Tuesday, June 25, 2013

በጭቆናና በበደል የተፈተነ የፍትህ እና እኩልነት አባት - ዶ/ር ቢሂምራዎ ራምጂ አምበድከር

ክፍል ፩

በማናዬ በላይ
አምበድከር በኢኮኖሚክስ ለኔ አባቴ ነዉ፡፡ እሱ ማለት ከሰራዉ በላይ ምስጋና የሚገባዉ ለተጨቆኑ የኖረ ጀግና ነዉ፡፡ ምንም እንኳን ከእዉነት በራቀ ምክንያት በሀገሩ አወዛጋቢ ቢሆንም ለኢኮኖሚክስ እድገት ያደረገዉ አስተዋፅኦ ገራሚ እና ሁሌ ሲዘከር የሚኖር ነዉ፡፡
አማርትያ ሴን


I.        ቅድመ ታሪክ
  ከሰዓት ነዉ፤ በጠራራ ፀሀይ ከትምህርት የሚመለሰዉ ህፃን እጅጉን ዉሀ ተጠምቷል፡፡ በአካባቢዉ ወደሚገኙ ቤቶች ሄዶ ዉሀ ለመነ ማንም ዉሀ ለመስጠት ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ ይህ ህፃን በአቅራቢያ ወዳለዉ የዉሀ ታንከር በማምራት ዉሀዉን ለመክፈት ሲታገል ያዩት ነዋሪዎች ለልጅ በማይመጥን ፍልጥ ያሳርፉበታል፡፡ የዉሀ ጥም ጉሮሮዉን እንዳከሰለዉ ይህ ህፃን ጥቂት ኪሎሜትችን ተጉዞ  እቤቱ ይደርሳል፡፡ ለቤተሰቡ ያቀረበዉ የመጀመሪያ ጥያቄ ‹ለምን?› የሚል ነበር፡፡

  በሌላ ጊዜ ይህ ህፃን ከታላቅ ወንድሙ ጋር በመሆን ከሚማሩበት ቦታ ለስራ ተለይቷቸዉ ወደነበረዉ አባታቸዉ ለመሄድ ጋሪ ተሳፍረዉ እየሄዱ ሳለ በመሀል ጋሪዉን የሚዘዉረዉ ካስት ሂንዱ የእነዚህ ህፃናት ማንነት ከተረዳ በኋላ ለህፃናቱ ለነሱም እንግዳ በሆነ እና በማያዉቁት ምክንያት ጋሪዉ እየከነፈ ገፍትሮ መሀል ሜዳ ይጥላቸዋል፡፡ አሁንም ጥያቄያቸዉ ‹ለምን?› ነበር፡፡

  ሌላ ልጨምር ከትምህርት ቤት ወደ ቤቱ እየተመለሰ ያለዉ ህፃን በመሀል ዶፍ ዝናብ ይይዘዋል፡፡ ከዚህ ዝናብ ለመጠለል በመንገዱ ላይ ወደሚታዩት ቤቶች ይጠጋል፡፡ የህፃኑን ማንነት ያዉቁ የነበሩት ሰዎች ገና ከሩቅ እንዳይደርስ ይከለክሉታል፡፡ ክልከላዉን አልፎ ቢጠጋ ምን እንደሚደርስበት በዚች በለጋ እድሜዉ ያየዉ ፈተና አስተምሮታልና ዝናቡን መርጦ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ እቤትም ሲደርስ የሚማርበት ደብተር እና መፃህፍት አንዳይሆን ሆነው ነበር፡፡

  የእንሰሳትን ፀጉር ሳይቀር የሚቆርጥ ፀጉር አስተካካይ የእርስዎን ፀጉር ቢፀየፍ፣ ትምህርት ቤት እንደሌላዉ ተማሪ ሳይሆን ከክፍል ዉጭ ሆነዉ እንዲያዳምጡ አሊያም ከአብዛኛዉ ተማሪ ተነጥለዉ በርቀት ማዳመጥ ብቻ ተፈቅዶሎት ቢማሩ ፤ ማንኛዉም የህዝብ አገልግሎት እርስዎን ቢያገል፣ ዉሀ በርቀት የሚያንቆረቁርልዎ ሌላ ሰዉ ከሌለ የዉሀ መጠጫዉን አሊያም ቧንቧዉን ነክተዉ መጠጣት ቢነፈጉ፣ በተወሰነ መንደር አቅራቢያ ማለፍ ቢከለከሉ፤ የሚያመልኩትን እምነት ምንነት ማወቅ ቢነፈጉ፤ በቤተ እምነቱም አይደለም መሄድ ጥላዎ እንኳን እንዳይደርስ ቢደረጉ ምን ይሰማዎት ይሆን?

  ከላይ የተገለፁትን ከፊሎቹ ሲሆኑ እነዚህን ተግባራት በተፃረረ መልኩ ለሚከዉኑት ተግባር የሚደርስብዎ ቅጣት ማኅበራዊ መገለል አሊያም መደብደብ ብቻ አይደለም ሐይማኖቱ ያዛል በሚሉት ኢ-ሰብአዊ ቅጣት ማሰቃየት ጭምር እንጂ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሹድራ (የዝቅተኛ ካስት አባል ቬዳን (ቬዳ አንዱ የሂንዱ ሀይማኖታዊ መፅሐፍ ነዉ) ከተማረ ያዳመጠበት ጆሮ ዉስጥ የቀለጠ ሊድ በጆሮዉ እንዲንቆረቆር ያዛል፡፡ ይህም ሂንዱ ሐይማኖት ለአማኒዎቹ ስለ ሐይማኖቱ ምንነት እንዳያዉቁ በመከልከል በዓለማችን ብቸኛዉ ሀይማኖት ያደርገዋል፡፡

  በአጠቃላይ ይህ እንግዲህ ከጥቂት አስርት አመታት በፊት በ1950 እና 60ዎቹ ጭምር በሙሉ ህንድ የሚተገበር አፀያፊና አሳፋሪ የማኅበረሰብ ስደራ (የካስት ወይም ቻቱርቫርና) ስርዓት ነዉ፡፡

  Caste/Chaturvarna የሚለዉ ቃል Class ወይም መደብ ከሚለዉ ቃል ጋር የሚቀራረብ ቢመስልም ጠለቅ ብሎ ለተመለከተዉ ልዩነቱ የጎላ ነዉ፡፡ በህንድ ያለዉ ካስት ስርዓት የሚያመለክተዉ በደረጃ የተሰደረ ቀድሞ በዉልደት የሚታወቅ ማኅበራዊ ድልድል ሲሆን አንድዬ በዘር ካገኙት መግባትም ሆነ መዉጣት የማይቻልበት ወደላይ ክብርን እና አገልጋይነትን ወደታች ንቀትና ትዕቢትን የሚያሳዩበት ስርዓት ነዉ፡፡ ካስት ዘላለማዊ ሲሆን ክላስ በአብዛኛዉ ጊዜያዊ ነዉ፡፡ ለምሳሌ ድሀ ከሆኑ ሀብታም በሚሆኑበት ጊዜ የሀብታሙን መደብ ይቀላቀላሉ፡፡ ለዚህ ነዉ መደብ የሚለዉ ቃል ምሉዕ በሆነ ሁኔታ የህንድን ካስት ስለማይገልፀዉ ካስት የሚለዉን ቃል ለመጠቀም የመረጥኩት፡፡

  ዘርዎ ከላይኛዉ ከምሁሩ ከብራሐሚን ክፍል ከሆነ የእርስዎ ጨዋነት (አላዋቂነት) ብዙ አያሳስብዎትም በቃ ሲፈጥርዎ አዋቂ ነዎት ተብሎ ይታሰባል ሌሎችም እርስዎን ሊያገለግሉ ግድ ነዉ፡፡ በተቃራኒዉ የዝቅተኛዉ ሹድራ አባል ከሆኑ የእርስዎ የመጠቀ እዉቀት ለዉጥ አያመጣም የተፈጠሩት በጉልበት ለማገልገል ነዉና፡፡

  • የህንድ ካስት/ቻቱርቨርና ስርዓት


  በህንድ ቫርና አራት ካስት በፒራሚድ መልክ የተሰደረ ሲሆን ብርሀሚን ከፈጠሪዉ (ማኑ) ጭንቅላት የተሰሩ ናቸዉ ተብለዉ የሚታሰብ ሲሆን የተማሩና የሀይማኖት አገልጋዮች ናቸዉ፣ ሸትሪያስ ከእጅ የተሰሩ ወታደር ናቸዉ፤ ቫይሲያስ ከእግር የተሰሩ ነጋዴ፣ ገበሬ፣ እንስሳት የሚያረቡትን ሲጨምር የመጨረሻዉ ሹድራ ከአምላካቸዉ ጥፍር የተሰሩ ናቸዉ ተብሎ ስለሚታመን የጉልበት ሰራተኞች (አገልጋይ እንደማለት) እና የተናቁ ናቸዉ፡፡ ከላይ የተገለፀዉ ግፍ የሚደርሰዉ በዝቅተኛ ላይ በሚገኙት በህንድ በቁጥር አብላጫዉን በሚይዙት በሹድራ ማህበረሰብ ላይ ነዉ፡፡ የካስት ስርዓቱ በዚህ አያበቃም በየካስቱ ዉስጥም የተለያዩ ክፍፍሎች ያሉት ሲሆን ሹድራዉ ከሌላ ሹድራ ለምሳሌ መፀዳጃ ቤት የሚያፀዳዉ ከጫማ ሰሪዉ የተሻልኩኝ ነኝ ብሎ እንዲያስብ የተደረገ ተጨማሪ ድልድል ይመስላል፡፡

  በህንድ የካስት ስርዓት ከሚመስልዎ ካስት ጋር ካልሆነ በቀር ጋብቻ አሊያም ራት አብሮ መመገብ ሲያምሮት ይቀራል፡፡ ይህ የድሮ ታሪክ አይደለም አሁንም ቢሆን በአንዳንድ የምዕራብ ባህል ገብቶናል ከሚሉ ጥቂት ከተሞቻቸዉ አልፎ አልፎ ከሚታዩ ጋብቻዎች ዉጭ አጠቃላይ የህንድ ማህበረሰብ ከሚመስለዉ ካስት ዉጭ ጋብቻ አይመሰርትም፡፡

  ይህ የማህበረሰብ ስደራ የሚሰጠዉ በሀብት፣ ባለዎት የበዛ ችሎታ (የአርስቶትል ማኅበረስብ እሳቤ መሰል Dominanat Appetite መሰረት ያደረገ) ፣ በሂደት በሚከዉኑት ሙያ አሊያም አኗኗር አይደለም ሲወለዱ የሚያገኙት እስኪሞቱ የማይለይ ኢሰብአዊ ድልድል ነዉ፡፡ በዚህ ስርአት ከላይ ያሉት ሶስቱ ከፍተኛ ካስት ሲሆኑ አራተኛዉ ሹድራ የሌሎቹ አገልጋይ ባሪያ ነዉ፡፡ ከዚህ የቫርና ስርአት ዉጭ ያሉት ሂነዱዎች እና አብዛኞቹ ሹድራዎች አይነኬ ተብለዉ ለሰዉ ልጅ የማይመጥን በደል ይደርስባቸዋል፡፡ የዚህ ፁሁፍ ርዕስ የሆነዉ ዶ/ር አምበድከር የሹድራ/አይነኬ አባል ነበር፡፡


  • ሐይማኖት እንደ መሣሪያ

  ይህ ቫርና በሂንዱ የሀይማኖት ስርዓት ድጋፍ ያለዉ ሲሆን ማንኛዉም ለካስቱ ከተመደበለት ስራ ዉጭ መስራት አይችልም ይህን ካደረገ ከሞት በሀኋላ የባሰ ግፍ እንደሚደርስበት በሐይማኖት እየተሰበከ ያድጋል፡፡ ለምን አኔ ሹድራ ሆንኩ ካለ በዛኛዉ ወደዚች አለም ከመምጣቱ አስቀድሞ የፈፀመዉ በደል እንደነበር ይነገረዋል፡፡ እናም በህንድ የሚኖሩ አይነኬዎች ለዘመናት (ከ2000 አመት በላይ) አገልጋይነታቸዉ እያስደሰታቸዉ ሌሎች ከላይ ያሉትን ሶስት ካስት ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡ ትምህርትንም አስመልክቶ ለካስቱ የተመደበዉን ኃላፊነት ለማከናወን ከሚጠቅመዉ ዉጭ መማር እንደማይቻል ይሰበካል፡፡ ለዚህም ነዉ የሹድራ አብዛኞቹ አባላት ያልተማሩ እና ያልነቁ የሆኑት፡፡ ለዚህ ‹ቫርና› ለሚሰኘው ስርዓት የሂንዱ ሐይማኖት ዋንኛ መነሻው ነዉ፡፡

  ይህ አፀያፊ እና ኢ-ሰብአዊ የህንድ ካስት ስርዓት የዱሮ ታሪክ ሆኖ አልቀረም፡፡ በቅርብ እንኳን በኔህሩ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ጥናት የካስት ስርአቱ በህንድ በአብዛኛዉ ገጠራማ አካባቢዎች መልኩን እየቀያየረም ቢሆን በመተግበር ላይ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ለዚህም ዋንኛዉ ምክንያት ስርዓቱ ከሂንዱ ሐይማኖት ጋር የተገናኘ እና በማኅበረሰቡ በሹድራ አባላት ጨምሮ ሰርፆ የገባ ስለሆነ በህግ በቀላሉ ለማስወገድ አለመቻሉ ነዉ፡፡

  የስርዓቱ መነሻ በግልፅ ካለመታወቁ ጋር ተያይዞ የተለያዩ እሳቤዎች የሚንፀባረቁ ሲሆን አንዳንዶች ከሂንዱ ሐይማኖት አመጣጥ ጋር ያያዙታል፡፡ እንደ ዶ/ር ቬሉ አንማሊ ገለፃ የህንድ ካስት ስርአት የመጣዉ በ1500 ኤ.ዲ አቅራቢያ ከሌላ አካባቢ (ከኢትዮጵያ እና ግብፅ) ከመጡ  ፀጉረ ልዉጥዎች ጋር በነበረ የረዥም ጊዜ ተደጋጋሚ ጦርነት በመጨረሻ አሸናፊ የነበሩት ቡድኖች ራሳቸዉን ብርሐማ (አምላክ እንደማለት ነዉ) ብለዉ በመሰየም እና ታላቅ ቦታ ለራሳቸዉ በመስጠት የተቀረዉን ማህበረሰብ ለመግዛት ይመቻቸዉ ዘንድ ሂንዱ የሚባል ሐይማኖታዊ መሳሪያ መስርተዉ አሁን ላለዉ ካስት ስርዓት ምስረታ እና ማኅበራዉ ዉድቀት ዳርገዉታል የሚል ነዉ፡፡ እናም ለዶ/ር ቬሉ ሂንዱይዝም እና  ብርሀሚኒዝም አንድ ናቸዉ የመጀመሪያዉ በሁለተኛዉ የተሰራ ነዉና፡፡ ሌላዉ አፈታሪክ አይነኬዎች ስጋ ተመጋቢ ስለሆኑ እና በወቅቱ የሞተ እንስሳ ስጋ ይበሉ ስለነበር በሽታ ይዘዉ ይመጣሉ ስለዚህ ከዚህ በሽታ ለመራቅ አትክልት ተመጋቢዎቹ አይነኬ አሏቸዉ የሚል ነዉ፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚያደርጉት አብዛኞቹ የከፍተኛ ካስት አባላት አትክልት ተመጋቢ መሆናቸዉን ነዉ፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም የላይኛዉ ካስት አባላት አትክልት ተመጋቢ ካለመሆናቸዉ ባሻገር ብዙ የሹድራ አባላት አትክልት ተመጋቢዎች ናቸዉ፡፡

  ---
  ይቀጥላል፡፡
  --- 
  ጸሐፊውን ለማግኘት bemanishe@gmail.com ላይ ይጻፉላቸው፡፡

  No comments:

  Post a Comment