Friday, May 31, 2013

የሕግ ማዕቀፍ ለናይል ፖለቲካ ምኑ ነው? (ክፍል ፩)
(ማስገንዘቢያ፤ በዚህ ጽሑፍ ላይ የተገለጹት ቀኖች፣ ወሮች እና ዓመተ ምኅረቶች በሙሉ በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ናቸው፡፡)

እንደ መግቢያ

የናይል ወንዝ ከደቡብ ተነስቶ ወደ ሰሜን 6825 ኪ.ሜ በመጓዝ በዓለማችን ከሚገኙ ረዥም ወንዞች ውሰጥ አንዱ ነው፡፡ 84 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚሆነውን ዓመታዊ የናይል ወንዝ ፍሰት በዋናነት 84 በመቶን የሚያዋጡት ከኢትጵያ ከፍታዎች የሚፈሱት የአባይ፣ የተከዜ እና የባሮ-አኮቦ ወንዞች ሲሆኑ ቀሪውን 16 በመቶ የኢኳቶሪያል ሀይቅ - የነጭ ናይል ድርሻ ነው፡፡ ግብጽ እና ሱዳን ሙሉውን ፍሰት እየተቀበሉ አብዛኛውን ውኃ ለዘመናት የትኛውም ተፋሰስ ሀገር በላይ ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡ ይህንን ለብቻ የመጠቀም መብት ቀድሞ በእንግሊዞች ቅኝ ግዛት ስር ሆነው በተፈጸሙ እና በ1951 በተፈጸመ የተፋሰስ ውኃ ሕጎች ከለላ ሰጥተው ሲያስፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ የናይል ወንዝ 11 ሉአላዊ ሃገሮችን እያቋረጠ ከ300 ሚሊዮን ለሚበልጡ የሰው ልጆች ለጥቅም የሚውል የውኃ ፀጋ አድሏቸዋል፡፡ ነገር ግን የአባይ ውኃ አንጻራዊ የፍሰት መጠን በዓለማችን ላይ ካሉት ሌላ ወንዞች አንጻር፤ ብዙ ሀገሮች የሚጋሩት ግን ደግሞ ዓመታዊ ፍሰቱ ትንሽ መሆኑ አንዳንድ ጸሐፊዎች "ናይል ምርቃት ነው ወይስ እርግማን?" ብለው ሲጠይቁ አብዛኛዎቹ "ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች የግጭት እንጂ የትብብር መገለጫዎች አይደሉም" ብለው ይከራከራሉ፡፡ እንደ አብዛኛዎቹ የዓለም አቀፍ ሀገራት ግንኙነቶች (International relations) የናይል ተፈሰስ አጠቃቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላቸው የሕግ መርሆች ይልቅ በተፋሰሱ ሀገሮች ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ብርታት ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡

የአባይ ተፋሰስ የፖለቲካ ጡዘት በምስራቅ ናይል ተፋሰስ ሀገሮች (ኢትዮጲያ፣ ግብጽ እና ሱዳን) ላይ ያተኩራል፡፡ በናይል ላይ የተፈጸሙትን የሕግ ማዕቀፎች መቃኘት አንዱ የጽሑፉ ዓላማ ሲሆን አዲሱ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተው የውኃ ስምምነት የተፋሰስ ሀገሮቹን ወደ ስምምነት መድረክ ያመጣልን? የሚለውን ጥያቄ በፊት ከተፈጸሙት የሕግ ማዕቀፎች፣ ነባራዊ የሃገራቱ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እና የተፋሰስ ሀገራቱ ከሚያንጸባቁት የመከራከሪያ ነጥብ አንጻር መቃኘት ሌላኛው የጽሑፉ ዓላማ ነው፡፡ የተፋሰሱ ወንዞች ዋና ዋና የሕግ መርሆችን ከናይል ወንዝ አንፃር ወደ መሬት አምጥተን የሚኖራቸው ተግባራዊነት መተንተንም ሌላው የጽሑፉ ዓላማ ነው፡፡

ግብጽ እና ሱዳን የግርጌ ተፋሰስ ሃገሮች (down streams) እንደመሆናቸው ከላይ ያሉ ሃገራት ተፈጥሯዊውን የናይል ውኃ ፍሰት ማስለወጥ ወይም/እና መቀነስ አይችሉም (Absolute territorial integrity) በማለት በተለያዩ መድረኮች የራስጌ ሀገራት (upstream) ውሃውን የግርጌ ሃገራትን በሚጎዳ መልኩ መጠቀም እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በበኩላ፤ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዓቃቢ ሕግ የነበሩት ሀርሞን አሜሪካ እና ሜክሲኮ በሪዎ ግራንድ ወንዝ ላይ በነበራቸው ክርክር ሃገራቸውን በመወገን በሰጡት መከራከሪያ ላይ የፈጠሩትን  ኀልዮት (theory) በመከተል፤ በሉዓላዊ ክልሏ ላይ የሚፈሰውን ውኃ እስከቻለችው ድረስ የመጠቀም መብት (Absolute territorial sovereignty) እንዳላት በተደጋጋሚ ብትገልጽም እስከአሁን ድረስ የታችኞቹን ሃገራት ሐሳብ ውስጥ የሚጥል የኃይል ማመንጫም ሆነ የመስኖ ሥራዎችን ከማቀድ አልፋ ስታስፈጽም አልታየችም፡፡ የዓለማቀፍ ሕጎች፣ ተቀባይነት ያላቸው የዓለም አቀፍ የተፋሰስ የውኃ አጠቃቀሞች፣ የፍ/ቤት ውሳኔዎችም ሆኑ የሕግ ሊቅ ጽሑፎች ለሁለቱም ክርክሮች ተቀባይነት አልሰጡም፡፡

ይልቁንም ሁለቱንም ተፋሰሶች ሊያስማማ የሚችል በዕኩልነት ላይ የተመሠረተ እና የታችኛዎቹን በማይጎዳ መልኩ የውኃውን ተፋሰስ የመጠቀም መርህ (equitable apportionment) ተቀባይነት ተሰጥቶታል፡፡ ዶ/ር ኤሊያስ ኑር Eastern Nile at cross road: preservation and utilization concerns in focus በተሰኘው ጽሑፋቸው ላይ ይህ መርህ የመጣው "...በአንድ ሀገር ውስጥ ባሉ የተለያዩ ከተማዎች (ኒው ጀርሲ እና ኒውዎርክ) መካከል በዴላዌር ወንዝ ላይ በነበራቸው ክርክር የአሜሪካኑ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኛ ሆምስ እ.ኢ.አ በ1923 ላይ ያለ ምንም ሃገራዊ ወገንተኝነት በሰጡት ውሳኔ እንደሆነ እና ከትንሽ ማስተካከያ ጋር የተፋሰስ አጠቃቀም ተደርጎ እንደተወሰደ" ገልጸዋል፡፡

የእንግሊዝ ቀኝ ግዛት አመጣጥ እና በናይል ወንዝ ዙሪያ የፈፀሟቸው የውኃ ስምምነቶች

ከ1853-1857 የነበረው የአሜሪካ የእርስበርስ ጦርነት ወደ ውጭ ሀገራት የሚላኩትን ዕቃዎች ማቆማቸው እንግሊዞች የነበራቸው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ሆኗል፡፡ የከሰረውን የጥጥ ኢንዱስትሪ ለመካስ እና ለእስያ መገናኛ ወሳኝ የሆነውን የስዊዝ ቦይ ለመቆጣጠር ከነበራቸው ፍላጎት በተለይ ግብጽን እና ሌሎች የናይል ተፋሰስ ሀገራትን ለመቆጣጠር መነሻ እንደሆናቸው በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ፕሮፊሰር ያቆብ አረሳኖ Ethiopia and the Nile: Dilemmas of national and regional hydro politics በሚሰኘው የዶክትሬት መመረቂያ ጽሑፋቸው ላይ ይገልጻሉ፡፡ በ1876 በተካሄደው የበርሊኑ ስብሰባ ላይ የምስራቅ አፍሪካ ሃገሮች በእንግሊዝ ስር እንዲተዳደሩ ከመወሰናቸው ባሻገር ኬኒያ፣ ግብጽና ኡጋንዳን ያካተተ የምስራቅ አፍሪካ ጠባቂዎች የተሰኘ ቡድን በ1887 ዓ.ም መሥረተዋል፡፡ በመቀጠል ግብጽንና ሱዳንን በጋራ ለማስተዳደር የሚያስችል ስምምነት በ1891 መሥርተዋል፡፡ እንግሊዞች ግዛታቸው በማስፋፋት በ20ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ ላይ ግብጽን፣ ሱዳንን፣ ኡጋንዳን፣ ኬንያን እና ታንዛንያን በማስተዳደር በናይል ተፋሰስ ላይ ያላቸውን የወሳኝነት ሚና ከፍ አድርገዋል፡፡

በቀኝ ግዛት የተቆጣጠሩዋቸውን ሀገሮችን በመወከል እንግሊዞች በተለየ በግብጽ እና/ወይም ሱዳን ውስጥ የነበራቸውን የናይል ወንዝ ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ ከሌላ ነጻ እና ቅኝ ግዥ ሃገሮች ጋር የተለያዩ የተፋሰስ ውኃ ስምምነቶችን ፈጽመዋል፡፡ፕሮፊሰር ያቆብ በመመረቂያ ጽሑፋቸው ላይ እንግሊዞች በግብጽ ውስጥ ያላቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የገቧቸውን ስምምነቶች በፈጸሙባቸው የጊዜ ተዋረዶች አስረድተዋል፡፡ በ1883 ናይል ወደ ግብጽ እና ሱዳን ያለውን ፍሰት እንዲጠብቁ ከጣልያን ጋር ስምምነት ፈርመዋል፡፡ በ1900 እንግሊዞች ከቤልጄም ንጉሥ ሊዮፓርድ ጋር ቤልጄም በያዘቻቸው የናይል ተፋሰስ ቀኝ ግዛቶች ምንም ዓይነት የግድብ ግንባታ እንደማትፈጽም የሴምሊክ እና ኢሳንጎ ወንዞች ሳይቀንሱ የነጭ ናይልን እንዲቀላቀሉ ተስማምተዋል፡፡ ጣልያኖች በኢትዮጵያ ያላቸውን የቅኝ ግዛት ፍላጎት በመደገፍ እንግሊዞች በድጋሚ የናይል ፍሰትን እንዲጠብቁ በ1917 ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ በሩዋንድ ካጊራ ወንዝ ላይ የተሠራው የኃይል ማመንጫ ውኃ ተመልሶ ናይልን እንደሚቀላቀል በመስማማት እንግሊዞች በድጋሚ ከቤልጄም ጋር በ1926 ላይ ተዋውለዋል፡፡ እንዲሁም በኮለኔል ሀሪንግተን አደራዳሪነት በጊዜው ብቻኛዋ ነጻ ሀገር ከነበረችው እና፣ በ1888 የጣልያንን ጦር በአድዋ ላይ ረትታ በጦርነት ተዳክማ የነበረችው ኢትዮጵያ የናይልን ፍሰት የሚቀንስ ምንም ሥራ ላትሠራ ንጉሠ ነገሥት ሚኒሊክ ቃል ገብተው ፊርማቸውን በ1894 በተፈፀመው ውል ላይ አሳርፈዋል፡፡ በ1921 ግብጽ እና እንግሊዝ ሱዳን መጠቀም የምትችለውን የናይልን ውኃ ብዛት በመጨመር (4 ቢሊዮብ ሜትር ኪዩብ ለሱዳን እና 48 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ለግብጽ) እና በተፈሰሱ ዙሪያ የሚሠሩ ማንኛውም ሥራዎች በቅድሚያ የግብጽን አዎንታ እንደሚፈልጉ በመግለጽ ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ ግብጽ እና በእንግሊዝ ስር የነበረችው ኡጋንዳ በቪክቶሪያ ሀይቅ ላይ የሚሠራውን የኦይን ፎል ግድብ በግብጽ እና በኡጋንዳ ኢንጂነሮች በጋራ እንዲሠራና ግድቡ የግብጽን ጥቅም ማስጠበቅ እንዳለበት ገልጾ በ1940 ስምምነቱ ተፈርሟል፡፡ በድጋሚ የዚህን ግድብ ቁመት ከፍ አድርጎ የሚጠራቀመውን ውኃ በመጨመር ወደ ግብጽ ያለውን ፍሰት ለመጨመር በ1944 ላይ ስምምነት ተፈጽሟል፡፡

ሱዳን ያላትን ድርሻ ለማሳደግ ባነሳችው ጥያቄ መሠረት ነጻነታቸው የተቀናጁት ግብጽ እና ሱዳን በ1951 አጠቃላዩን 84 ቢሊዮን ሚትር ኪዩብ የናይል ውኃ 55.5 ቢሊዮን ሚትር ኪዩብ ለግብጽ 18.5ቱን ለሱዳን ቀሪውን 10 ቢሊዮን በፍሳሽ እና በትነት ለሚባክነው በመተው ከ80 በመቶ በላይ ድርሻ የምታዋጣውን ኢትዮጵያ በመተው ለሁለት ተከፋፍለውታል፡፡ በጊዜው የኢትዩጵያ አስተዳደር የነበረው የንጉሠ ነገሥት ኃይሥላሴ መንግሥት ስምምነቱ ተቋውሞን አሰምቷል፡፡ ግብጽ እና ሱዳን ሙሉውን የናይል ውኃ ከመካፋፈላቸው በተጨማሪ የጋራ ድርጅት (Permanent Joint Technical Commission on the Nile) አቋቋመው በናይል ወንዝ ዙሪያ የሚፈጠሩ ማናቸውም ጉዳዮች ለመከታተል ተስማምተዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ዋተርበሪ አገላለጽ ከዚህ ስምምነት በኋላ ግብጽ እና ሱዳን በናይል ዙሪያ ለሚደረጉ ማናቸውም ውሳኔዎች የጋራ አስተሳሰብ በመያዝ ጋብቻ ፈጽመዋል፡፡ ከ22 ዓመታት እርስ በርስ ጦርነት በኋላ በ2003 ዓ.ም የሱዳን ለሁለት ሉአላዊ ሀገሮች መሰንጠቅ የናይል ወንዝ በደቡብ ሱዳን መልክአ ምድር ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ከመገኘቱ እና ደቡብ ሱዳን የተለየ አቋም ከመያዝዋ አንጻር  ትዳራቸውን ያሻክረዋል የሚል እምነት አለ፡፡

ከ17 ዓመት እርስ በርስ ጦርነት በኋላ የማርኪሲስት ሌኒኒስቱ የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ዋነኛ ረዳቱ በነበረው ዩ.ኤስ.ኤስ.አር ላይ ፀሐይ በመጥለቁ እና አሜሪካ ባደረገችለት ከፍተኛ እርዳታ አሸንፎ የኢትዮጵያን አስተዳደር የተቆጣጠረው የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ከግብጽ ጋር ለዘብ ያለ ስምምነት ፈጽሟል፡፡ በኢትዩጵያ በጊዜው የሽግግር መንግሥት ፕሬዘዳንት መለስ ዜናዊ እና በግብጹ ሁስኒ ሙባረክ መካከል በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ቅርብ ግንኙነት (Nile as a source of mutual interest) ለመመሥረት የታሰበ ማዕቀፍ በ1984 ስማምተዋል፡፡

የግንቦት 2002ቱ የናይል ተፋሰስ የሕግ ስምምነት ማዕቀፍ (Nile River Basin cooperative framework)

የናይል ተፋሰስ ሃገራት በናይል ዙሪያ ቋሚ ድርጅታዊ (Nile River Basin Commission) እና የሕግ ማዕቀፍ (cooperative framework agreement) መመሥረትን ዓላማ አድርገው "ፍትሐዊ በሆነ የተፋሰሱ የውኃ ሀብት አጠቃቀም ቀጣይና ዘላቂነት ያለው ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ልማትን እውን ለማድረግ" በ1991 በመሠረቱት ጊዜያዊ ድርጅት (Nile basin initiative) ከ10 ዓመታት ተደጋጋሚ ውይይቶች በኋላ በዓለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው የተፋሰስ የሕግ መርሆችን አካትቶ በአምስት ዋና ዋና ክፍሎች እና በ44 አንቀጾች ተከፋፍሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉን አሳታፊ የሕግ ማዕቀፍ በ2001 በሩዋንዳ ኪንሻሳ ላይ ለፊርማ ክፍት (Adopt) እንዲሆን በ7 ምርጫ እና በ1 ተቃውሞ አልፏል፡፡ በዚህም መሠረት የሕግ ማዕቀፉ በግንቦት 2002 ላይ በኡጋንዳ ኢንቴቤ ከተማ ለፊርማ ክፍት ተደርጓል፡፡ ኢትዩጵያን ጨምሮ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ታንዛንያ የውኃ ሚኒስሮቻቸውን ልከው በመጀመሪያው ቀን ፊርማቸውን አሳርፈዋል፡፡ የብሩንዲ መንግሥትም በግንቦት 10 ቀን 2004 ዓ.ም ስምምነቱን ፈርሟል፡፡ ይህም ተዋዋይ ወገኖቹን ወደ 6 አድርሶታል፡፡

ዋነኞቹ የአባይ ውኃ ተጠቃሚዎች ግብጽ እና ሱዳን ስምምነቱን ባለፈረም ብቻ ሳይሆን ወኪሎቻቸውን ከ2002ቱ የናይል ተፋሰስ ሚኒስትሮች ስብሰባ እንዲቀሩ በማድረግ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ግብጾች ክርክር ይህ የሕግ ማእቀፍ በፊት ከተዋዋሉዋቸው ሕጎች በተለየ ከ1951 ስምምነት ጋር መጣጣም (confront) እንዳለበት ነው፡፡ የራስጌ ተፋሰስ ሀገሮች በበኩላቸው ተቀባይነት ያለውንና በቬይና ስምምነት አንቀጽ 64 ላይ የተካተተውን መርህ በመከተል ከአዲሱ ስምምነት ጋር የሚቀረኑ የበፊት ስምምነቶች ዋጋ አይኖራቸውም (lex posterior rule-principle of ‘jus cogens’) በማለት አዲሱ ስምምነት የነበሩትን ስምምነቶች በሙሉ እንደሚያፈርሳቸው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በማዕቀፉ አንቀጽ 14(ለ) ላይ የተገለጸው የውኃ ጥበቃ አዋጅ በተሻለ ጠንከር እንዲል የግርጌ ተፋሰስ ሀገሮች ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ በዚህ መሠረት 'not to significantly affect' የሚለው 'not to adversely harm' በሚል እንዲስተካከል ያቀረቡት ጥያቄ በተደጋጋሚ ውይይቶች መፍትሔ ሊያገኝ ስላልቻለ የናይል ቋሚ ድርጅት በተቋቋመ በ6 ወር ውስጥ መፍትሔ እንዲፈልግለት በመስማማት የሕግ ማዕቀፉ ለፊርማ ክፍት ተደርጓል፡፡ ዶ/ር ደረጄ ዘለቀ The Nile basin cooperative framework agreement Negotiation and the adoption of a water security paradigm: Flight in to obscurity or logical cul-de-sac? በሚለው ጽሑፋቸው ላይ እንደታዘቡት መፍትሔው ለወደፊት እንዲቆይ መደረጉ "ለ10 ዓመቱ ውይይት ምክንያታዊ መፍትሔ ለመፈለግ ወይም ቋሚ ድርጅቱ ሲቋቋም እንደገና ወደማያልቀው ድርድር መግቢያ እንደሆነ" ይገልጻሉ፡፡ ይህ በሁለት የተለያዩ አመለካከቶች ላይ የተመሠረት የሕግ ክርክር የራስጌ እና የግርጌ ተፈሰስ ሀገሮች ወደ ጋራ ስምምነት ከማምጣት ይልቅ የዓመታት ግጭቶቻቸው ጎልተው እንዲወጡ ዳርጎታል፡፡

በሕግ ማዕቀፉ አንቀጽ 42 መሠረት ስምምነቱ ተፈፃሚነት የሚኖረው 6 የፈረሙ ሃገሮች በሀገራቸው ውስጥ ባለው የሕግ አካሄድ እንደ ሃገራቸው ሕግ አድርገው ካጸደቁት (ratify) ነው፡፡ ነገር ግን ግብጽ በ2003 የተነሳውን የሕዝብ መነቃቃት ከ30 ዓመት በላይ ሀገሪቷን ሲያተዳድሩ የነበሩትን ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን አስወግዶ በጊዜያዊ የወታደር አመራር ላይ ስለነበረች የግብጽ ከፍተኛ የመንግሥት ወኪሎች "ቋሚ መንግሥት አቋቁመን የሕግ ማዕቀፉን መደራደር እስከምንችል ድረስ የማፅደቅ ሥራ ለጊዜው እንዲያቋዩት" ለኢትዮጵያ እና ለኡጋንዳ መንግሥታት በጠየቁት መሠረት አዎንታቸውን አግኝተው የማፅደቁን ጉዳይ አቆይተውታል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሰዐት የእስላም ወንድማማቾች ፓርቲ በተካሄደው ምርጫ የግብጽ ሕዝቦችን አብላጫ ድምጽ አግኝቶ ሥልጣን ቢቆናጠጥም ከፈረሙት 6 ሀገሮች መካከል ስምምነቱን ያፀደቀ ተፋሰስ ሀገር አልታየም፡፡ የሕግ ማዕቀፉ መጽደቁ ከሚኖረው የውኃ አጠቃቀም እና አካባቢ የመጠበቅ መርህ አስገዳጅነት በተጨማሪ የናይል ተፋሰስ ቋሚ ድርጅት (Nile river basin commission) እንደሚያቋቁም ልብ ይሏል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ያቆብ አርሳኖ አገላለጽ 6 ሃገራት ወደ ማፅደቅ መሄዳቸው ለግብፅ እና ሱዳን ስጋት ይሆንባቸዋል፡፡ እነሱ በሌሉበት ተፈጻሚነት ያለው የሕግ እና የድርጅት ማዕቀፍ በናይል ላይ እንዲመሠረት ስለማይፈልጉ ወደ ማዕቀፉ ሊያመጣቸው እንደሚችል ጥርጣሪያቸውን ገልጸዋል፡፡

ግብጽ እና ሱዳን የነበራቸውን የቀደመ ናይልን የመጠቀም መብት (historic right) ለማስጠበቅ እንደመከራከሪያ የሚጠቅሷቸው በ1921 እና በ1951 የተፈጸሙትን ስምምነቶች አስገዳጅነት አላቸው በሚል ነው፡፡ ነገር ግን የ1921ዱ እና የ1951ዱ የሕግ ስምምቶች በአሁኑ ጊዜ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው የሚነሱ የተለያዩ አግባብነት ያላቸው የሕግ ክርክሮች አሉ፡፡

በመጀመሪያ የ1921ዱ ስምምነት የተፈፀመው እራሳቸውን ችለው በነበሩ ሀገሮች ሳይሆን የስምምነቱ ክፍሎች የሆኑት ግብጽ እና ሱዳን ብቻ ሳይሆኑ የቀሩት የተፋሰስ ሀገሮች በቅኝ ግዛት ስር ነበሩ፡፡ ከቀኝ ግዛት የተላቀቁ ሀገሮች በቀኝ ግዛቶቻቸው የተገቡትን ግዴታዎች መቀጠል አለባቸው ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር ደረጄ ዘለቀ From tenuous legal arguments to secularization and benefit sharing: Hegemonic obstinacy –the question stumbling block against resolution of the Nile water question በሚለው መጣጥፋቸው ወራሽ ሀገሮች በአውራሻቸው የተገቡትን ግዴታዎች የመቀጠል (Universal succession) እና ሙሉ በሙሉ ያለመቀበል መርሆች (Clean state tabula) እንዳሉ ጠቅሰው በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነት ያለው የሕግ መርሕ ታንዛንያ በ1961 ከእንግሊዝ ቀኝ ግዛት ነጻ ስትወጣ በጊዜው በነበሩት ፕሬዝዳንት ስም የተሰየመው ኔየር ዓልዮት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መርሕ መሠረት ነጻ የወጡ ሃገራት ከራሳቸው ሥልጣን የመነጨን እንጂ በአውራሹ አስተዳደር የተገቡ ግዴታዎች ለወራሹ አስተዳደር ጠቃሚ መስለው ካልታዩት በስተቀር አይመለከቱትም የሚል ነው፡፡

ከታንዛናይ በተጨማሪ ኬንያ በ1955 እና ኡጋንዳ ነጻነታቸውን ከእንግሊዝ እንደተቀናጁ የ1921 ስምምነት እንደማይመለከታቸው ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው እና በ1961ኙ የቪይና የዓለም አቀፍ ስምምነት አንቀጽ 59 የተገለጸው የስምምነቱ አባል ሀገራት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ስምምነት ከፈፀሙ የበፊቱ ስምምነት ውድቅ እንደሚሆን ነው፡፡ ስለዚህ የ1951ኙ ስምምነት መፈረም የ1921ዱን ስምምነት ውድቅ ሲያደርገው የ2002ቱ ስምምነት መፈረም የ1951ዱን ስምምነት ውድቅ ያደርገዋል፡፡ እንዲሁም አንድ ስምምነት የስምምነቱ አካል ያልሆኑ ሌላ ሦስተኛ ወገኖችን እንዳማይገዛ (pacta tertiis nec nocent nec prosunt) የታወቀ የሕግ መርሕ ስለሆነ የ1921ዱም ሆነ የ1951ዱ የሁለትዮሽ ስምምነት ከግብጽ እና ከሱዳን ሌላ ተፋሰስ ሀገሮችን እንደማይገዛ ማንም ባለሙያ ያልሆነ ምክንያታዊ ሰው ይረዳዋል፡፡ ግብጽ ከማንም በላይ ተጠቃሚነትዋን አስጠብቃ ለመቀጠል የቅኝ ግዛቷ የሰጠቻተን የጠባቂነት (protectionist) አስተሳሰብ ይዛ ዛሬም የ1951ዱን ስምምነት አስገዳጅነት እንዳለው የመንግሥት አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ ባለሙያዎቿም ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ፡፡ እንደ ግብጽ የሕግ ባለሙያዎች ክርክር በ1951ዱ የተሰጣቸው የግብጽ እና ሱዳን ድርሻ እንደተጠበቀ ሆኖ ለፍሳሽ እና ለትነት የተተወውን 10 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ኢትዮጵያ መጠቀም እንደምትችል ነው፡፡ ግብጾች ከሚያነሱት የሕግ ክርክር በተጨማሪ ወደ ተፋሰስ ሀገሮች የኃይል እርምጃ እንደሚጠቀሙ በማስፈራራት፣ ከመጋረጃ ጀርባ በተፋሰስ ሀገሮች የሚደረጉ ጦርነቶችን በመደገፍ ሀገራቱ እንዳይረጋጉ በማድረግ እና በተለይ የበለጸጉ ሀገሮችና የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በናይል ላይ ለሚሠሩ ሥራዎች እርዳታ እንዳይሰጡ በመደለል የቀደመ የናይል ወንዝን የመጠቀም መብታቸውን ሲያስጠብቁ ኖረዋል፡፡

(ለሰኞ /ግንቦት 26፣ 2005 ይቀጥላል፡፡)

በቀጣዩ ጽሑፍ የተፋሰስ ውኃ የሕግ መርሖች እና አፈፃፀማቸው ይዳሰሳል፡፡
----
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው mikiyaslaw@gmail.com ይጻፉላቸው፡፡

No comments:

Post a Comment