለን በሚል] በአብዮቱ ከተወሰነለት በላይ የማኅበረሰቡን ዕድገት አያሳይም፤ ታሪክም የሚነግረን ማኅበረሰብ የሚለወጠው በቴክኖሎጂ ዕድገትና እሱን ተከትሎ በሚያድገው ተግባራትን የመፈፀም አቅም ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ ፖለቲካዊ መዋቅር በማኅበራዊ ስርዓት ውስጥ አንዳንዴ ወደፊት የመራመጃ መንገድ ነው፣ ሆኖም ለማኅበራዊ ለውጥ የሚያስፈልገን ዝግመታዊ የለውጥ ሒደት ነው፡፡››


ለውጥ ለማን እና በማን?

ለአገራችን የሚበጀው ለውጥ በማን እጅ እንዳለ በእርግጠኝነት አይታወቅም - በኢሕአዴግ ወይስ በተቃዋሚዎች፡፡ ኢሕአዴግ ያለበት ችግር የፖሊሲ ነው ወይስ የዴሞክራሲያዊነት? ተቃዋሚዎች ያላቸው ጥንካሬስ? ሁለቱም ወገኖች ይበጅም፣ ይጉዳ የየራሳቸው ጥንካሬ እና ድክመቶች አሉባቸው፡፡ የኢሕአዴግ አባላት በአመራሮቹ የሚሰጣቸውን ከማስፈፀም እና ከማስተጋባት ባሻገር፣ ለሕዝቡ ስለሚቀርቡ እና ሕዝብም ስለሆኑ - ‹‹የለም፣ ይሄ መታረም አለበት›› ብለው ቢታገሉ እና ፓርቲው ፖሊሲውን እንዲያስተካክል፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን እንዲያሰፋ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብኣዊ መብቶችን እንዲያከብር ቢያምጹ ፓርቲው ያለአባላቱ መቆም ስለማይችል ሳይወድ በግዱ ይስተካከላል - ይህም አብዮት/ለውጥ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችም ውስጥ እንደዚያው፡፡ አብዮቶች በገዢው ፓርቲ እና ተቃዋሚዎች ውስጥ ቢጀመሩ በአገሪቱ ላይ እውነተኛ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ፡፡

የክፍል አለቃ፣ የትምህርት ቤት ዳይሬክተር፣ የቢሮ አለቃ፣ የዕድር ሊቀመንበር፣ የማኅበር ሙሴ እና ወዘተ በማኅበረሰባችን እና ተቋሞቻችን የሚመረጡት እንዴት ነው? በቁመና፣ በሹመት፣ በግርማ ሞገስ፣ በመንፈሳዊ ዝንባሌ ወይስ በምን? እነዚህ አመራረጦች የራሳቸው ሚና ቢኖራቸውም ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን አያለመልሙም፤ ስለዚህ እያንዳንዱ አካል መሪውን ሲመርጥ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዕጩው በአባላት ተጠቁሞ፣ ተመርጦ ቢሾም - እታች የተለመደው እላይ ድረስ ይሄዳል፡፡ መሪው ሕዝቡን ሳይሆን፣ ሕዝቡ መሪውን መምረጥ የሚችልበት ስርዓት በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚዘልቀው፣ በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ሹመቶች ላይ ማኅበረሰቡ በጊዜ ሒደት (በአዝጋሚ-ለውጥ) ዴሞክራሲን እንዲለማመድ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ማኅበረሰባዊ ለውጥ በመሆኑ ነፃ የሲቪክ ማኅበረሰብ ሲኖር የሚመጣ ነው፤ ከሌለ በአብዮትም ቢሆን ማምጣት መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡

እናንተስ ምን ትላላችሁ?

(ይቀጥላል)
----
ማስታወሻ፡-

  • ይህ ‹‹ስለለውጥ›› በሚል ዐቢይ ርዕስ በተከታታይ የሚቀርቡ ጽሑፎች አካል ነው፡፡
  • የመጀመሪያውን ክፍል ጽሑፍ እዚህ ማግኘት ይቻላል፡፡

No comments:

Post a Comment