Tuesday, April 28, 2015

ስቃይና መብት ጥሰት -አጥናፍ ብርሃኔ

አጥናፍ ብርሃኔ 
ስቃይና መብት ጥሰት ያደረሱብኝ ሰዎቸ ስም ዝርዝር ( ሁሉም የፌደራል ፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል አባላት) በተለይ
- ሳጅን ምንላድርግልህ
-ታደሰ ወይም ጥጋቡ ( የሽፋን ስም )
- ኢንስፔክተር አሰፋ
- ም/ሳጅን መኮንን
- ኢንስፔክተር ገብሩ
ዋና ዋና የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመበት ቀንና ሰአት - ሚያዝያ 17 እስከ ሃምሌ 11 /2006 አም

የማሰቃየት ተግባራት የተፈጸመበት ቦታ - የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ህንጻ በተለይ ቢሮ ቁጥር 5.፣ 32

ዋና ዋና ማሰቃየት ተግባራት
- ታደሰ የተባለው መርማሪ ፓሊስ ያለምንም ምክንያት ምርመራ ክፍል ውስጥ እያነቀኝ በተደጋጋሚ “እውነቱን የማትናገር ከሆነ ሽባ ነው የምናደርግህ ፣ እኛ ለግለሰብ መብት አንጨነቅም” በማለት በጥፊ ሲደበድበኝ ነበር

- ሳጅን ምን ላድርግልህ የተባለ መርማሪ “ጦማር ምን ማለት አንደሆነ ተናገር” ሲለኝ ጦማር ማለት መጻፍ ነው ብለውም ፡።፡።”ምህጻረ ቃል ነው እያንዳንዷ ምጻረ ቃል ምን ማለት አንደሆነች ካልተናገርክ አንላቀቅም” በማለት ከግርግዳ ጋር እያጋጨ ደብድቦኛል፣ ከግርግዳ ማጋጨት ብቻም ሳይሆን ረጅም ሰአት ከአቅሜ በላይ የሆነ የአካል አንቅስቃሴ እየሰራሁ የተመረመርኩ ሲሆን ምራቁን እየተፋብኝ አጸያፊ ስድብ ሲሰድበኝ ነበር፡፡

- ግንቦት ወር ላይ ሳጅን ምን ላድርግልህ የተባለው መርማሪ “ ኢህአዴግን ለምንድነው ተችታችሁ የምትጽፉት ?” “ከአገር ውጪ የምትሄዱት የመንግሰትን ስም ለማጥፋት ነው አንጂ የአባይ ግድብ ቦንድ ለመግዛት አይደለም” በማለት እጄን ወደላይ አድርጌ አንድመረመር አንዲሁም ጆሮዬን እየጎተተ በጥፌ ሲደበድበኝ ውሏል፡፡ ከዚህ ቤት ደንቁረህ ነው የምትወጣው በማለትም ያስፈራራኝ ነበር፡፡ እየተፋብኝ አጸያፊ ስድብ እየተሰደብኩ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት ተፈጽሞብኛል፡፡

- በሰኔ ወር ኢንስፔክተር አሰፋ የሚባለው መርማሪ ሌሊት 6 ሰአት አካባቢ ጠርቶኝ አላማችሁን ካልተናገርክ ጭለማ ቤት ነው የምትገባው በማለት ከማስፈራራቱም በላይ ሌሎች እስረኞች ሲደበደቡ እና ሲጮሁ ሲያለቅሱ በማሰማት እነደነሱ አንዳትሆን በማለት ዛቻ ተፈጽሞብኛል።

- ሰኔ ወር ላይ ኢንስፔክተር ገብሩ የታሰርኩበት ክፍል ውስጥ በመግባት ወረቀት ጽፈሃል የሚል በውል በማላውቀው ምክንያት ከሌሎች እስረኞች ለይቶ በተኛሁበት በተደጋጋሚ ከባድ የእርግጫ ደብደባ ፈጽሞብኛል። ሲደበድበኝም ህዝብ ልታጫርስ ነው እያለ ነበር፣ አስካሁንም የዛን ቀኑን ድብደባ ምክንያት ነው ያሉትን ነገር አላውቀውም፡፡

- በማእከላዊ ቆይታዬ 4በ4 በሆነች ክፍል ውስጥ በቀን ሁለቴ ብቻ ለ15 ደቂቃ ወደውጪ በመውጣት ከአስር ሰው ጋር ተቆልፎብኝ ታሬያለሁ ፡፡ የመጸዳዳት እድልም ቀኑን ሙሉ አልነበረኝም ፡፡ በየቀኑ ከባድ የአካል አንቅስቃሴ መስራት የምርመራው አካል ነበር፡፡

- በሃምሌ ወር ከምሽቱ 2.30 አካባቢ ሳጅን ምንላድርግልህ ፣ ም/ሳጅን መኮንን እና ሌላ የማላውቀው መርማሪ በመሆን ጭንቅላቴን በሃይል ከግንብ ጋር በማጋጨት እና የኮምፒውተር ኬብል በማሳየት አንደምገረፍ በመንገር ሳጅን ምንላድርግልህ የተባለው መርማሪ ፓሊስ የጻፈው የእምነት ቃል ላይ በግዳጅ አንድፈርም ተገድጃለሁ፡፡

*ይህ ጽሁፍ ለኢትዬጲያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከገባው አቤቱታ ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው 

No comments:

Post a Comment