Tuesday, February 12, 2013

ሞትን በሕይወት፣ ጥላቻን በፍቅር የረታ ይቅርታ!በፍቅር ለይኩን

በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ከተማ የሚገኙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ጓደኞቿና የነፃነት ትግሉ አጋሮቿም፡- ‹‹እናዝናለን ኤሚፍቅርሽ፣ ርኅራኄሽ፣ ለሰው ልጆች ነፃነትና መብት መከበር ያለሽ ጽኑ አቋም በልባችን ለዘላለም ይኖራል፡፡ ትግላችን እንዳቺ ያሉ የእውነት፣ የፍትሕ ጠበቃዎችንና ሐቀኞችን በአጥፍ ጨምሮ ይቀጥላል፡፡ ኤሚ እንወድሻለን፣ ሁሌም እናስታውስሻለን! አንቺ የዘረኞችን የመለያየት ግንብ የናድሽ ጀግናችን ነሽ፣ አንቺ በልባችን ውስጥ ለዘላለም ሕያው ነሽሞት በአንቺ ላይ ስልጣን የለውም፣ ሞትን በሕይወት፣ ጥላቻን በፍቅር ያሸነፈሽ የሕዝባችን ታላቅ ሰማዕት ነሽና …!›› በማለት ወደ ትውልድ አገሯ አሜሪካ በእንባና በመሪር ሐዘን ሸኟት፡፡
                                                   
ውቧ፣ ማራኪዋና ከዓለማችን አስር ምርጥ ከተሞች ተርታ የተመዘገበችው የደቡብ አፍሪካዋ የኬፕታውን ከተማ የደቡብ አፍሪካ የታሪክ፣ የቅርስ፣ የባህልና የፖለቲካ ማዕከል ናት፡፡ የድኅረ ምረቃ ትምህርቴን የተከታተልኩባት ኬፕታውን ለአምስት መቶ ዓመታት ያህል አፍሪካውያን ያለፉበትን ውስብስብ የታሪክ ጉዞ የሚያስቃኙ፣ የጥቁር ሕዝቦችን የአይበገሬነትና የነፃነት ተጋድሎ የሚዘክሩ በርካታ ቅርስና ሕያው አሻራ ያላት ታሪካዊ ከተማ ናት፡፡

ኬፕታውን ታላቁ አፍሪካዊ የነፃነት አርበኛ ኔልሰን ማንዴላና የትግል አጋሮቻቸው ለ27 ዓመታት የተጋዙባትን ቀዝቃዛውን የአትላንቲክ ውቅያኖስንና የከተማይቱን ግርማና ውበት የሆነውን የቴብል ማውንቴንን ተንተርሶ የተገነባው የሮቢን ደሴየት ግዞት ቤት/ወኅኒ ቤት የሚገኝባትም ናት፡፡

ይህን ለዘመናት በርካታ አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦች ለሰው ልጆች ነፃነትና ሰብአዊ መብት ሲሉ የተጋዙበትን የሮቢን ደሴየት ግዞት ቤት/ወኅኒ ቤት በየቀኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎችና አጥኚዎች፣ ፖለቲከኞች፣ መሪዎች፣ ታላላቅ የሆኑ የዓለማችን የፊልም እንዱስትሪዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ዝነኞችና ባለ ጠጋዎች ይጎበኙታል፡፡ እናም የደቡብ አፍሪካዋ ‹‹እናት ከተማ›› ኬፕታውን የቱሪስቶችና ውብ የመዝናኛ ከተማም ጭምር ናት፡፡

በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ በትምህርት ክፍላችንና የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሙን ነፃ የትምህርት ዕድልና አጠቃላይ ወጪያችንን የሸፈነልን የሮቢን ደሴየት ሙዚየም፣ በኬፕታውን የሚገኙትን ቤተ መዘክሮችን፣ የደቡብ አፍሪካውያንን የነፃነት ተጋድሎ የሚያንጸባርቁ ታሪካዊ ቦታዎችንና ቅርሶችን መጎብኘት እንድንችል ዕድልን አመቻችቶልን ነበር፡፡ በዚህ ዕድልም ከጎበኘኋቸውና በማስታወሻ ደብተሬ ከመዘገብኳቸው አስደናቂ ስፍራዎች መካከል አንዱ ለዛሬ ጽሑፌ መነሻ ሆኖኛል፡፡

እኔና የክፍል ጓደኞቼ ጉብኝታችን ፕሮግራሞች ውስጥ ካየናቸው የአፓርታይድ አገዛዝን ጭካኔና ክፋት ከሚዘክሩ ታሪካዊ ቦታዎች በኬፕታውን ከተማ የሚገኘው የጉጉሌቱ ታውን ሺፕ አንዱ ነው፡፡ ይህ ታውን ሺፕ/መንደር በአብዛኛው ጥቁሮች የሚኖሩበት ነው፡፡


እነዚህ በአራቱም የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ የጥቁር አፍሪካውያን መንደሮች በደቡብ አፍሪካውያን ሕይወት ዘረኛው የአፓርታይድ ስርዓት የተወው ጠባሳ ገና ፈፅሞ የሻረ እንዳልሆነ ማረጋገጫን የሚሰጡ ናቸው፡፡ እስከአሁንም ድረስ ጥቁር አፍሪካውያኑ የሚኖሩባቸው እነዚህ መንደሮች ድህነትና ጉስቁልና በእጅጉ የሚንጸባረቅባቸው መሆናቸው የሕዝቦቻቸው ኑሮ ይመሰክራል፡፡  

በዚህች በጉጉሌቱ የድኆች መንደር ውስጥ ነዋሪዎቿና ሥራ አጥ ወጣቶቿ ካሉበት አስከፊ ድህነትና ጉስቁልና በመጠኑም ቢሆን ለማውጣትና እገዛ ለማድረግ በአሜሪካውያን ቤተሰቦች የተቋቋመ አንድ ፋውንዴሽን አለ፡፡ በጉብኝታችን ወቅት ስለዚህ ፋውንዴሽን ማብራሪያ የሰጠን አስጎብኚያችን የፋውንዴሽኑን አመሰራረት ታሪክ እንዲህ ሲል አጫወተን፡፡ እኔም በማስታወሻዬ የዘገብኩትንና በዚህች ድህነትና ወንጀል በተንሰራፋበት የጥቁሮች መንደር ‹‹ሞትን በሕይወት፣ ጥላቻን በፍቅር ስለረታው›› አስደናቂ የእርቅ/የይቅርታ ድንቅ ታሪክ ላስነብባችሁ ወደድኹ፡፡

ደቡብ አፍሪካውያን ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል በ1970ዎቹ እና በ1980ዎቹ  መጨረሻ አካባቢ ላይ እጅጉን የተፋፋመበት ወቅት ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ያገኙ ደቡብ አፍሪካውያን ጥቁር ተማሪዎች ትግሉን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ያሻገሩበትን ትልቅ ዕድል ፈጥሮ ነበር፡፡

በዚህ በኬፕታውን ከተማ በዋነኝነት ለክልሶች፣ ለኢንዲያንስ (Colors and Indians) እና ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ተማሪዎች የመማር ዕድል እንዲያገኙ በተቋቋመው የዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲ፣ ከአሜሪካን ካሊፎርኒያ ኮሌጅ በFulbright Scholarship ዕድል አግኝታ የመጣች አንዲት በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ ነጭ አሜሪካዊ ወጣት በዩኒቨርስቲው ያለውን የተማሪዎችን ፀረ አፓርታይድ እንቅስቃሴና ትግል ለማጥናት በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲ ለአስር ወራት ቆይታ ለማድረግ መጥታ ነበር፡፡

ኤሚ የተባለችው ይህች አሜሪካዊት ሴት በዩኒቨርስቲ ቆይታዋ ከጥቁር ተማሪዎች ጋር ለመተዋወቅና አጋርነቷን ለመግለፅ ብዙም ጊዜ አልወሰደባትም ነበር፡፡ እናም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተማሪዎቹ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ዋና የትግል አጋርም ለመሆን በቃች፡፡ የፀረ አፓርታይድ ትግሉንም በሐሳብና በሞራል መደገፉን ተያያዘችው፡፡ በተጨማሪም ከአፍሪካውያን ተማሪዎች ጋር ስለ አፍሪካውያን የነፃነት ትግልን በተመለከተ ሰፊ ውይይትና ጥናት ማድረጓንም ቀጠለች፡፡ ከአፓርታይድ አገዛዝ ወደ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንግስት በሽግግር ወቅት ለነበረችው ደቡብ አፍሪካም የምትችለውንና የአቅሟን ሁሉ አድርጋለች፡፡ 

ኤሚ ከተማሪዎቹ ጋር ያስተሳሰራት የፀረ አፓርታይዱ ትግል ይበልጥ ወንድማዊና እህታዊ የሆነ ቤተሰባዊ ወዳጅነትን አተረፈላት፡፡  እናም ኤሚ አፍሪካውያን ጥቁር ተማሪዎች በሚኖሩባቸው በተከለሉ የጥቁሮች መንደሮች እየተዘዋወረች የዘረኛውን የአፓርታይድ መንግሥትን አስከፊና ዘግናኝ ጭቆና በዓይኗ ለመታዘብና ምስክር ለመሆን ቻለች፡፡

ጭቆና፣ ድህነት፣ መከራ፣ ጉስቁልና፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ የዘረኛው አፓርታይድ መንግሥት ክፉ ተግባርና ግፍ አባሳቸውን በሚያስቆጥራቸው በእነዚህ የድሆች ከተማዎች ውስጥ ያለውን ዘግናኝ ሕይወት ኤሚ በአዕምሮዋና ብዕሯ መከተቡን በሚገባ ተያያዘችው፡፡