Thursday, May 9, 2013

መብት በአደባባይ
ሰዎች ይሰበሰባሉ፣ አደባባይም ይቀመጣሉ፣ መብታቸውንም ይጠይቃሉ፤ ፖሊሲ ይቀየር ዘንድ ይጮኻሉ፣ ግፍ ይቆም ዘንድ ከፍ ያለ ድምፃቸውን ያሰማሉ፣ አደባባይ እንደወጡ በዛው ውለው ሊያድሩም ይችላሉ፣ አቤቱታ በተለያየ መንገድም ያሰባስባሉ፣ የሚመለከተውን አካልም መፍትሄ እንዲሰጥ ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ተግባር ሰላማዊ በሆነ እና ሕግን በአከበረ መንገድ ሲከናወን ሰላማዊ ሰልፍ ይባላል፡፡ ጥያቄዎች ግን ይከተላሉ፤ ሰዎች ለምን ወደ አደባባይ ይወጣሉ? ለምን በሕግ የተቋቋሙ እንደ ፍርድ ቤት ያሉ ተቋማትን አይጠቀሙም? ለምን በመረጧቸው አካላት አማካኝነት አቤቱታቸውን አያቀርቡም? ለምን የሚመለከተውን አስተዳደር አካል (Administrative Body) በቀጥታ ሂደው አይጠይቁም? ኧረ ለመሆኑ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረገስ ውጤታማ ነውን? የሚሉ ጥያቄዎች ተከትለው ይነሳሉ፡፡
ሰላማዊ ሰልፍ ለምን?

ከ20ኛው ክፍለዘመን ታላላቅ የታሪክ ሊቃውንት መካከል የሚጠቀሰው እንግሊዛዊው የታሪክ ሊቅ Eric Hobsbawm 'Interesting Times: A Twentieth-Century Life' ባለው መፅሃፉ የሰላማዊ ሰለፍን ሀሴት ሲገልፅ፡

Next to sex, the activity combining bodily experience and intense emotion to the highest degree is the participation in a mass demonstration at a time of great public exaltation."


በማለት የሰልፍ አካል መሆን ደስታው የበዛ እንደሆነ፤ ከወሲባዊ እርካታ ጋር አንፃፅሮ ይገልፀዋል፡፡
 
በዚህ የኤሪክ ሆብስባውም ሀሳብ በመንደርደር ሰዎች ለምን ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣሉ/ መውጣት ይፈልጋሉ? የሚሉትን ጉዳይ እንመለክት፡፡


ዴሞክራሲ!
ከሁሉም በፊት ሀሳብን ለማስተጋባት አደባባይ መውጣትንም ሆነ በአደባባይ መሰብሰብን ዋጋ የሚሰጠው ዲሞክራሲ ነው፡፡ ሰዎች ሀሳባቸውን አደባባይ ወጥተው ሲለፁ የስርዓት የኔነትን (Legitimate regime)፤ እንዲሁም የዲሞክራሲውን መጠናከር (Democratic Consolidation) ገላጭ መሆኑ ነው፡፡ ለዛም ነው ዲሞክራሲ መኖር እና ዲሞክራሲን መሻት ዋነኛው ወደ አደባባይ የመውጣት ምክንያት የሚሆነው፡፡
የብዙሃን አመራር - የህዳጣን መብት
ከዲሞክራሲያዊ ስርዓት ዋነኛ ምሰሶዎች መካከል አንዱ የብዙሃኑ አገዛዝ፤ የህዳጣኑ መብት (Majority Rule - Minority Rights) የተሰኝው ነው፡፡ ይሄም ማለት ብዙሃኑ የመረጡት እንደ ህግ ሆኖ ይገዛል፤ ስርዓቱም በነሱ ፍላጎት መሰረት ይሆናል፤ ይሄንም በተወካዮቻቸው አማካኝነት ያካሂዱታል፤ ነገር ግን የብዙሃኑ ሕግ ገዥ ቢሆንም፤ በህዳጣኑ መብት ላይ ጉዳት ማምጣት የለበትም ወይም የብዙሃኑ ስርዓት የህዳጣኑን መሰረታዊ መብቶች መንካት የለበትም የሚል ነው፡፡ በዚህ መሃል ህዳጣኑ በብዙሃኑ ፍላጎት የወጣውን ህግ እያከበሩ፤ ነገር ግን ያልተስማሙበትን ህግ፣ ስርዓት እና ፓሊሲ ይቀየር ዘንድ ድምፃቸውን ሊያሰሙ ይችላሉ፡፡
እናም አደባባይ በመውጣት ሀሳባቸው ሀይል እንዲኖረው በማድረግ ፤ መብታቸው ይሰፋ ዘንድ መናገር የህዳጣኑ ሕጉን የሚገዳደሩበት አንዱ አካሄድ ነው፡፡
እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች አሁን ባለንባት ኢትዮጵያ ወሳኝ ቦታን ይይዛሉ፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ እና አጠቃላይ የሀገሪቱ እንቅስቃሴዎች በአንድ ግዙፍ የፖለቲካ ፓርቲ እጅ ባሉበት በዚህ ወቅት፤ ህዳጣኑ የሚጮሁበት መድረክ በእጅጉ የጠበበ ከመሆኑ ጋር ተዋህዶ እነዚህ አካላት በአደባባይ ድምፃቸውን ያሰሙ ዘንድ አደባባዩን ይፈልጉታል፡፡

Non – Justiciability

አንድ ሰው ተበደልኩ ብሎ ሲያስብ፣ እና የመብት ጥሰት ደረሰብኝ ብሎ ሲያምን ጉዳዩን ለፍርድ ቤት አቅርቦ መፍትሄ ማግኝት እንደሚችል ዲሞክራሲያዊ ስርዓቶች የሚቀበሉት መሰረታዊ የመብት ማስፈፀሚያ መንገድ ነው፡፡ እነዚህም መብቶች የፍርድ ይሁንታን ያገኙ መብቶች (Justiciable Rights) ይባላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መብቶቹ እንደ መብት በሕግ የተከበሩ ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች እነዚህን መብቶች በፍርድ ቤት ጠይቆ ማስፈፀም ላይቻል ይችላል፡፡ ለምሳሌ የኢፌድሪ ሕገ መንግስት በአንቀፅ 43 ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የዘላቂ ልማት መብት ተጠቃሚ መሆን እነዳለባቸው እንዲሆኑ ፤ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ይህ መብት አልተከበረልኝም ብሎ በፍርድ ቤት ማስፈፀም አይቻልም፤ ምክንያቱ የሀገሪቱ ኢኮኖሚን ግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን መንግስት ይህ መብት ይከበር ዘንድ በርትቶ መስራት እንደሚጠበቅበት በሕገ መንግስቱ ተገልጿል፡፡ እናም መንግሰት ይሄን ግዴታውን እየተወጣ አይደለም ብሎ ያሰበ ኢትዮጵያዊ አደባባይ በመውጣት በመንግስት ላይ ጫና ማሳደር ሊፈልግ ይችላል፤ ሕጉም ይፈቅድለታል፡፡ ይሄም አካሄድ ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍን በፍርድ ይሁንታ ላልተሰጣቸው መብቶች (Non-Justiciable Rights) እንደ ማስፈፀሚያነት ሊተቀሙበት ችላሉ እንደማለት ነው፡፡

እነማን ሰላማዊ ሰልፍ ይውጡ? ምንስ ያገኛሉ?
በዋናናት የሰላማዊ ሰልፍ መውጣትን ውጤታማነት የሚያውቀው ሰልፉን የተሳተፈው ሰው ነው፡፡ ለዛም ነው በመግቢያችን የጠቀስነው የኤሪክ ሆብስባውም ጉዳዩን ከወሲባዊ እርካታ ጋር ያመሳሰለው፡፡ ነገር ግን ይህ ሰላማዊ ታቀውሞም/ድጋፍ የሌሎቹን መብት የሚጥስ መሆን የለበትም፡፡ የሌሎቹን መብት መጣስ በሚጀምርበት ወቅት የሞራል የበላይነቱን እና ሕጋዊነቱን ያጣል፤ ስኬቱም ይከሽፋል፡፡ እናም አደባባይ ለድጋፍ/ተቃውሞ የሚወጣ ህዝብ የሰላማዊ ሰልፍ አስኳል የሆነውን ሰላማዊነትን (Peaceful nature) መሰረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል፡፡


እነዚህ ሰልፈኞች ምን ሊያገኙ ነው አደባባይ የወጡት የሚለው ተያያዥ ጥያቄን ስናይ ደግሞ፤ ከላይ የጠቀስነው ስርኣቱ ለኔም ከለላ ይሰጣል ከሚለው ጥቅል ለዲሞክራሲው ከሚሰጥ ይሁንታ (Legitimacy) ጀምሮ ተሳታፊዎች እንዲነቃቁ ማሳቻሉ፤ የሰልፉ አካላት አንድነትን እንዲያዳብሩ እና መፍትሄ በጋራ እንዲሽቱ (Promotion of a sense of solidarity) ፤ እንዲሁም የተነሱበት አላማ ገዝፎ እንዲታይ (To increase the visibility of the cause) እና ምላሽም በተሻለ መንገድ እንዲያገኝ ያስችላል፡፡

የመንግስት ግዴታ

መንግስትስ ሚናው ምን ሊሆን ይገባል? የሚለው ጥያቄም ወሳኝ ነው፡፡ በመጀመሪያ መንግስት የብዙሃኑን ህግ ለማስጠበቅ፤ የህዳጣኑን መብት ደግሞ ለማክበር ነው የተቀመTው ካልን፤ ከብዙሃኑም ሆነ ከህዳጣኑም ወገን ሰላማዊ በሆነ መንገድ  ሰልፍ እወጣለሁ የሚልን አካል ባለመከልከል ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል፡፡ የዘመናዊ ህገ መንግስቶች መሰረት Yሆነው የአሜሪካ ሕገ መንግሰት በመጀመሪያው ማሻሻያው ይሄን ግዴታ በፌደራሉ መንግስት ላይ ይጥላል፡፡ ሰዎች ምንም አይነት ስብሰባ ለማድረግ በሰላማዊ መልኩ መሰብሰባቸውን እና ጉዳታቸውን ለመግለጽ የሚያደርጉትን ማንኛውንም አይነት ሰላማዊ የአቤቱታ መግለጫ መንገድ የሚከለክል ህግ መንግስት ማውጣት አይችልም ብሎ ያፀናዋል፡፡

የዚህ አይነት መንግስት በመብቱ ጣልቃ እንዳይገባ የሚከለክሉ ህጎች መብቱን ተፈጥሮዊ (Inherent) መሆን ግምት ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው፡፡ ዜጎች መብቱን ያገኙት ከህግ ሳይሆን ከተፈጥሯቸው ነው፤ መንግስት ደግሞ በተፈጥሮዊ መብታቸው ላይ ጣልቃ መግባት አይችልም በማለት መንግስት ራሱን ጣልቃ ከመግባት እንዲያቅብ የሚያስገድዱ መብቶች ናቸው፡፡

የኢፌድሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 30 ላይ ይሄን መብት እንደ ተፈጥሮዊ መብት (Human Rights) ባይቆጥረውም፤ በዲሞክራሲያዊ መብትነት (Democratic Rights) ተቀብሎ መብቱን ለዜጎች ይሰጣል፤ በተዘዋዋሪም (A contrario) ይሄን መብት የሚፃረሩ ማንኛውም አይነት ተግባር ሊኖር እንደማይችል ይገልፃል፡፡ በሰላማዊ መንገድ የመሰለፍ እና የመሰብሰብ መብትን በተመለከተ በመንግስት በኩል ያለው ዋነኛ ግዴታ፤ መብቱን የሚፃረር ምንም አይነት ህግ ከማውጣት መቆጠብ እና በተግባርም መብቱን ለዜጎች መተው ነው፡፡

ከዚህ የመታቀብ አሉታዊ ግዴታ (Obligation to refrain) በተጨማሪ፤ በሰላማዊ መንገድ የመሰለፍ እና የመሰብሰብ መብትን ከማስከበር አንፃር ከመንግስት የሚጠበቅ አዎንታዊ ግዴታም (Positive obligation) አለ፤ የዜጎችን ደህንነት እና ፀጥታ ማስከበር፡፡ ይህ ግዴታ በዋነኛነት የሚመነጨው ከመንግስት-ዜጎች ማህበራዊ ውል (Social Contract) ነው፡፡ መንግስት የዜጎች ተወካይ ሁኖ ሲቀመጥ፤ ዋነኛው ስራው የዜጎችን ፀጥታ እና ደህንነት ማስከበር ነው፡፡ እናም ዜጎች በሰላማዊ መንገድ የመሰለፍ እና የመሰብሰብ መብታቸውን ሲጠቀሙ መንግስት ደህንነታቸውን ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ይህ ግዴታ በሁለት መንገድ ጠቃሚ ሆኖ ይገኛል፤ የመጀመሪያው በሰላማዊ መንገድ አደባባይ የወጡትን ዜጎች (ምን አልባትም ህዳጣኑን) ደህንንት ከመጠበቅ አኳያ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሰልፉ ላይ ያልተሳተፉ ዜጎችን (ምን አልባትም ብዙሃኑን) ከምንም አይነት የደህንነት ስጋት ነፃ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም በሰላማዊ መንገድ የመሰለፍ እና የመሰብሰብ መብትን ከማስጠበቅ አኳያ የመንግስት ግዴታዎች በሁለት ትይዩ ይቀመጣሉ፤ መብቱን የሚፃረር ሕግ ባለማውጣት እና የመብቱ ተጠቃሚዎችን ከለላ በመስጠት፡፡

በመግቢያችን የጠቀስነው ኤሪክ ሆብስባውም የሰላማዊ ሰልፍ ፅኑ ባህሪ እንዲህ ገልፆ ይጨርሳል:

‹‹Unlike sex, which is essentially individual, it [Mass Demonstration] is by its nature collective...and it can be prolonged for hours....It implies some physical action--marching, chanting slogans, singing — through which the merger of the individual in the mass, which is the essence of the collective experience, finds expression.”

No comments:

Post a Comment