Monday, December 3, 2012

በኢትዮጵያ የቡድን አመራር ተጀምሯል?
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከማንኛውም የሕዝብ ወገን (ከወጣቶች፣ ከሴቶች፣ ከነጋዴዎች…) ጋር ሲወያዩ/ሲያወሩም ሆነ ሲያገኙ ብቻቸውን ሆነው ነበር፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ግን ይህ ዕድል የተሰጣቸው አይመስልም፤ ቀደም ሲል የአገሪቱን ባለሀብቶችን ሲያነጋግሩ ከአራት ሚኒስትሮች ጋር በመሆን ነበር፡፡ የኡጋንዳን የነጻነት 50ኛ ዓመት በዓል ላይ የተገኙት ከበርካታ ባለሥልጣናት ጋር (አቶ በረከት ስምኦንን ጨምሮ) ነበር፡፡ በመጨረሻም ደግሞ ከሰሞኑ የተከሰተው የሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች መሾም ኢትዮጵያ ውስጥ የቡድን አመራር ተጀምሯል? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ተጀምሮስ ከሆነ የቡድን አመራር ለኢትዮጵያ ይበጃት ይሆን?

ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር - ድንገተኛ?

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ዞን ዘጠኝ ላይ ‹ከመለስ በኋላ› በሚል የጠቅላዩን ሞት ተከትሎ በተነበበ ጽሑፋቸው “…ከሁለት ዓመት በፊት ከኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር መካከል አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዴት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነትን ሹመት እንዳገኙ ማስታወስ ይገባናል፡፡ በዚህ ወቅት ፓርቲው  በመተካካት ጥያቄ እና በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጤና መቃወስ ምክንያት ተወጥሮ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ በጣም የሚያስገርመውና የሚያስደምመው የሕወሓት ልሂቃን ሁለት አማራጭ ይዘው ቀረቡ፡፡ አንደኛ በአገሪቱ ላይ ዴሞክራሲ እንዳይቀጭጭ ከተፈለገ እና እኛ የምንወክለው የሕዝብ ቁጥር አነስተኛ ስለሆነ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ቦታ  ከብአዴን እና ኦህዴድ ብንመርጥ የግንባራችንን የኃይል ሚዛን ስለሚያዛባው  በኛ በኩል ተቀባይነት የለውም የሚል ሐሳብ አቀረቡ፡፡ ሁለተኛ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጽ/ቤት ለሦስት ወይንም ለሁለት በመክፈል የስልጣን ክምችቱን (premiership) ብናሰራጨው የተሻለ ይሆናል አሉ፡፡ በመሆኑም የመጀመሪያው ሐሳብ በግንባሩ ተቀባይነት በማግኘቱ ከሁለቱ ብዙኃን ፓርቲ ውጪ የሆነ ሰው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ለመምረጥ በቅተዋል፡፡  ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ሀገሪቱን ለሌሎች ስጋቶች ስለሚያጋልጣት ተቀባይነት አላገኘም…” የሚል አንቀጽ አስፍረው ነበር፡፡


ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ እንደተናገሩት ቀደም ሲል ኢሕአዴግ ተወያይቶበት የነበረው የሦስት ጠቅላይ ሚኒስትር አጀንዳ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ስም መምጣቱ መልኩን ቀይሮ የመጣ መፍትሔ እንጂ ድንገተኛ ክስተት አይደለም፡፡ ምናልባትም ደግሞ በመገናኛ ብዙኃን እንደተደሰኮረልን፣ የመለስን ምትክ በአንድ ሰው ማምጣት ስለማይቻል ለአራት እንዲሆን የተበጀ አዲስ መፍትሔ ነው ብሎ ማለት የዋህነት ይሆናል፡፡ ይልቁንም ለሕወሓት በሩን ለመክፈት ይመስላል፤ ሹመቱን እንመልከተው፡፡

አዲሱ ሹመት

ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ሕወሓት) የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የፋይናንስና የኢኮኖሚ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ፣ አቶ ሙክታር (ኦሕዴድ) የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ዘርፍ አስተባባሪ፣ አቶ ደመቀ መኮንን (ብአዴን) የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ፣ አቶ ቴዎድሮስ አድሃኖም (ሕወሓት) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ሌሎችም ተሹመዋል፡፡ እዚህ ግን የመረጥኳቸው በጣም ስትራቴጂያዊ ሹመቶች ናቸው ያልኳቸውን ብቻ ነው፡፡

በአዲሱ ሹመት መሠረት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ደኢሕዴን ጨምሮ ሁሉም የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች በጠቅላይ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ በመሾማቸው ሁሉም ፓርቲዎች እኩል ውክልና ኖሯቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ኢሕአዴግ ከዚህ ቀደም ያልነበረው የሁሉም ፓርቲዎች ውክልና በአዎንታዊ መልኩ ሲታይ የቡድን አመራር ሊያመጣ የሚችል ቢመስልም፤ የዘርፎቹ አፈጣጠር እና የሌሎችም የሚኒስትሮች ሹመት ቀድሞ ቦታ ያጣ የመሰለውን “የኢሕአዴግ አለቃ” ሕወሓት መልሶ ወደላይ ያፈናጠጠው ሆኖ ተጠናቋል፡፡

በዚህ አሰላለፍ የመረጃ፣ ደኅነንት፣ ኢኮኖሚ እና ጦር ሰራዊቱ ጉዳይ በሕወሓት ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ከሕገ-መንግሥቱ ተጻራሪ በሚመስል መልኩ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነት ለአራት ተሸንሽኖ ሦስት አራተኛው ለምክትሎቹ ተሰጥቷል፡፡ ይህንን ዓይነቱ አሰላለፍ ብዙዎችን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ሥልጣናቸውን የነጠቀ ሹመት ሲሉት፤ በሌላ በኩል የኃይል ሚዛኑ ያረፈው ደኅንነትና መረጃ፣ ኢኮኖሚውንና ጦር ሰራዊቱን የሚቆጣጠረው ሕወሓት እጅ ላይ መሆኑ አሁንም ዞሮ፣ ዞሮ

የቡድን አመራር

የቡድን አመራር የአንድን ግለሰብ የበላይነት ለማስወገድ ወይም በነጠላ የሚሠራ አገራዊ ስህተትን ለመቀነስ የተዘየደ የአመራር መንገድ ነው፡፡ የቡድን አመራር  በቭላድሚር ሌኒን የተዋወቀ USSR ሶሻሊዝምን ለመምራት የቀረበ እና በስታሊን አማካይነት የተስፋፋ የአመራር ስትራቴጂ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቡድን ለመምራት በመወሰን ብቻ ስርዓትን ለመለወጥ እንደማይቻል በሚያሳብቅ ሁኔታ ስታሊን የራሱን ኃያልነት በሚያጠናክር (ማዕከል ባደረገ) ቡድን ጽንሰ ሐሳቡን አክሽፎታል፡፡ ከራሺያ በተሻለ ቻይናን በአንድዬ ‹‹ኮሚኒስት›› ፓርቲ የጠቀለሏት ማኦ ሴቱንግ ኅልፈተ ሕይወት በኋላ የተከተለው የቻይና የቡድን አመራር የእርሳቸውን ፖለቲካ በማስቀጠል እና አንጻራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በተከታታይ በማስመዘገብ ስኬታማ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡

አሁንም ኢትዮጵያን በአንድዬው ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ - ግንባር›› የጠቀለሉት መለስ ኅልፈትን ተከትሎ የመጣው አመራር አንዱን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ለአራት ከፋፍሎ፣ ቀድሞ ምንም አይሠራም ቢባል ማጋነን የማይሆንበትን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታን 75 በመቶ ሥራ ሰጥቶታል፡፡ ይህ በእርግጥ የቡድን አመራር ይባላል? እውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተረፈቻቸው ሩብ ሥልጣን አገሪቷን በራስ መተማመን መምራት ይችላሉ?

አዳዲሶቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሥራቸውን ተከፋፍለው ከመሠማራታቸው በፊት ብዙዎች ዶ/ር ደብረጽዮን ለብቻቸው ኢኮኖሚውን እና ከመረጃ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በበላይነት እንዲመሩ መሾማቸውን በማስታወስ ሥልጣናቸው በተዘዋዋሪ በኃይለማርያም ላይ ሳይቀር የበላይ እንደሚያደርጋቸው ከመናገርም በላይ፣ እንዲያውም ከሁለት ዓመት በኋላ የሚመጣውን ምርጫ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ የሚችሉት እሳቸው መሆናቸውን አመላካች ነው እያሉ መከራከር ጀምረዋል - እግረ መንገዳቸውንም ሹመቱ የቡድን አመራር ሳይሆን አንድ ሰውን ማዕከል እንዳደረገ በመጠቆም፡: ስለዚህ እየመጣ ያለው የቡድን ሳይሆን የሌላ ግለሰብ አመራር ነው ቢባል ይቀላል::

No comments:

Post a Comment