Tuesday, June 25, 2013

ልማት ሲሉ፥ ‘በኢትዮጵያ ልማት አለ‘ ማለታቸው ነው?


በጣልያን የ5 ዓመት ወረራ ወቅት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንገድ ግንባታን አስተናግዳለች፡፡ ከአዲስ አበባ በአራቱም አቅጣጫ ወደየክልሉ የሚፈሱት መንገዶች በጣልያን ነው የተቀየሱት፡፡ ሌላው ቀርቶ አሁን በቅርቡ በዘመነ ኢሕአዴግ የተገነባው እና ‹የሚሌኒየሙ ድልድይ› የተባለው ድልድይ አጠገብ ለብዙ ዐሥርት ዓመታት አገልግሎት የሰጠው ድልድይ የተገነባው በጣልያን ወረራ ጊዜ፣ በኢትዮጵያውያን ጉልበት እና በጣልያኖች ጥበብ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ኢትዮጵያውያን አባይን የሚሻገሩት ዐፄ ፋሲለደስ ባስገነቡት ድልድይ፣ አሊያም በዋና/በጀልባ ነበር፡፡

ጣልያን እነዚያን መንገዶች ለምን ይገነባ እንደነበረ ለመረዳት ቢያንስ በዚህች አንቀጽ ስለቅኝ ግዛት ማውራት ያስፈልጋል፡፡ የአውሮጳ ቅኝ ገዢዎች አፍሪቃን መቀራመት ከመጀመራቸው በፊት አውሮጳቸውን በኢንዱስትሪ አጥለቅልቀዋት ነበር፡፡ ኢንዱስትሪዎቻቸውን ለመገንባት የሚፈጀውን የሰው ኃይል ለመሙላት አፍሪካ መጥተው ባሪያዎችን በወሰዱበት ወቅት ያዩትን ጥሬ ሀብት ለኢንዱስትሪዎቻቸው ለማቅረብ የሚያስችላቸውን ዘላቂ ስርዓት ለመዘርጋት ነው ወደአፍሪቃ ተመልሰው የመጡት፡፡ ስለዚህ በቅኝ ግዛት የሚይዟቸውን አገራት በመሠረታዊ ልማት ማሳደግ እና ሁሉንም ነገር በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል ያለው ሚና ትልቅ ስለነበር ያለ የሌለ ኃይላቸውን በሙሉ እንደደረሱ በዚያ ላይ ያውሉ ነበር፤ ሌላው ቀርቶ በጦርነት ወቅት እንኳን ከፊት እየተዋጉ ከኋላ ይገነቡ ነበር፡፡ ምክንያቱም የመሠረተ ልማት ግንባታ ለዜጎች የሚሰጠው ፋይዳ አሌ የማይባል ቢሆንም ገዢው የሚፈልገውን እንዲፈፅምም ያስችለዋል፡፡

ይህንን መጥቀስ ያስፈለገው በኢሕአዴግ ዘመን ያለውን ዓይነት ልማት የውጭ ወራሪዎችም ሳይቀሩ ያደርጉት የነበረ ዓይነት መሆኑን ለማስታወስ ሲባል ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹በመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ከዓለም ሦስተኛ ደረጃ ሲቀመጥ፣ አገሪቱን በግል ኢንቨስትመንት ግን ከመጨረሻ ስድስተኛ ደረጃ ላይ› እንዳስቀመጣት የዓለም ባንክ የሰሞኑ ሪፖርት ይነግረናል፡፡ የግል ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ አልከሰመም እንዲባል ያደረገውም ቢሆን በጥቂት ባለሀብቶች እና በገዢው ፓርቲ አባላት፣ ደጋፊዎችና የስርዓቱ ተጠቃሚዎች የሚመሩ መካከለኛ አቅም ያላቸው ኢንዱስትሪዎች ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ይህ ለአንድ ወገን መጠቀሚያነት ብቻ ሰለባ የሆነ የግል እና የመንግሥት ኢንቨስትመንት የኢትዮጵያ መንግሥትን የ‹‹ልማት እንቅስቃሴ›› ከቅኝ ገዢዎች የልማት እንቅስቃሴጋ እንድናመሳስለው ያስገድደናል፡፡

ያም ሆኖ ግን ኢሕአዴግን ከወራሪው ፋሺስትጋ ማመሳሰል ጨካኝነትም፣ ኢ-ሚዛናዊነትም ሊሆን የሚችልባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ ሌላው ቢቀር ትንሽም የሚንቀሳቀሱት የግል ኢንቨስትመንቶች ንብረትነታቸው ያው ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ በሆኑ ሰዎች መሆኑ ከሚጠቀሱት አንዱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የሚያደርገውን መሠረታዊ ልማት ለአገሪቱ በሥጦታነት ያቀረበው ይመስል ስለሚመካበት እና ሥልጣኑን ለማስቀጠያነት የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ስላደረገው፣ ቅኝ ገዢዎች ሳይቀሩ የሚያደርጉት ነገር መሆኑን ለማስታወስ እና ሕገ መንግሥቱም ቢሆን በአንቀጽ 89 ላይ እንደሚደነግገው ኢትዮጵያውያን ሁሉ የምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ተጠቃሚ የመሆን እና የተሻሻለ የኑሮ ሁኔታ እንዲያገኙ ፖሊሲ ከመቅረፅ እስከማስፈፀም ብሎም የሀብት ክፍፍል ፍትሐዊ እንዲሆን እስከማድረግ የሚደርስ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ማስታወስ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡

ለመሆኑ ከፕሮፓጋንዳው በመለስ፣ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የአንድ ታዳጊ አገር መሄድ ባለበት የምጣኔ ሀብታዊ ፍሰት እየፈሰሰ ነው ወይስ በዘፈቀደ የሚጓዝ? ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የሚታይበት ነው ወይስ ጥቂቶች ሲበለፅጉ ብዙኃን የሚቆረቁዙበት? ተራ የበጀት ቁጥር ዕድገት ነው ወይስ በመጨረሻው ቀን የዜጎች ኑሮ አዎንታዊ ለውጥ የሚመዘገብበት?...

የኢትዮጵያ ልማት፤
‹‹ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል››?

በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት አለ፡፡ እንደምሳሌ (የከተሞቹን ‹ማስተር ፕላን› በሚገባ መጠበቃቸው፣ የመኪና ማቆሚያ ማስተረፋቸው፣ ለተፈጥሮ/አካባቢ ያላቸው ተስማሚነት /environment friendliness/፣ ለሕዝብ የሚበጅ አገልግሎት ሰጪነታቸው /ወይም ኪራይ ሰብሳቢ አለመሆናቸው/ ግን ቢሆንም፣…) በየከተሞቹ መሐል በየጊዜው የሚበቅሉ ሕንፃዎች በሽ ናቸው፤ (በታቀደላቸው ጊዜ የሚጠናቀቁት ከስንት አንድ መሆናቸው ባይወራም፣ በመዘግየታቸው የሚወጣባቸው አገራዊ ወጪ/ብክነት ባይነገርም፣ ከጥራታቸው ይልቅ ብዛታቸው ብቻ ቢደሰኮርም) የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በርካታ ናቸው፤ (የዓመታዊ በጀቱ ሩብ ገደማ በለጋሽ አገራት የሚሞላ ቢሆንም፣ የዋጋ ግሽበቱ መቶኛ ከምጣኔ ሀብት ዕድገቱ መቶኛ ንፅፅር የሚበልጥ ቢሆንም) ሁለት አሐዝ ዓመታዊ የጠቅላላ ገቢ ዕድገት (GDP Growth) እየተመዘገበ ነው፡፡

እነዚህን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ተቃርኖዎች የዕድገት እና የልማት ልዩነት ውጤቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ልማት›› እያለ የሚጠቅሰው ነገር እና የምናየው እንቅስቃሴ እውነትም አገሪቷ እየለማች ነው እንድንል ያስገድዱናል፡፡ በተቃራኒው የብዙኃኑ ኑሮ ከአምና ካቻምና እየከበደ እንጂ እየቀለለ አልሄድ ሲል እንደሚባለው ‹‹የልማቱ ወጪ›› ሊሆን ይችላል በሚል በእንቆቅልሽ እንኖራለን፡፡ በጅቡቲ ወደብ ‹‹ኢትዮጵያውያን የሚበሉት መኪና ነው ወይ?›› እስኪባል መኪና ወደአገር ውስጥ እያስገባን፣ ብዙ መኪና አለባት በምትባለው አዲስ አበባ 45 በመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎች በአውቶቡስና ታክሲ የመጓጓዝ አቅም አጥሯቸው በእግር ነው የሚጓጓዙት ሲባል ሀብትና ዕድገቱ የት ሄደ ብለን ግራ እንጋባለን፡፡ በተለይ ‹ኢኮኖሚስት› ባለመሆናችን በኢኮኖሚ ሳይንስ ትክክለኛው ዕድገት ምትሀታዊ ለሚመስለን ሌሎች ባለሙያዎች ግራ እንደተጋባን አለን፡፡ እውን ግራ መጋባታችን የአለማወቃችን ውጤት ነው ወይስ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ራሱ ነው ግራ ተጋብቶ ግራ የሚያጋባን?

ዕድገት ወይስ ልማት (Growth Vs. Developtment)?

በምጣኔ ሀብታዊ ኢኮኖሚክ ልማት ላይ ቀደምት ከሚባሉት ተመራማሪዎች መካከል አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ማይክል ቶዴሮ ቀዳሚው ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ቶዴሮ ምጣኔ ሀብታዊ ልማትን ሲበይኑት ‹‹የኑሮ ደረጃ ማደግ፣ ሰዎች ለራሳቸው የሚኖራቸው ግምት መሻሻል ብሎም ከጭቆና ነጻ መውጣት እና በርካታ የሕይወት አማራጭ ማግኘት ነው›› ይላል፡፡

በጀርመን አገር ነዋሪ የሆኑት ኢትዮጵያዊው የምጣኔ ሀብት ፕሮፌሰር ፈቃዱ በቀለ ‹‹እንደጂዲፒ የመሰሳሉት የዕድገት መለኪያዎች በቀጥታ የሒሳብ ስሌት (Linear Mathematic) ስለሚሰሉ የተወሳሰበውን የኢኮኖሚክስ ዓለምና ተለዋዋጩን የሰው ባሕርይና የፍጆታ አጠቃቀም አስልቶ ማቀረብ በፍፁም አይቻልም›› ብለው ጽፈዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ዕድገት (Growth) የምጣኔ ሀብት ልማትን (Developtment) ያክል የሰፋ ጉዳይ አይደለም፡፡ ዕድገት የቁጥር ጉዳይ ሲሆን፣ ልማት ደግሞ የዜጎች ሕይወት ደረጃ መሻሻል ላይ ያተኩራል፡፡ ቢሆንም ግን የአንድ አገር ምጣኔ ሀብት ዕድገት ለልማት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ስለሚያደርግ ወሳኝ ነው፡፡ በመሐከላቸው ያለው መሥመርም ቀጭን ነው… በተለይ ለለሙት አገራት (developed countries) የምጣኔ ሀብት ዕድገት የምጣኔ ሀብቱን ሁኔታ ለመለካት ይጠቅማል፡፡ እንደኢትዮጵያ ባሉ በመልማት ላይ ያሉ አገራት (developing countries) ግን ከዕድገት ይልቅ ልማት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻል ረገድ በትክክለኛው የምጣኔ ሀብት መሥመር እንዲጓዙ ያግዛቸዋል፡፡

‹‹…የኢሕአዴግ መንግሥት በአለፉት ዐሥር ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ ሲታይ 10 በመቶ እንዳደገ ሲነግረን ከርሟል። ይህንንም እነ ዓለም የገንዘብ ድርጀትና በጠቅላላው የዓለም የኢኮኖሚ ማኅበረሰባት ያረጋግጣሉ። ይሁንና ግን በኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ውስጥ ስንትና ስንት የፈጠራ ሥራዎች በተካሄደባቸው የካፒታሊስት አገሮች ውስጥ እንደ ኢትዮጵያው ዓይነቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ታይቶ አይታወቅም። ለምሳሌ ፕሮፈሰር ሁንትና ፕሮፌሰር ሼርማን የሚባሉት ሁለት የአሜሪካ ፕሮፌሰሮች፣ Economy from a Traditional and Radical Point of View፣ በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ የአሜሪካን ኮንግረስ ያቀረበውን ሀተታ እንደዚህ ብለው ይመዘግባሉ። 1839-1879 . ባለው ጊዜ ውስጥ የአሜሪካን ኢኮኖሚ በግምት በተጨባጭ 4.3% 1879-1919 . ደግሞ 3.7% 1919-1959 . ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ 3% እንዳደገ ይገልጻሉ። ለዚህ ዕድገት የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ግኝት ወይም ፈጠራ 50% አስተዋፅዖ እንዳበረከተ ይናገራሉ›› በማለት ዶ/ር ፍቃዱ የዕድገቱ ቁጥር በራሱ አጠራጣሪ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ቁጥሩ በሚያከራክርበት ሁኔታ ‹‹አለ›› የሚባለው ዕድገት ልማትን ለማምጣት ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄን ማሰቡ በራሱ ያስፈራል፡፡

የኢንዱስትሪ እና የግብርና ዘርፍ ምርት እያሽቆለቆለ፣ የአገልግሎት (ሆቴል እና ቱሪዝም…) ዘርፉ ዕድገት ከታቀደው በላይ እየወጣ የ90 በመቶ አርሶ እና አርብቶ አደሮች አገሯ ዜጎች የኑሮ ደረጃ አድጓል ማለት አይቻልም፤ ዜጎች ከአገራቸው ለመውጣት የዱር አውሬ ሲበላቸውና የድንበር ጠባቂ ሲገድላቸው፣ የባሕር ሲሳይ ሲሆኑ እና በኮንቴነር ታፍነው ሲሞቱ ዜና በየዕለቱ እየሰሙ ዜጎች ለራሳቸው ያላቸው ግምት ጨምሯል ማለት አይቻልም፤ ዜጎች በ‹‹ፍርሐት ቆፈን›› በታሰሩበት እና ጭቆና በበዛበት ፖለቲካዊ ከባቢ እና የግል ኢንቨስትመንት በተዳፈነበት ገበያ አማራጮችን ማግኘት አይቻልም፡፡

እንግዴህ - በዚህ ሁሉ ማግኘት ‹‹አይቻልም›› በሚል ቃል በተከበበት አገር ውስጥ ማይክል ቶዴል የሚበይንልን ‹ልማት› መፈለጋችንን ማቆም  አልያም የልማት ትርጓሜን  ደግመን መበየን ጊዜው አሁን ነው፡፡ ስለምን ልማትን ያለአገሩ ትፈልጉታላችሁ?
---
*ጸሐፊው የኢኮኖሚክስ ባለሙያ ባለመሆኑ ሙያዊ ዕውቀት ያላቸው ድምዳሜውን እንዲሞግቱት በዚሁ አጋጣሚ ይጋብዛል፡፡

No comments:

Post a Comment