Sunday, June 23, 2013

‹ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች›፡ የዴሞክራሲ ፀጋ ወይስ ፈተና?


ዘላለም ክብረት

‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን…›› እያለ የሚጀምረው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት፤ ዴሞክራሲን እና ሰላምን የማስፈን ሂደትን በዋናነት ‹ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› በመስጠት፤ እንዲሁም ሉአላዊነትንም ‹ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› በማጎናፀፍ፤ ኢትዮጵያ የምትወከለው በቡድኖች እንደሆኑ ያስረግጣል፡፡ [1]  እዚህ ላይ የሚነሳ ትልቅ ጥያቄ አለ፤ በሕገ መንግስቱ ‹ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች› በመባል የሚጠሩት የተለያዩ ዘውጎች ‹… ዴሞክራሲ እንዲሰፍን…› ማድረግ ይችላሉን? የሚል፡፡

ዴሞክራሲ ምን ይፈልጋል?

ዴሞክራሲ ሂደት እንጅ ግብ አይደለም ብለን ብንነሳም፤ የዴሞክራሲ የመጨረሻ ግቡ ግን የጋራ ሰላም (Mutual security) እና መልካም ሕይወት (Good life) እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ስለዚህም እነዚህን ዋነኛ ዓላማዎች ለማሳካት ዴሞክራሲ በዋናነት ከዜጎች እና ከፖለቲካው ተዋናዮች የሚፈልጋቸው ዋነኛ ግብአቶች አሉት፡፡

የመጀመሪያው እና ዋነኛው የዴሞክራሲ ምሰሶ፤ ሰላማዊ እና ሕግን መሰረት ያደረገ ውድድር ነው፡፡ ይህም ማለት ዴሞክራሲ ዜጎች የሚሻላቸውን አካል የሚመርጡበት ስርዓት ነውና ተወዳዳሪዎች ሰላማዊ ይሆኑ ዘንድ ዴሞክራሲ ትፈልጋለች፤ ነውጠኛ አማራጭን ዜጎች የጋራ ሰላምን በዴሞክራሲ አማካኝነት ለመቀዳጀት የሚያደርጉትን ትግል እጅግ ይጎዳዋልና፡፡ ሌላው ከፖለቲካ ተዋናዮች የሚጠበቀው ቅድም ሁኔታ ደግሞ ሕግ አክባሪነት ነው፡፡ ምንም እንኳን የፖለቲካ ተዋንያን የተሻለ ሕግ እና ስርዓት ለዜጎች ለመስጠት ቢነሱም፤ የተሻለ ሕግ እና ስርዓት ለማምጣት ያለውን ሕጋዊ ስርዓት አክብረው ቢጀምሩ ለዴሞክራሲ መጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፤ አዲስ ስርዓትንም ‹ሀ› ብሎ ከመጀመር ይታደጋል፡፡

እንግዲህ ሰላማዊነት እና ሕጋዊነት ከፖለቲካ ተዋንያን የሚጠበቁ ዴሞክራሲ ቅድመ ሁኔታዎች ከሆኑ፤ ከህዝቡስ ምን ይጠበቃል? የሚለው ጥያቄ ወሳኝነት ይከተላል፡፡ በህዝቡ ዘንድ በዋናነት እንዲዘጋጅ የሚጠበቀው የዴሞክራሲ ስንቅ ሰጥቶ መቀበል እና የጋራ ጥቅምን ማሰስ  (Cross cutting cleavage) ነው፡፡ ይሄም ማለት በሕዝቡ ዘንድ የዴሞክራሲ መዘርጋት ለሁላችንም የጋራ ሰላም ይሰጠናል፤ ስለዚህም ከራሴ/ከቡድኔ ጥቅም ይልቅ ይሄን ለሁላችንም ጥቅም ሊሰጠን የሚችልን አካሄድ መምረጥ አለብኝ ብሎ ማሰብ ነው፡፡ የጋራ ጥቅምን ከማስፋት ይልቅ መግፋትን በሚመርጥ ሕብረተሰብ ውስጥ ዴሞክራሲን መመስረት የማይቻል እንደሆነ ዘርፍ አጥኝዎች የብዙ ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ የሚያሳዩት ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም የዴሞክራሲ ዋነኛ ግብ የጋራ ሰላም (Mutual security) እና መልካም ሕይወት ነውና፡፡

የዘውግ ባህሪያት ለዴሞክራሲ

ዴሞክራሲ የጋራ ሰላም ማምጣትን እንደ ግብ ከያዘ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በዘውግ (Ethnically divided) በተካፋፈሉ ሀገራት ምን መልክ ይኖረዋል? የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሻው የርዕሰ ጉዳያችን አበይት አጀንዳ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ምን እንደሚፈልግ ከላይ ለመግልፅ እንደሞከርነው ሁሉ ዘውግ (Ethnicity) የራሱን ፍላጎቶች እና ዓላማ እንዳለው ማሳየትም ጉዳዩን የበለጠ ግልፅ ያደርገዋል፡፡

Donald Horowitz ‘Ethnic Groups in Conflict’ ባሉት ስራቸው የዘውግ ግንኙነትን ሲገልፁ ‹Ethnic affiliations are Powerful, Permeative, Passionate and Pervasive› በማለት ነው፡፡ ይህም የሚነግረን እውነት፤ ሰዎች የዘውግ ግንኙነታቸው የነሱን ሁሉንም ነገር እንደሚወስን እና በቀን ተቀን ሕይወታቸው ውስጥ ሁነኛ ቦታ ያለው የባህሪ ወሳኝ አድርገው እንደሚወስዱት ነው፡፡


ይህ ዘውግ ጥብቅ ተፅዕኖ ግለሰቡን ከአንድ ሰውነት ወደ ሕብረተሰብነት በመቀየር፤ ራሱን በሕብረተሰቡ ብቻ እንዲገልፅ ይገፋዋል፡፡ ታዲያ ይህ ምን ችግር አለው; ያልን እንደሆን፤ ዴሞክራሲ የሚፈልገው የጋራ ጥቅምን መሻት (Pursuit of mutual benefit) ዘውገኝነት በሚፈልገው የአንድ ቡድን ጥቅም ማስፋት (Ethnic cleavage) ጋር ይጋጭና፤ ስርዓቱን ወደ ፅንፍ (Polarization) በመምራት የዴሞክራሲን አበባ በእንጭጩ ይቀጥፈዋል፡፡ ሁሉም ዘውግ ‹የትኛው ቡድን ነው ስልጣን መያዝ ያለበት; › በሚል የቡድን የሂሳብ ስራ ላይ ተጠምዶ ስለሚውል፤ ዴሞክራሲ የሚፈልገውን ሁሉን አቀፍ የጋራ ስርዓት እና ፍላጎት ይረሳዋል፡፡ እንዲሁም ሰዎች የራሳቸውን ሕይወት ከዘውጉ መኖር ጋር ስለሚያያይዙት፤ ዘውጋቸው ያብብ ዘንድ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይሉም፤ ይባስ ብሎም መበለጥን በመፍራት (Fear of domination) ምክንያት ሌሎች ዘውጎችን እና ግለሰቦችን ለመጨቆን ይነሳሳሉ፤ ይህ ምግባራቸውም የዴሞክራሲ መሰረት የሆነውን የጋራ ጥቅምን መፈለግን በእጅጉ በመናድ ዴሞክራሲን ያፈርሷታል፡፡  

እነዚህን ከዴሞክራሲ ፍላጎት ጋር ‹የሚቃረኑ›፤ የዘውግ ባህሪያት ስንመለከት፤ እውን ብዝሃነት የዴሞክራሲ ስንቅ ነውን; ብለን ለምንጠይቀው ጥያቄ መልሳችን ወደ አሉታዊነት ያደላ ያደርግብናል፡፡ ነገር ግን የዘውጎች መኖር እውነታው ነውና፤ የዴሞክራሲ አስፈላጊነት አጠያያቂነቱ ለዜሮ ቀረበ ነውና፤ የሁለቱን ፍላጎትና ባህርይ ማስታረቅ የመፍትሄው መጀመሪያ ይሆናል፡፡

የዴሞክራሲና የዘውግ እርቅ

የዘውግ ፍላጎቶች ከዴሞክራሲ ፍላጎቶች ጋር በመሰረታዊነት የሚጋጩ መሆናቸው በአንድ በኩል፤ እንዲሁም ግጭቱን ከማስታረቅ ይልቅ የራስን ጥቅም ለማሳደግ በመሻት ሰዎች ለቡድናቸው ድል ለማስገንት በሚያደርጉት ጥረት በሌላ በኩል ዴሞክራሲን በማሃል እንድትዘነጋ ያደርጋታል፡፡ ነገር ግን አንዱን የአንዱ የበላይ ወይም ዘውግን ከዴሞክራሲ ፍላጎት ነጥለን መውሰዳችን የኋላ ኋላ ምንፈልገውን የጋራ ሰላም ያስገኝልናል ማለት አይደለም፤ እንዲያውም ይንድብናል፡፡
ስለዚህ የዘውግ መኖር ልንክደው የማንችለው እውነታ በመሆኑ እንዲሁም ዴሞክራሲ ተወዳጁ የስርዓት አይነት በመሆኑ፤ አንዱ አንዱን ጥሎ ይለፍ ማለቱ አያዋጣንም እና፤ ሁለቱን አስታርቆ መጓዝ ብቸኛው መፍትሄ ይሆንልናል፡፡ እንዴት ይታረቁ? ቀጣዩ ጥያቄ ነው፡፡

የላይፓርት Consociational Democracy

የዘውግ ዴሞክራሲ ግጭትን እንዴት እንፍታ ለሚለው ጥያቄ አብዛኛዎቹ የዘርፉ ምሁራን የዘውጎችን በምርጫ መወከል እንደ ዋነኛ መመዘኛ በመውሰድ፤ መፍትሄዎችን ከምርጫ ውጤት ጋር በማያያዝ ለማቅረብ ይሞክራሉ፡፡ የዴሞክራሲ እና የዘውግ የተፎካካሪነት ባህሪ (Competing nature) ካሳሰባቸው ምሁራን አንዱ፤ Arend Lijphart በዋናነት የሚሸመግሉት የዴሞክራሲና የዘውግ ግጭት መፍትሄው የሚያጠነጥነው ከምርጫ በኋላ በሚመጣ ውጤት ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ይሄም ማለት ከተለያዩ ዘውጉች የተወከሉ ፖለቲከኞች የምርጫን ውጤት በመጋራት (Powersharing) እና በጋራ አስተዳደርም ላይ የጋራ ሕብረት ፈጥረው (Consociation) ማስተዳደር ሲችሉ፤ ዴሞክራሲም ሊያመጣው የሚሻው የገራ ሰላምም ይኖራል፤ ዘውጎችም የሚፈልጉትን ያገኛሉ በማለት ነው፡፡ ላይፓርት ይህ ይሆን ዘንድ ዋነኛ ምሰሶ አድርገው የሚያቀርቧቸው ሰፊ የጥምር መንግስት፤ ነፃ አስተዳደር፤ በሁሉም መስክ ምጥጥን መፍጠር እና የሕዳጣንን ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት መኖርን ነው፡፡ ይህ ሲሟላ ዘውግና ዴሞክራሲ የጋራ ሀገር ይኖራቸዋል በማለት ይደመድማሉ፡፡
ነገር ግን ይህ የላይፓርት መንገድ መፍትሄውን ለልሂቃን አሳልፎ በመስጠቱ ምክንያት ሰፊውን ሕዝብ ያገለለ ነው፤ እንዲሁም ልሂቃን በራሳቸው ችግር ተጠልፈው ሲገኙ የችግሩ መፍትሄ ከመሆን ይልቅ የችግሩ ምንጮች ሊሆኑ ይችላሉ የሚለውም ትችት በተጨማሪ ይቀርባል፡፡

የሆርዊትዝ Vote pooling

የዘውግ ግጭቶችን ከዴሞክራሲ መጠናከር ጋር አስተሳስረው በመተንተን የሚታወቁት Donald Horowitz በበኩላቸው የአረንድ ላይፓርትን የምርጫ ማግስት ትንታኔ ውድቅ በማድረግ፤ የራሳቸውን የምርጫ ዋዜማ መፍትሄ ያቀርባሉ፡፡ ሆርዊትዝ እንደሚሉትም ከምርጫ በኋላ የሚደረግ የስልጣን መጋራት መፍትሄው ዘላቂ ካለመሆኑም ጋር ተያይዞ ስጣንን በኮታ ማደሉ የዴሞክራሲ መጠናከርን በፍፁም አያሳይም ይሉና፤ የራሳቸውን መፍትሄ ሲያቀርቡም ዴሞክራሲ የዘውግና ዴሞክራሲን የሁለትዮሽ መንገድ ወደ አንድ ለማምጣት ዋነኛው ስራ መሰራት ያለበት በምርጫ ዋዜማ ነው ይላሉ፡፡ ሲያብራሩም ዴሞክራሲ የምትፈልገውን የጋራ ጥቅም፤ ልዩነቶቻችን በማርገብ መመልከት ይኖርብናል፤ ለምሳሌ ዘውገ ብዙ የፖለቲካ ፕርቲዎችን መመስረት ዴሞክራሲን የምንታደግበት አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡ የጋራ ፍላጎቶችን የሚያጠናክሩ ተግባራትን ባከናወን ቁጥር የተለያዩ ዘውጎች አባላት ደህንነት ስለሚሰማቸው ድምፃቸውን ዴሞክራሲን ብቻ በማሰብ ሊሰጡ ይችላሉ፤ ሆርዊትዝ ይሄን መራጮችን የማማለል ሂደት ‹Vote Pooling› ይሉታል፡፡ መራጮች ዘውግ ዘለል የሆነው ምርጫቸው በነሱ ሕይወት ላይ የተለየ ተፅዕኖ እንደማይፈጥር እንዲያምኑ (Power incentive) ይሆናል፤ ይሄም ዴሞክራሲ የምትፈልገውን የጋራ ሜዳ (Cross cutting cleavage) ይሰጣታል በማለት፤ ሆርዊትዝ መፍትሄያቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

ሌሎች በበኩላቸው የላይፓርትንና የሆርዊትዝን መንገዶች ደባልቆ መጠቀሙ፤ የእርቁ ዋነኛ መፍትሄ ይሆናል ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›

የኢፌድሪ ሕገ መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኙ ዘውጎችን በጥቅሉ  ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› በሚሉ ልዩነታቸው በቅጡ ባልተገለፀ አጠራር ያስቀምጣቸዋል፡፡ ብዙ ምሁራን የቃላቱን መደራረብ ተመልክተው የስያሜው መነሻ ስታሊናዊ እንደሆነ እና መንግስት የቃላቱን ትርጉም ምንነት ባለመግለፁ ምክንያት የሀሳቡ አረዳድ ዘንድ እክል ፈጥሯል ይላሉ፡፡ ሌሎች በበኩላቸው ጎሳ (Clan) የሚለውን መጠሪያ መጠቀምን መርጠዋል፤ ነገር ግን ይህ ስያሜ የቡድኑን አጠቃላይ የስነልቦና ተሳስቦ (Psychological makeup) አይገልፅም በሚል ትችት ይቀርብበታል፡፡እኔ በዚህ ፅሁፍ ለመጠቀም የመረጥኩት ‹ዘውግ› የሚለው ስያሜ፤ ገላጭም ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡

በጣሊያናዊው ሊቅ Conti Rossini "un museo di popoli" በመባል የተገለፀችው ኢትዮጵያ የብዙ ዘውጎች ስብስብ መሆኗ ግልጽ ቢሆንም፤ ስንት ዘውጎች እንዳሏት ለመናገር ግን አንድ አይነት ቁርጥ ያለ ጥናት አናገኝም፡፡ በተለምዶ ‹ከ80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች ያሏት ሀገር› ሲባል ይሰማል፤ ነገር ግን የመጀመሪያው ‹የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን› በህዳር 2000 ዓ.ም ሲከበር የፌደሬሽን ምክር ቤት ‹የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጥናት ቡድን› በኢትጵያ 69 ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› እናዳሉና በሕገ መንግስቱ ‹እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ቢያንስ አንድ ተወካይ ይኖረዋል…› የሚለውን ድንጋጌ በማክበርም ሁሉም ‹ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ›  በፌደሬሽን ምክር ቤት መቀመጫ እንዳላቸው ገልፆ የነበረ ሲሆን፤ አምስተኛው ‹የብሔር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን› በ2005 ዓ.ም ሲከበር ደግሞ ‹የብሔር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች› ቁጥር 75 ነው በማለት ጭማሪ ማሳየቱን ይሄው ቡድን ገልፆል፡፡ ይሄም የኢትዮጵያን ዘውጎች ቁጥር፤ ‹ይህ ነው› ብለን መደምደምን ከባድ ያደርግብናል፡፡

ለማንኛውም እነዚህ በዙ ዘውጎች እንዲሁም ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የሚሸፍኑት 8 ተፎካካሪ ዘውጎች (Competing ethnic groups)፤ የዘውጋቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚያደርጉት ጥረት ዴሞክራሲ የምትፈልገውን የጋራ ሜዳ ላይፈልጉት ይችላሉ፤ የዚህ የፍላጎት ማጣት ደግሞ ዴሞክራሲ በመፍቀሬ ዘውግ ውስን ሀሳብ እንድትጨፈለቅ ሊያደርጋት ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ብዝሃ ዘውግን ከዴሞክራሲ አስተሳስራ ለመሄድ ጉልህ ርምጃ አድርጋለችን; ብለን ስንጠይቅ ደግሞ መልሳችን ወደ አሉታ ይቀርብብናል፡፡ ዋነኛው ጉዳይም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ማህበረሰብ ዴሞክራሲ እና ዘውግ በተቃራኒው ከቆሙበት፤ ወደመሃል ለማምጣት የትኛውን መንገድ መርጠዋል? የሚለው ሲሆን፤ የሚደርሱበት ውሳኔም ‹ዘውግ የዴሞክራሲ ፈተና ነው› የሚለውን ድምዳሜ ለማርገብ ያስችላል፡፡***[1] የቡድን መብት ከግለሰብ መብት ወይም የግለሰብ መብት ከቡድን መብት ይቀድማል/ይከተላል የሚለው ክርክር ቁርጥ ያለ መልስ ሳያገኝ የቀጠለ ሲሆን በዚህ ፅሁፍም ይሄን ሀሳብ ለማንሳት ፈጽሞ አልተሞከረም፡፡

No comments:

Post a Comment