Friday, February 1, 2013

የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ቡድን የአዲስ ጉዞ ጅማሬበኤርሚያስ አማረ

ከዓለም የእግር ኳስ ካርታ ላይ ከጠፋን ሰነበትን፤ ከአጠቃላይ ሕዝቧ ከግማሽ የሚልቀው ወጣት በሆነባት ሀገርም ሰላሳ አንድ ዓመት ሩቅ ነው፡፡ አሁን ያለው ትውልድ የሀገሪቱ እግር ኳስ ትልቁ ማሰሪያ በሆነው ብሔራዊ ቡድን ላይ የሚያውቀው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎን ማሳካት እንደማይችል፤ ከሜዳው ውጪ ማሸነፍ ቀርቶበት በአነስተኛ ጎል ተሸንፎ መምጣት እንደሚሳነው እና አባላቱ ከሌሎች ሀገራት አቻዎቻቸው በሥነ ልቦና፣ በአካል ብቃት እና በቴክኒኩ ሰፊ ልዩነት እንዳላቸው ነበር፡፡

በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመራ በሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአዲሱ ትውልድ ጭንቅላት ውስጥ ያሉትን አስተሳሰቦች ሙሉ በሙሉ ባይቀለብስም የመቀልበስ አቅም እንዳለው ግን በትልቁ መድረክ ላይ አሳይቷል፡፡ ይህ ቡድን ለዚህ ደረጃ መብቃቱ በራሱ እንደ አሸናፊነት የወሰዱት ዜጎች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ አሁንም መከራከሪያቸው ብሔራዊ ቡድኑ ለሶስት አስርታ ከዓለምአቀፍ መድረኮች ርቋል ነው፡፡

በዕድል፤ የተሰጣቸውን ዕድል

አንድ የማይካድ ነጥብ ቢኖር ለሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ ያበቁን ጀግኖች ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ታሪኳ ለአቅመ ሜዳ ካደረሰቻቸው ምርጥ ተጫዋቾቿ ጋር ሲነፃፀሩ ቀዳሚውን ቦታ ሊወስዱ እንደማይችሉ ነው፡፡ ይህን መደምደሚያ ለመስጠት ቢያንስ በባለፉት ሰላሳ ዓመታት በሀገሪቱ እግር ኳስ ውስጥ ማለፍ ግድ ይላል፡፡ ዞረን ወደ ዋናው ሕልማችን ወይም ግባችን ስንመለስ ሙሉጌታዎች ያላሳኩትን ሳልሃዲን እና አዳነ መፈፀም ችለዋል፡፡
የእነ አዳነን ታሪክ ከዕድል ጋር የሚያይዙ ዜጎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ዕውነት ነው፤ ለረጅም ዘመናት በአፍሪካ ዋንጫ ጉዞ በማጣሪያዎች ከሰሜን እና ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር እየተደለደልን የቀደመው ትውልድ ኢትዮጵያን ወደ ትልቁ የእግር ኳስ ካርታ ሊመልሳት አልቻለም፡፡ ወደፊት ታሪክ ሲዘክራቸው እንዴት አላለፉም ወይም እንዴት ማሳካት አቃታቸው ከሚለው ይልቅ በግርድፉ አላለፉም ወይም ለአፍሪካ ዋንጫ አልበቁም የሚለው ነጥብ ትልቁን ቦታ ይወስዳል፡፡ አዲሱም የእግር ኳስ ትውልድ ተሳትፎውን ያሳካበት መንገድ ሳይሆን የደረሰበት ቦታ በታሪክ መዝገብ ላይ ደምቆ ይፃፋል፡፡


1990ዎቹ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን እና በኢንጂኒየር ግዛው ተክለማርያም በሚመራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መካከል ጥሩ መቀራረብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በተለይ በእግር ኳሱ የበላይ ፊፋ ፕሬዚዳንታዊ የምረጡኝ ዘመቻ እነ ሌናርት ዮሐንሰን በካፍ በኩል የኢትዮጵያን ድምፅ አጥብቀው የሚፈልጉበት ዘመን ነበር፡፡ ተቀራርቦ የመነጋገሩን ዕድል ያገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች የእነ ሙሉጌታ ትውልድ ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የሚሰናከልበትንዓብይምክንያት ፊት ለፊት ማንሳታቸው አልቀረም፡፡ሁልጊዜ የምንደለደለው ከሰሜን እና ምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር” … የፌዴሬሽኑ ሰዎች ጥያቄ ወይም አቤቱታ ነበር፡፡ በእንዲህ ዓይነት መንገድ የተጀመረው ማግባባት ከዓመታት በኋላ የሰሜን እና ምዕራብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች የሌሉበት ምድብ ውስጥ ያስገባን ጀመር፡፡ የሚፈሩት ሀገሮች ቢኖሩ እንኳን በቅርብ የእግር ኳስ ታሪካቸው ያን ያህል የምንርበተበትላቸው አልነበሩም፡፡ በሶስት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች እነ ግብፅ ከሌሉበት ምድብ ብንደለደልም የማለፍ ሕልማችን ግን ሊሰምር አልቻለም፡፡

ይልቅስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መልካም አጋጣሚ ይዞ የመጣው ካፍ የአፍሪካ ዋንጫን ውድድር መርኃ ግብር ወደ ጎዶሎ ቁጥር ዓመታት ለመቀየር ያደረገው ውሳኔ ነው፡፡ በዚህም በአንድ ዓመት ልዩነት ሁለት ጊዜ አህጉራዊው ዋንጫ ሊካሄድ በቃ፤ 2012 እና 2013፡፡ የጨዋታ ካላንደር መጨናነቅ አፍጥጦ የመጣበት የካይሮው /ቤት በአራት የደርሶ መልስ ግጥሚያዎች አላፊ ቡድኖችን ለመለየት ተነሳ፡፡ ይህን ዕድል በአግባቡ የተጠቀሙበት የሰውነት ቢሻው ልጆች በዕድል ሳይሆን የተሰጣቸውን ዕድል ወደ ውጤት ቀይረው ሕልማችንን አሳኩልን፡፡ የእኛ የተመልካቾች ብቻ ሳይሆን የእነርሱም ሕልም ሰመረ፡፡

ሜዳ ሳይኖር ብሔራዊ ቡድን

በደቡብ
አፍሪካው ውድድር ከወከሉን ሃያ ሶስት ተጫዋቾች በሥርዓት ከተዋቀረ የታዳጊዎች ሥልጠና (ፕሮጀክት) ላይ የተገኙት ከአምስት አይበልጡም፡፡ አብዛኞቹ በራሳቸው እና በትውልድ መንደራቸው ለስፖርቱ ልዩ ፍቅር ባላቸው ዜጎች ጥረት እና ክትትል ለዚህ አኩሪ ታሪክ የበቁ ናቸው፡፡ የእነ ደጉ ዘመን እግር ኳሰኞች በሜዳ የታደሉ አይደሉም፡፡ ለእግር ኳስ መስፋፋት ትልቁን አስተዋፅኦ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ስፖርቱ በቀላሉ ኳስ ማንከባለያ ሜዳ ካገኘ መከናወኑ ነው፡፡ የሰፈር ሜዳዎች በአዳዲስ ሕንፃዎች እና ግንባታዎች እየተመናመኑ በመጡባት አዲስ አበባ የእግር ኳስን .. የሚቆጥሩ ታዳጊዎች ቁጥር እጅግ እየቀነሰ ነው፡፡ ይህም በብሔራዊ ቡድኑ ከመዲናዋ መንደሮች የተገኙትን ተጫዋቾች ውስን አድርጎታል፡፡ በእርግጥ ተፈላጊው ነጥብ የብሔራዊ ቡድኑ ስኬት እንጂ የአካባቢ ውክልና ባይሆንም ይህ አደጋ አዲስ አበባን አዳክሞ ወደ ክልል ከተሞችም ተሻግሯል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ለአኩሪ ታሪክ ካበቁን፤ የእግር ኳስ መሠረተ ልማቶች ቢስፋፉላቸው በሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ የታዩብንን ቀዳዳዎች የማንደፍንበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ የቀደመው ትውልድ በክዋክብቱ የተሻለ ኑሮ ፍለጋኩብለላውእየኮረኮመው ወርቃማ ዘመኑ አልፎበታል፡፡ የዚህኛው ትውልድ እግር ኳስ ደግሞ ያለ መሠረት ልማቶች ከአቅሙ በታች እንዲያመርት ተፈርዶበታል፡፡ ሜዳ እና ተያያዥ ጉዳዮች ሳይሟሉ በስኬት የታጀበ ብሔራዊ ቡድን ማለም አሁንም የዋህነት ነው፡፡

ውድድሩ እና የእኛ ቡድን

ትላልቆቹ ግብፅ እና ካሜሩን በቀሩበት ውድድር እኛ መሳተፋችን ከሰላሳ አንድ ዓመታት ጥማታችን ጋር ተዳምሮ የሚነሳ ሌላው የስኬታችን መለኪያ ሆኗል፡፡ ይህንኑ ክስተት መዘው በአፍሪካ ቡድኖች መካከል ያን ያህል የገዘፈ የብቃት ልዩነት ሜዳ ላይ የለም የሚሉ ድምፆች ይደመጣሉ፡፡ እነደእኔ እንደእኔ በዚህ ዘመን በእግር ኳስ ሜዳ በተፎካካሪ ቡድኖች መካከል የሚታየው ልዩነት የተንቦራቀቀ አይደለም፡፡ እግር ኳስን በውጤት መለኪያ (በአሸነፈ/ተሸነፈ) ብቻ ካየነው በእኛ እና ወደ ቀጣዩ ዙር ባለፉት ስምንት ቡድኖች መካከል ትልቅ ወንዝ አለ፡፡ ቁምነገሩ ሜዳ ላይ በእንቅስቃሴ የታየው ነገር ነው፡፡ ከጎል ቁጥሩ ጀምሮ ኳስ ይዞ እስከመንቀሳቀስ፣ ተጋጣሚ እንደፈለገው ጨዋታውን እንዳይዘውር እስከመቆጣጠር፣ ጠንከር ሲልም በክዋክብት የታጠሩትን ትልልቅ ቡድኖች አጥቅቶ እስከመጫወት በእግር ኳስ ካርታ ሚጢጢ ከሚባሉት ቡድኖች በሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ ታይቷል፡፡ነገር ግን መደምደሚያውን የሚሰጠው ወደ ሩብ ፍፃሜ ማለፍ እና መውደቅ ከሚለው አንፃር እንዳልሆነ ይሰመርበት፡፡ ሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ በቀደሙት ዓመታት ጎላ ብሎ የሚታየው እና የውድድሩን ጣዕም የሚያሳጣው የኃይል አጨዋወት እጅግ መቀነሱን የታዘብንበት ውድድር ነው፡፡

አንድ ለሰባት

የሩብ ፍፃሜው ጉዞ በሰባት የምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች ተወሯል፤ አንድ ፀጉረ ልውጥ የሆነችውና ከደቡብ አቅጣጫ የገባችው አዘጋጇ ሀገር ናት፡፡ እንደ ክፍለ አህጉር ካየነው የዘንድሮው ውድድር ለምዕራብ የአፍሪካ ሃገሮች ትልቅ ስኬት ሆኗል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ የኃይል ሚዛን በሰሜን እና ምዕራብ ሀገራት መካከል ይገኛል፡፡ ይህ የኃይል ሚዛን ፉክክር ከሜዳ ውጪም በእግር ኳሱ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ይንፀባረቃል፡፡ በሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሰሜኖቹ በሶስት ቡድን ተወክለው 1992 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሩብ ፍፃሜ ተወካይ ሳያገኙ ተመልሰዋል፡፡ አሁን ያለው ፈተና አንድ ለሰባት ነው፤ ደቡብ አፍሪካ ከሰባቱ የምዕራብ አፍሪካ ተወካዮች ጋር የምታደርገው ፍጥጫ፡፡ በነፃነት ማግስት በተሳተፈችባቸው ሶስት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ወርቅ፣ ብር እና ነሐስ ያከታተለችው የማንዴላ ሀገር ወቅታዊ ብቃቷ በአዘጋጅነቷ ውስጥ ራሱን ደብቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎም ከውጤት አንፃር ሳይሆን በቀጣይ ለእግር ኳሱ ይዞ ከሚመጣው በጎ ነገሮች አንፃር በደማቁ ሊፃፍ፣ ሊነገር እና ለውይይት ሊቀርብ ይገባዋል፡፡
ማክሰኞ ምሽት በይፋ የተሰናበትነው መድረክ ለወጣቶቻችን እግር ኳስ ተጫዋች መሆን የት ድረስ እንደሚወስድ በተጨባጭ መልስ የሰጠ ነው፡፡ ይህ መልስ ለታዳጊዎቹ ብቻ ሳይሆን ታዳጊዎቹን ኮትኩተው ለሚያሳድጉ ወላጆችም ጭምር ነው፡፡ ሌላው የዓለምአቀፍ መድረክ ልምድ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን የተረዳንበትም ውድድር ሆኖ አልፏል፤ ሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ፡፡ በአርበኝነት ስሜት ሳይሆን ውጤት ያጣንባቸውን ጨዋታዎች በእግር ኳስ ቴክኒክ መነጥር ስንፈትሻቸው የፈራነውን ያህል ከዓለም እግር ኳስ እንዳልራቅን እንረዳለን፡፡ ከፍ ሲል ልጆቻችን ነጋ ጠባ ከምንዘምርላቸው የአውሮፓ እግር ኳስ አድማቂዎች ጋር አብሮ የመቆም አቅም እንዳላቸው የመሰከርንበትም ሆኗል፡፡

የደቡብ አፍሪካው ድግስ ከዛሬ ጀምሮ በትልቁ የሚያጣው የእኛን ትኩረት ብቻ ሳይሆን ለእግር ኳስ ስፖርት ልዩ ፍቅር ያላቸው የኢትዮጵያን ልጆች ቀለም እና ዝማሬ ነው፡፡ ሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ የእግር ኳሳችንን ብቃት፣ አቅም እና ድክመት በደንብ ያየንበት ውድድር ነበር፡፡ ከሙገሳው ጀርባ እነዚህን ሶስት ነጥቦች ወደ መሬት አውርዶ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን በመንደፍ ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ የእግር ኳስ ሥርዓት ኢትዮጵያ አጥብቃ ትሻለች፡፡ ትላንትና ማታ ወደ ሀገራቸው የገቡት ጀግኖቻችን የሚከተሉትን ጥያቄዎች በብሔራዊ ቡድኑ ሥም ይዘው ከደቡብ አፍሪካ ተመልሰዋል፡፡ የመንደር ሜዳዎችን ተንከባከቡልን! ዘመናዊ ስቴዲየም ገንቡልን! የአሰልጣኞቻችንን አቅም አሳድጉልን! መሠረት ያለው የታዳጊዎች ሥልጠና ዘርጉልን! አስተማማኝ የሊግ ውድድር አዋቅሩልን! በዕውቀት የሚሠራ እና የሚያሠራ የእግር ኳስ አመራር አስቀምጡልን! … ፡፡
እንኳን ለምትወዷት ሀገራችሁ አበቃችሁ!

No comments:

Post a Comment