Thursday, June 13, 2013

FAQ: ኢትዮጵያ - አባይ - ግብፅ
የሰሞኑ የሚዲያ ትኩረት ሁሉ ለወትሮውም እሰጥ አገባ ላልተለየው የኢትዮጵያ-ግብፅ-ሱዳን የአባይ ዙሪያ ግንኙነት ሆኗል፡፡ አትዮጵያ ‹በአባይ የመጠቀም መብት አለኝ› በማለት ለዘመናት ስትጠይቅ የነበረውን መብቷን የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ በመስራት ‹መጠቀም ጀምሬያለሁ› ካለች ጊዜ ጀምሮ እየጋለ የመጣው ይህ ሙግት ሰሞኑን ደግሞ ሞቅ በማለት ‹ጦርነትን›  እንደ አማራጭ እስከ መውሰድ በሚደርስ የከረረ ምት እየጋመ ነው፡፡ በናይል ተፋሰስ ጉዳይ ላይ እጅ በጣም የበዙ ፀሃፍት ከጅኦግራፊ እስከ የውጭ ግንኙነት፤ ከህግ እስከ ውጊያ ጥበብ ድረስ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ትንታኔዎችን ፅፈዋል፡፡ ምናልባትም የናይል ጉዳይ በምርምር ረገድ የነተበ (Rotten) እና ብዙ የተባለበት (Exhausted) ጉዳዮች አንዱ ነው ማለት ሳይቀል አይቀርም፡፡
የሰሞኑን ትኩሳትም ኢትዮጵያዊያን በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ ግንዛቤያቸውን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል በሚል እሳቤ፤ በዚህ ፅሁፍ ብዙ የተተነተነውን የአባይ ተፋሰስ ጉዳይ በሌላ ትንታኔ ከማየት ይልቅ፤ በአባይ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች (Frequently Asked Questions) ላይ ያሉ እውነታዎችን በማስቀመጥ፤ የምርምር ስራዎቹን ለማየት ያልቻሉ ሰዎች በቀላሉ ስለ ጉዳዩ ግንዛቤ እንዲጨብጡ በማሰብ እንዲህ ቀርበዋል፡፡

1.    የአባይ ተፋሰስን (Nile Basin) ከሌሎች ተፋሰሶች ምን ይለያዋል?

ዓለም ላይ ካሉት 264 (አንዳንዶች 272 ናቸው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ 300 ይደርሳሉ ይላሉ) ድንበር ዘለል ተፋሰሶች (International Watercourses) መካከል የአባይ ተፋሰስ  ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት አስገዳጅ በሆነ የሕግ ማዕቀፍ የሌለው ብቸኛው ተፋሰስ መሆኑ፤ ተፋሰሱን በማስዳደር በኩል ትልቅ እክል የፈጠረ ልዩ ጉዳይ ሆኖ የሚነሳ ነው፡፡

2.   በአባይ ተፋሰስ አስተዳደር ላይ ያሉት አማራጮች ምን ምን ናቸው?

የተፋሰሱን ሀገራት በሙሉ ያስማማ አንድም አስገዳጅ ሕግ በሌለበት፤ የተፋሰሱ ሀገራት የራሳቸውን ርምጃ (Unilateral Measures) እንዲወስዱ ያስገደዳቸው መሆኑ እየታየ ነው፤ ለምሳሌ ኢትዮጵያ በተፋሰሱ ላይ እየገነባችው ያለው የኤሌክትሪክ ግድብ፡፡ ነገር ግን የተፋሰሱ ሀገራት በዘላቂነት የወንዙን አጠቃቀም ችግር ይፈቱ ዘንድ ሊወስዷቸው የሚችሉ አማራጮች አሉ፡፡
የመጀመሪያው አማራጭ ተባብሮ መስራት (Coordination) ሲሆን፤ ይህ አማራጭ ተመራጩና በአለማቀፍ ሕግም ታላቅ ድጋፍ ያለው ነው፡፡
ሁለተኛው አማራጭ ተበደልኩ የሚለው አካል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ዘላቂ መፍትሄ ማግኝት ነው፡፡ ይህ አማራጭ በተፋሰሱ ላይ ምንም አይነት ሁሉንም አካላት አስገዳጅ የሆነ ሕግ ባለመኖሩ፤ በውሃ አጠቃቀም ላይ አስገዳጅ የሆነ ዓለማቀፍ ስምምነት ባለመኖሩ (Binding International Treaty) እንዲሁም የዓለማቀፍ ልማዳዊ ሕግ (Customary International Law) በውሃ ጉዳይ ባለመዳበሩ ምክንያት አዋጭነቱ አጠራጣሪ ነው፡፡
ሌላው አማራጭ ግብፅና ሱዳን ከዚህ በፊትም እንደሞከሩት ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉትን የላይኞቹን ተፋሰስ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ማሳመፅ እና ኢትዮጵያን አሁን ያለው አጠቃቀም ሳይነካ አስገዳጅ ውል ውሰጥ መክተት ሲሆን፡፡ ይህ ግን በተግባር ሳይሳካ የቀረ ያረጀ አማራጭ ነው፡፡
የመጨረሻው አማራጭ ‹ጦርነት› ነው፡፡ ነገር ግን በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ ጦርነት ማስነሳት ለህልም የቀረበ አማራጭ ነው፤ ምክንያቱም በጦርነቱ ‹ባለ ድል› አካል አይኖርምና፡፡ ታሪክም ባለፉት 2000 ዓመታት ውስጥ ውሃ የግጭት (Conflict) ምንጭ እንጅ፤ የጦርነት (War) ምክንያት ለአንዴም ሆኖ አለማወቁ የጦርነትን አማራጭነት ሩቅ ያደርገዋል፡፡

3.   ኢትዮጵያ አባይን ሙሉ ለሙሉ ብቻዋን  መጠቀም ትችላለችን?

አትችልም፡፡ ምክንያቱም የ19ኛው ክፍለ ዘመን መርህ የነበረው እና አንድ ሀገር የውስጥ ሀብቷ እንደፈለገች መጠቀም ትችላለች (Absolute Territorial Sovereignty) የሚለው አስተሳሰብ በተግባር ጎጅ እንደሆነ ታውቆ፤ ሀገራት የውስጥ ሀብታቸውን ፍትሃዊ በሆነ አጠቃቀም (Equitable use) እና ለሌሎች ሀገራት የከፋ ጉዳት  በማያስከትል (No Significant Harm) መንገድ መጠቀም አለባቸው፤ በሚሉት ሁለት መሰረታዊ ዓለማቀፍ አስገዳጅ መርሆች በመተካቱ፤ ኢትዮጵያ ‹ወንዙ የራሴ ነውና ብቻየን እጠቀማለሁ› ልትል አትችልም፤ በቅርብ ዓመታት ታሪኳም እንደዛ ብላ አታውቅም፡፡

4.   ግብፅና ሱዳን አባይ የእኛ ነው ለምን ይላሉ?

የታችኞቹ የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ተብለው የሚጠሩት ግብጽና ሱዳን በተደጋጋሚ በህጋዊ ውል ጭምር ‹አባይ የእኛ ሀብት ነው› ይላሉ፡፡ በምን ላይ ተነስተው ነው እንዲህ የሚሉት?፤ ለሚለው ጥያቄ መልሱ በሁለት ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ የመጀመሪያው ‹የተፈጥሮ መብት (Natural/Acquired Right) አለን› የሚል ሲሆን፤ ይሄም ‹ተፈጥሮ የሱዳን እና የግብፅ በርሃዎች አባይን ይጠጡ ዘንድ ለእኛ ለግሳናለች፤ ሌሎች ሀገራት የራሳቸው ሌሎች አማራጮች አሏቸው› የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ‹ታሪካዊ መብት (Historical Right) አለን› የሚል ነው፤ ይህም ማለት በታሪክ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በአባይ ውሃ ላይ እየተጠቀሙ የነበሩት እና ያሉት ግብፅና ሱዳን ናቸው የሚል ነው፡፡

5.   በአሁን ወቅት የግብፅና ሱዳን አቋም ተቀባይነት አለውን?

የለውም፡፡ ምክንያቱም ከላይ ጠቀስናቸው ፍትሃዊ አጠቃቀም (Equitable Use) እና በሌሎች ሀገራት ላይ የከፋ ጉዳት ያለማስከተል መርህ (No Significant Harm Rule) ጋር ስለሚጋጩ፡፡ ‹ግብፅ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ በወንዙ ላይ ተጠቃሚ ነበረች እና አሁንም ያ መብቷ ሳይነካ ይቀጥል› ማለት ‹ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ፍትሃዊ የሆነ አጠቃቀም ድልድል ውስጥ ሳይገቡ አርፈው ይቀመጡ› የማለት ያክል ነው፡፡

6.   በአሁኑ ወቅት ግብፅ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለውን ግድብ አስመልክታ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ብትወስደው ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?

ከላይ እንዳየነው የአባይን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ ውጤታማነቱ እጅግ አጠራጣሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የአባይ ተፋሰስ ገዥ ደንብ ባለመኖሩ፤ በውሃ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ አስገዳጅ ዓለማቀፍ ሕግ ያለመኖሩ እና ዓለማቀፉ ልማዳዊ ሕግ ተጠናክሮ ባለመውጣቱ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ መሰረታዊ የፍትሃዊ አጠቃቀም (Equitable Use) እና ሀገራት ላይ የከፋ ጉዳት ያለማስከተል መርህ (No Significant Harm Rule) ጥሳ ከተገኝች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱ ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡ አንድ ተጨማሪ የሕግ ግዴታም ይነሳል፤ ‹በተፋሰስ ላይ ሊደረጉ የታሰቡና በሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የግንባታ እቅዶችን ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት የማሳወቅ ግዴታ› (Notification of planned measures with possible adverse effects) የተሰኝው፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለውን ግድብ በድብቅ አቅዳ ነው ያስጀመረችው፤ ግብፅና ሱዳን ደግሞ ‹ለእኛ ማሳወቅ ነበረባት› ይላሉ፤ በዚህ ሁኔታ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ቢሄድ ምን ውጤት ይኖረዋል? የሚለው ጥያቄ እስከ አሁን በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ በውል ያልተመለሰ ጥያቄ ነው፡፡ የጥያቄውም ዋነኛ ነጥብ ‹በተፋሰስ ላይ ሊደረጉ የታሰቡና በሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የግንባታ እቅዶችን ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት የማሳወቅ ግዴታ› ወደ ዓለማቀፍ ልማዳዊ ሕግነት (Customary International Law) አድጓል ወይስ አላደገም? የሚል ሲሆን፤ አንዳንዶች ‹አድጓል› ሲሉ ሌሎች ደግሞ ‹አላደገም› ይላሉ፡፡ መርሁ ወደ ዓለማቀፍ ልማዳዊ ሕግነት አድጎ ከሆነ፤ ኢትዮጵያ የግድቡን የግንባታ እቅድ የማሳወቅ ግዴታ ነበረባት/አለባት፤ ያላደገ ከሆነ ደግሞ ግዴታ የለባትም ማለት ነው፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ‹ግድቡ በሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የከፋ ጉዳት (Significant Harm) ያስከትላል ወይስ አያስክልም?› የሚለውም አብሮ መታሰብ አለበት፡፡

7.   ለመሆኑ ኢትዮጵያ በአባይ ጉዳይ ላይ አስገዳጅ ውል ፈርማ ታውቃለችን?

አዎ፤ የ1902ቱ የአንግሎ ኢትዮጵያ ስምምነት፡፡

የስምምነቱ ዋነኛ ዓለማ የድንበር ጉዳይ ቢሆንም፤ በስምምነቱ አንቀፅ 3 ላይ እንዲህ ተደንጓል፡

‹‹ጃንሆይ ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ከጥቁር አባይና ከባህረ ፃና፤ ከሶባት ወንዝ ወደ ነጭ አባይ የሚወርደውን ውሃ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር አስቀድሞ ሳይስማሙ ወንዝ ተዳር እዳር የሚያፍን ስራ እንዳይሰሩ፤ ወይም ወንዝ የሚደፍን ስራ ለማሰራት ለማንም ፈቃድ እንዳይሰጡ በዚህ ውል አድርገዋል፡፡››

ነገር ግን የዚህ ውል የአማርኛ ቅጅ ከእንግሊዘኛው ይለያል፤ በሚል ብዙ እሰጥ አገባ ነበረበት እናም የእንግሊዘኛውን ቅጅ እነሆ፡

‘His Majesty Emperor Menelik, king of kings of Ethiopia, engages himself towards the Government of His Britannic Majesty not to construct or allow to be constructed any works across the Blue Nile, Lake Tana or the Sobat, which would arrest the flow of their waters in to the Nile, except with His Britannic Majesty’s agreement and the Government of the Sudan.’ 

ይህ ውል የቅኝ ግዛት ውል በመሆኑ፤ የቅኝ ግዛት ውሎች ደግሞ ከድንበር ጉዳዮች ውጭ ውድቅ በመሆናቸው ኢትዮጵያን አያስገድዳትም፡፡ ግብፅም ይሄን ውል እንደመከራከሪያ ብዙም አታነሳውም፡፡ ነገር ግን ሱዳን በቀደሙት ዓመታት አልፎ አልፎ ታነሳው የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡

8.   ግብፅና ሱዳን በተደጋጋሚ የሚያነሷቸው የ1929 የቅኝ ግዛት ውል እና የ1959 የሁለትዮሽ ውሎች ለላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ምንድን ናቸው?

ምንም አይደሉም፡፡ ምንም እንኳን ግብፅና ሱዳን የ1929ኙን የሰነድ ልውውጥ (Exchange of Notes) እና የ1959ኙን የሁለትዮሽ ስምምነት በተደጋጋሚ ሲያነሱ የሚታዩ ቢሆኑም፤ የ1929ኙ ሰነድ የቅኝ ግዛት ሰነድ በመሆኑ ውድቅ የሚሆን ሲሆን፤ የ1959ኙ ስምምነት ደግሞ በግብፅና በሱዳን መካከል የተደረገ በመሆኑ የስምምነቱ አባል ያልነበሩትን ሀገራት ሊያስገድድ አይችልም፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ በሁለቱም ውሎች አባል ካለመሆኗ ጋር ተያይዞ የማትገደድ መሆኗን አጥብቃ ስትገልፅ ነበር፣ እየገለፀችም ነው፡፡

9.   ግብፅና ሱዳን ‹የናይል ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ስምምነት› ለምን አልፈረሙም?

‹የናይል ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ስምምነት› እየተባለ የሚጠራዉ በአብዛኛው የናይል ወንዝ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በግንቦት 2002 ዓ.ም የተፈረመው ውል፤ ‹የአባይን ጉዳይ ይፈታዋል› በሚል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ሲሆን፤ በመጨረሻው ሰዓት የተፋሰሱ የላይኛው እና የታችኛው ሀገራት በአንድ አንቀጽ ላይ መስማማት ባለመቻላቸው ምክንያት ለጊዜው አልተሳካም፡፡ ስምምነት ያልተደረሰበት አንቀፅ 14 ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ በላይኛዎቹ የተፋሰስ ሀገራት የቀረበው የስምምነት ረቂቅ ላይ አንቀፁ እንዲህ ይነበባል፡ 

[…] the Nile Basin States recognize the vital importance of water security to each of them. The states also recognize that the cooperation, management and development of waters of the Nile River System will facilitate achievement of water security and other benefits. The Nile Basin States therefore agree, in a spirit of cooperation:
a. To work together to ensure that all states achieve/sustain water security,
b. Not to significantly affect the water security of any other Nile Basin State.

በሌላ በኩል ግብፅና ሱዳን በበኩላቸው እዚሁ አንቀፅ ላይ ንዑስ አንቀፅ (b) እንዲህ ይስተካከል ይላሉ፡

Not to adversely affect the water security and current uses and rights of any other Nile Basin state’.

ዋነኛው ልዩነት ግብፅና ሱዳን ‹አሁን ያለውን የአጠቃቀም ኮታን በማይነካ መልኩ› የሚል ሀረግ ይግባበት ማለታቸው ሲሆን፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉት የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ደግሞ አሁን ያለው ጠቅል (Hegemonic) አጠቃቀም ፍትሃዊ ስላልሆነ፤ አጠቃቀሙ ፍትሃዊ (Equitable) በሆነ መንገድ ይከናወን ዘንድ የቆውን ለግብፅና ሱዳን ብቻ የመጠቀም መብት የሚሰጠው የኮታ ክፍፍል መከለስ አለበት በማለት ይከራከራሉ፡፡ 

የሆነ ሆኖ የአባይ ተፋሰስ አሁንም ብቸኛው በሕግ ማዕቀፍ ስር ያልገባው የዓለማችን ተፋሰስ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

10.  የሰሞኑ ዛቻ አዲስ ነውን?

ሰሞኑን በተለይም ከግብፅ ወገን እየመጣ ያለው ዛቻ እና ማስፈራሪያ ከዚህ ቀደሞቹ ብዙም የተለየ አይደለም ለአብነት ያህልም፡

ሱዳን እና ግብፅ ግጭት ላይ በገቡበት ወቅት ‹ሞገደኛው› የሱዳን ፖለቲከኛ ሀሰን አል ቱራቢ ‹አባይን አቅጣጫውን እናስቀይረዋለን›፤ ብለው በመዛታቸው የዛኔው የግብፅ ፕሬዘደንት የነበሩት ሆስኒ ሙባረክ እንዲህ በማለት ነበር የመለሱት፡

'Those who play with fire in Khartoum [...] will push us to confrontation and to defend our rights and lives.’

የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም አል ቱራቢን ሲያስጠነቅቁ፡

'I am warning Turabi not to play with fire, at the same time, not to play with water.’
በማለት ነበር፡፡

በ1971 ዓ.ም ግብፅ ‹አባይን አስቀይሸ፤ ሲናን አለማለሁ› የሚል እቅድ ይፋ ባደረገችበት ወቅት፤ ለዚህ እቅዷ ምላሽ በወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዘደንት መንግስቱ ሀይለማርያም ‹ግብፅ በእቅዷ የምትገፋበት ከሆነ የአባይ ውሃ እንዲቀንስ እንሰራለን› በማለት በተሰጣት ወቅት፤ የጊዜው የግብፅ አቻቸው አንዋር ሳዳት ሲመልሱ፡

'If Ethiopia takes any action to block our right to the Nile water, there will be no alternative for us but to use force'.

በማለት የጦርነት ነጋሪት ሲጎስሙ ነበር፡፡ ሰሞኑንም ነጋሪት መችው በርክቷል፤ ውጤቱ ምን ይሆን? የሚለውን ‹ጊዜ ጌታ› ብለን እንጠብቅ፡፡

No comments:

Post a Comment