Friday, July 19, 2013

የስደተኛው ማስታወሻ ከአውሮፓ


(ክፍል ፬)

ውዴ ባለፈው የጥገኝነት ጥያቄሽ ተቀባይነት ሳያገኝ ቢቀር ምን እንደሚደረግ እያጫወተወኩሽ ነበር፤ ይኸው ቀሪው ደግሞ ይሄን ይመስላል፡፡

አሻራና አውሮፓ

አንድ ሰው ጥገኝነት ሲጠይቅ መጀመሪያ የእጅ አሻራውን ለፖሊስ እንዲሰጥ ይገደዳል። ይህ የሚሆነው ወደሌላ አገር ሄዶ ድጋሚ ጥገኝነት እንዳያመለክት ነው። አውሮፓ ውስጥ ካሉት 25 የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት በአንዷ ጥገኝነት የጠየቀ ማንም ሰው በምንም መልኩ ቢሆን ወደሌላ የሕብረቱ አባል አገር ሄዶ ድጋሚ ጥገኝነት መጠየቅ አይችልም። ከጠየቀም መጀመሪያ ወደጠየቀበት አገር በፖሊስ ተይዞ እንዲመለስ ይገደዳል።
ወደሶስተኛ አገር የሚደረግን ስደት ከባድ የሚያደርገው ይህ ሕግ ነው። ሰኔ 8፣ 1982 በአየርላንድ ዋና ከተማ ዳብሊን 12 የአውሮፓ አገሮች መካከል የመጀመሪያው ስምምነት እንደተደረገ ይነገራል። ከዚያ ቡኃላ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉለት እስከ አሁን ድረስ በስራ ላይ ይገኛል። ስለሆነም አንድ ስደተኛ ወደሌላ የአውሮፓ አገር የጣቱን አሻራ ይዞ ከተሰደደ ወደነበረበት ቦታ እንደሚመልሱት ስለሚታወቅ ሌላ አማራጭ ማሰብ ግድ ይለዋል።

በሦስተኛ ደረጃ ያለው አማራጭ አህጉሪቱን ለቆ መሰደድ ይሆናል። እንደአማራጭ የሚቀርበውም ወደሰሜን አሜሪካ ወይም ወደአውስትራሊያ መጓዝ ነው። ነገር ግን ይህን ሶስተኛ ስደት ለማሳካት የሚከፈለው የገንዘብና የራስ መስዋዕትነት እጅግ ብዙ ስለሚሆን ከጥቂቶች በቀር ይህን መንገድ የሚሞክር የለም።

ከዚህ ሁሉ ፈተና ግን መጀመሪያውኑ ከአገር አለመውጣት ይመከራል። ችግሩ ልብ ብሎ የሚሰማ አይኖርም። ወይም አብዛኛው ሲደርስበት ካልሆን ከሰው መማር ይከብደዋል። በትምህርት፣ በስራ፣ በጋብቻ ወይም በሌላ መንገድ ሕጋዊ ሆኖ ለመኖር ካልሆነ በስተቀር ለማንኛውም ሰርቶ ማደር ለሚችል ሰው ተሰዶ ጥገኝነት መጠየቅ አይመከርም። የድህነታችን መሰረቱ ምን እንደሆነ ማወቅ፣ ያለመተማመናችን መንስዔው ማን እንደሆነ መጠየቅ፣ የፍትህ መጓደሉ መንስዔ ከየት እንደመጣ ማየት፣ ነፃነትን ለመፈለግ ቀና ማለትና የበኩልን ማበርከት። ይህን ስታደርጊ አንድም አገርሽ ላይ የመኖርን ጣዕም ታውቂዋለሽ ስለዚህ አትሰደጅም አንድም ተገደሽ ብትሰደጅ እንኳ ጥገኝነት የማግኘት ዕድል አለሽ። እንዲያ ሲሆን በስደትም ሆነሽም ለአገርሽ ነፃነት መታገል አትዘነጊም። ግን እንዲሁ በዘፈቀደ ኖረሽ ኖረሽ ከአገር መሰደድ የሚያስከፍለው ዋጋ እንዲህ በቀላሉ የምትመልሺው እንዳይመስልሽ አሁንም ደግሜ አስጠነቅቅሻለሁ።

የጥገኝነት መብት ካልተሰጠሽ የፖሊስ የውጣልን ደብዳቤ ደርሶሻል ማለት ነው፤ አገሪቱን መልቀቅ አለብሽ ተብሎ ደብዳቤ ካንዴም ሁለት ጊዜ ደርሶሻል እንበል። ወደጎረቤት አገሮች ብትሄጅ ከባድ አይደለም ግን የእጅሽን ጣቶች አሻራ ማሽን ላይ ያስቀምጡትና ከወዴት እንደመጣሽ ያውቁብሻል። ትንሽ አስቀምጠው አንጠልጥለው ወደነበርሺበት ድብርት ይመልሱሻል። ይህ አውሮፓ ምድር ላይ ያሉት የብዙ ወገኖችሽ የዕለት ተዕለት እንግልት ነው።

ሁለት ሦስቴ ጉዳይሽ ውድቅ ተደርጎብሽ ጥገኝነት እንደማያስፈልግሽ ቁርጡን ነግረውሽ ወደ አገርሽ ብትመለሺ ምንም እንደማትሆኚ ገልፀው ደብዳቤ ሰጥተውሻል። ወደ አገርህ እንዳትመለሺ አገርሽ ከአገርነት ተርታ እየወጣች እንደሆነ ታውቂያለሽ። አገርሽን የቀድሞዎቹ ነፃ አውጭዎች መንግስት ሆነው የጨረባ ተስካር አስመስለዋታል። ይህን በተለይ ከአገር ከተሰደድሽ ቡሃላ በደንብ ይገለጥልሻል። እድሜ ለኬዝ ድሮ የማታዪውን ሃቅ ለማየት አብቅቶሻል። ስለዚህ መመለስ ጎመን በልቶ የማያልቅ ዳገት ለመውጣት መነሳት ይሆንብሻል።

የለገመውን ጉልበቴን አጠንክሬ ጨክኜ ዳገቱን ልሞክረው፣ ጨክኜ ወደአገሬ ልመለስ ብትይ እንኳ አገርቤት ተቀምጠው መውጫ ቀዳዳ ያጡ በርካታ ወዳጆችሽ ይታወሱሻል። አሁንም ጨከን ብለሽ ወደመመለሱ ብታተኩሪ የማይገለጠው ይሉኝታ ጠፍንጎ ይይዝሻል። ይህን ሁሉ አመት ምን ስሰራ ቆይቼ መጣሁ እላለሁ? ገብቼ ምን እበላለሁ? ስመጣ በትኜው የመጣሁት የመሰለ ስራ እንደሆነ ተቀምጦ አይጠብቀኝ! ታዲያ እንዴት አድርጌ እመለሳለሁ? እያልሽ የመመለሱህ ወኔሽን ብን ብሎ እስኪጠፋ ትሞግቺዋለሽ።

ስለዚህ እንዲህ መልስ በሌለው ህሊና ላለመሰቃየት አትሰደጂ። ወይም ለስደት መንስዔውን መንግስት ታገይና ተሰደጂ። ለተለያዩ ጉዳዮች የተወሰኑ የአውሮፓ አገሮችን ለማየት እድል አግኝቻለሁ። በነዚህ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወዳጆችንም ለማፍራት ችያለሁ። ያየሁት ነገር በሙሉ ስደትን የሚያበረታታ አይደለም። እጅግ የሚያሳፍር ኑሮን ለመግፋት የተገደዱ ወገኖች መሰደዳቸው ሲቆጫቸው ማየት የተለመደ ክስተት ነው። ግን ከተሰደዱ ወዲያ ወደኋላ መመለስ ስለሚከብድ እንደባከኑ መቅረትን ይመርጣሉ።

ለምሳሌ ዛሬ አገርሽ ላይ እንዴት እንደምትኖሪ አስቢ። ለመሰደድ አስበሽ ያን ሁሉ ገንዘብ አውጥተሽ እዚህ ስትመጪ ምን እንደሚገጥምሽ እየነገርኩሽ ልቀጥል። አንድ ክፍል ለሶስት ወይም ለስድስት ይሰጥና ለቀለብ የሚሆንሽን አስቤዛ ይሰፍሩልሻል ወይም ገንዘብ ያድሉሻል። የቀለብ ገንዘብ ከሰጡሽ ያሻሽህ ለራስሽ እየሰራሽ መብላት እየገዛሽ መጠጣት ሲሆን ቀለብ ከሰፈሩልሽ ደግሞ እየሰሩ የሚሰጡሽን ተሰልፈሽ እየበላሽ መኖር ነው። አብዛኛውን ጊዜ ስራ ስለማታገኚ ከዶርም ዶርም እየዞርሽ በማውራት ሙሉ ጊዜሽን ታባባክኛለሽ። ስደት ለወሬ ይመች የለ እንዲሁ ሁሉም ስለራሱ ሲያወራ ጀንበር ወጥታ ትጠልቃለች።

ወሬ? በስደት ትልቁ ሃብት ነው። በየቦታው በማህበር ተሰባስበው በሚኖሩና  በመንፈስ ታስረው ስራ አትሰሩም ተብለው በየመጠለያው ቁጭ ባሉ አበሾች በትጋት ይወራል። በስደት ውስጥ የወሬ ትንሽ የለውም፤ ጊዜ ለማሳለፍ ብቻ ሳይሆን እየተሰራም ትልቁ ሓብት ወሬ ነው። አፋዊ ወሬ ሲጠገብ ዘመኑ የፌስ ቡክ በመሆኑ ወደ ኮምፒውተራይዝድ ቀደዳ መዞር ነው። ከዚያም በመንፈስ ከታሰረበት ሳይነቃ አፋዊ ወሬውን በኮምፒውተሩ እያዋዛ አመታትን ያለቁምነገር ባክኖ ለመኖር ይተጋል። ስደት ለአብዛኛው አይሳካም ወይም አልጋ በአልጋ አይሆንም ወይም የሚያስከፍለው የራሱ መራር መስዋእትነት አለ። ይህ መስዋእትነት ማንነትሽን አጥፍቶት አዲስ ማንነት አላብሶሽ ሊያልፍ ይችላል፡፡

መስዋእትነቱን ስትከፍዪ ኖረሽም ስደት እንዳሸነፈሽና እንዳስከፋሽ ልትኖሪ ትችያለሽ። ጥገኝነት ሰጪዎቹም ብትያቸው ብትያቸው አንዴ ከጠመሙ የማይቀየሩ ናቸውና እንደባከንሽ ላለመቅረት ወደሌላ አገር ለመሄድ መገደድሽ አይቀርም። ግን ምንም ብታደርጊ፣ ምንም ብትሆኚ ሁልጊዜ የሰውነት ባህሪሽን ተጠቅመሽ ለምን ወደዚህ መጣሁ እያልሽ ዕድልሽን ስታማርሪ ትኖሪያለሽ። ያኔም ከምትረግሚያቸው ሰዎች መካከል አንዱ እኔ እንደምሆን አውቃለሁ።

ሳሚና አበሾች! በአውሮፓ ጫካዎች ውስጥ!

ውዴ ሆይ! አሁንማ ብቸኝነት እየቀለለልኝ መጥቷል። እነሳሚን ከተዋወቅሁ ቀን ጀምሮ ትርፍ ጊዜዬን ከነዚህ ልጆች ጋር ማሳለፍ ጀምሬያለሁ። የበለጠ እየተግባባኋቸው ነው። የሚኖሩበት ሕንፃ ሰፋ ያለ ሳሎን አለው። አልፎ አልፎ ብቅ ከሚሉ የሌሎች አገሮች ስደተኞች በስተቀር ይህ ሳሎን የነዚህ አበሾች መሰብሰቢያ ነው። እየቆየሁ እንደተረዳሁት ከነዚህ አራት ልጆች ውስጥ አንዱ ብቻ ነበር በኢትዮጵያዊነት የሚታወቀው፤ ሌሎቹ በኬዛቸው ምክንያት ኤርትራዊ ናቸው።

ኤርትራዊ የሆኑበት ምክንያት ምን መሰለሽ? ኬዝ የሚባለው ረጅም ልብ ወለድ ታሪክ ነው። ይህን ታሪክ አንዳንዴ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ ሲፃፍ አንዳንዴም ሙሉ በሙሉ ልብ ወለድ ሊሆን ይችላል። አንቺም ወደ አውሮፓ ስትገቢ ኬዝ ያስፈልግሻልና ጥሩ ነው የሚሉትን መርጠው ይሰጡሻል። ኤርትራውያን የመኖሪያ ፈቃድ ስለሚሰጣቸው አንቺም ኤርትራዊ ብትሆኚ በቀላሉ ወረቀቱን ታገኛለሽ ቢሉሽ እሽ እንደምትይ አትጠራጠሪ። ምክንያቱምእሰው አገር መሄድ ያደርጋል ደንቆሮ...’ አይነት ነገር ስለሚገጥምሽ ነው። እንዲህ ልትሆኝ የማትችይው፤ እውነቱን ስታውቂው እና አይ! የማለት አቅሙ ሲኖርሽ ብቻ ነው።

ስጎበኛቸው ከሚሰበሰቡበት ሳሎን ጥግ ተቀምጬ የሚሆነውን እከታተላለሁ።ማቲ” ጮክ ብሎ የሚናገርና ድምፁ ለሬድዮ የሚሆን የካሳንችስ ልጅ ነው። ሳሚ ደግሞ ጠመንጃው እያሉ የሚጠሩት የወጣት ሽማግሌ የሆነ ገጠር ተጀምሮ አዲስ አበባ የተጨረሰ ያለሰፈር ያደገ ሰው ነው። አሌ ደግሞ ምርጥ ወመኔ የአብነት ልጅ ነው። ምንም አልተማርኩም ይላል። እንደፖለቲከኛ በውጭው የሚያራምደው ጥሩነት ይታይበታል። የሶስቱም ኬዛቸው ኤርትራዊነት ነው ግን ሶስቱም ምርጥ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ከሳሎኑ ጥግ ካለች አንድ ሶፋ ላይ ተቀምጦ ቻት ሲያደርግ ይውላል። ከአራቱ ውስጥ ብቸኛው የኬዝ ኢትዮጵያዊ እሱ ነው። በ’ሳ’ የሚጨርስ ስም አውቆ ነው የመረጠው ይሉታል። ለኬዙ እንዲረዳውና በስሙ ኦሮሞ መሆኑ እንዲታወቅለት ነው ስሙን የመረጠው እያሉ እፊቱ ያሙታል።

ማቲ ሳሚን ሲተርበው ከማቲ ድምፅ ማማር በተጨማሪ የሳሚ አለመብሸቅ ያስገርመኝ ነበር። ማቲ ሳሚን ጠመንጃው ይለዋል። ትክክለኛው ስምህ ጠመንጃው ነው! ወይም ደግሞ ዳምጠው! ደሞ አንተን ብሎ ሳሚ! ሳሚ እኮ የአራዳ ልጅ ስም ነው! ትንሽ አታፍርም ሳሚ ብለህ ለራስህ ስም ስታወጣ? ዳምጠው ወይም ጠመንጃው ብትል ወረቀት ይሰጡህ ነበር፡፡ አንተ ግን ዘለህ ሳሚ ስትላቸው ከፊትህ ጋር ስለማይሄድ ሊያምኑህ አልቻሉም።ጠመንጃው የመሰለ ስምህን እና ጎጃም አዘነህን አምባሳደር ጋር ጥለህ መጥተህ ከኛ ጋር ስደት እኩል አደረገህ!’ እያለ ይሞልጨዋል። ሳሚ የብርጭቆ ቂጥ የሚመስል መነፅሩን ከፍ እያደረገ የሚመልሰውን ይመልሳል። የሚመልሰው ስለማያጣ አይበሽቅም። 

ሳሚ ያኔ አውቶቡስ ስንጠብቅ ሲተዋወቀኝሳሚብሎ ነበር የነገረኝ። እናም ሙሉ ስሙን ጠየቅኩት። አሁንም ማቲ እንደተለመደው በሚደላው ድምፁ ጣልቃ ገብቶታዲያ ምን እንዲልህ ፈለግህ? መቼስ እየተዋወቀህ መታወቂያውን ከዋሌቱ አውጥቶ ስሙን አይቶ አይነግርህ? አሁንም መታወቂያውን ካላየ ሳሙኤል ይሁን ሰሚር፣ ሳምሶን ይሁን ሰመረ አያውቀውም። ኬዝ የሚሉት ጣጣ ከደምለው አንስቶ ሳሚ ላይ ጣለው ታዲያ እንዴት ይልመደውእያለ ሲወርድበት ቡና ልጠጣ ብሎ ክፍሉን ጥሎልን ይወጣል።

ያገኘኋቸውን ልጆች ባገኘኋት ትርፍ ጊዜ ስልክ ደውዬ እጠራቸዋለሁ ካልሆነም ወደቤታቸው እሄዳለሁ። ስጠራቸው አብዛኛውን ጊዜ ሳሚ ብቻውን ነበር የሚመጣው። ከሳሚ ጋር በተለይ የቀረበ ግንኙነት ከመሰረትኩ በኋላ ብዙ ጊዜ ወደቤቴ ይመጣ ነበር። ኬዛቸው ኤርትራ የሆኑትን ጨምሮ ባጠቃላይ አምስት ኢትዮጵያውያኖች በዚህ መጠለያ እንደሚኖሩና አንዱ ከክፍሉ እንደማይወጣና እንደማይቀርባቸው ሲነግረኝ አይቼው ባለማወቄ ተገርሜ ነበር፡፤ ለብቻዬ ያሳለፍኳቸውን ሶስት ወራት እያሰብኩእንዴት እናንተ እያላችሁ ለብቻው ይውላል?’ ብዬ ጠየቅኩት።

ፀባዩ እንደዛ ነው፤ ሰላም ብሎን ያልፋል፣ አልፎ አልፎ ስንገናኝ ያወራናል እንጂ ዝምተኛ ነውነበር ያለኝ። ከዚያም አስከትሎወደዚህ መጠለያ ከመጣ ጀምሮ ምንም አይናገርም፣ ቆይ አንድ ቀን ክፍሉ ወስጄ አስተዋውቅሃለሁአለኝ።
ስሙ ማን ይባላል?’
እኛ ... ሊቀ እንለዋለን
ሊቀ የኬዝ ስሙ መሆኑ ነው?’
አይ የተማረ ስለሆነ ነው እንጂ፣ ሊቀ ሊቃውንት ማለት ነው፤ ያለ ማንበብ ሥራ የለውም...ክፍሉ ውስጥ ያሉት መጽሐፍት ብዛት ብታይ ትገረማለህ?
ታዲያ እውነተኛ ስሙ ማን ነው?’
ስትተዋወቀው ራሱ ይነግርሃል!... ማስትሬት ዲግሪ ያለው ልጅ ነው፤ ለዲግሪው ብሎ ስሙን አልቀየረም ሲሉ ሰምቻለሁ
አንተ እዚህ የመጣኸው መቼ ነው?’
ከሁለት ዓመት በፊት ነበር የመጣሁትአለ። እንዴት እንደመጣ ታሪኩን ነገረኝ። ወሬውን ሲጀምር መጀመሪያ አርፎበት ከነበረበት ጊዚያዊ መጠለያ ነበር የጀመረልኝ።

----
የስደተኛው ማስታወሻ ቀደምት ጽሑፎች፡- ክፍል አንድ፣.... ክፍል ሁለት.... ክፍል ሦስት
----
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው ethioswe13@gmail.com ይጻፉላቸው፡፡

No comments:

Post a Comment