Monday, April 27, 2015

የተሰደድኩ 'ለታ - በጆማኔክስ ካሳዬ

1.    ቶሎ እርምጃ ወስደን ነገሮች በፍጥነት ባይከናውኑ ኖሮ ይህንን መልአክት አሁን ከቅሊንጦ ሆኜ የምጽፈው ይሆን ነበር፡፡

ዓርብ የአዳማ ከሰዓቱ ሙቀት ያየለ ነበር ለሥራ ነጠል እንድታደርገኝ መርጬያት የነበረችው ጥግ ሙቀት ሲያይልባት ወጣ ገባ ማለት ጀምሬያሁ ቅዳሜ ማታ ቴዲ አፍሮ በሚያዘጋጀው ኮንሰርት አንድንገባ አዲስ አበባ እየደዋወልኩ ስጠይቅ  ኤዲ (ኤዶም ካሳዬ)  እንደማትገኝ ስትነግረኝ ትንሽ ቅር ብሎኝ ነበር ቢሆንም ቀን ቴስት-ኦቭ አዲስ የምግብ ፌስቲቫል ላይ ሳልናገር ተከስቼ የዞን ዘጠኝ ጓደኞቼን እና ሌሎች ጓደኞቻችንን ሰርፕራይ ለማድረግ ዱለታ ላይ ነኝ፡፡

የቀኑ መገባደጃ ላይ አንድ አጭር የስልክ መልእክት ወደ ስልኬ ገባ ፡፡ዞላ(ዘላለም ክብረት) ነበር ፡፡
ስልክ መልእክቷ  እጥር ምጥን ያለች ብትሆንም አንዳንድ ጊዜ የዞን9 አባላት ኦንላየን ያለው የግል ቡድናችን ውስጥ ውይይቶቻችን በድምጽ ብልጫ መወሰን ሲኖርብን  ወይም ደግሞ የሞቀ ክርክር እየተደረገ አንድ ሰው ኦፍላየን ሲሆን “ኀረ ወደኢንተርኔት ና እና ሃሳብ ስጥ” አይነት ነገር መልእክት ስልካችን ላይ እንላላካለን፡፡ ከዞላ የመጣውም አጭር መልክት ተመሳሳይነት ነበረው፡፡  ግን ይሄኛው በጣም ያጠረ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ከዞላ ድጋሚ ሌላ ቴክሰት ተደገመ ፡፡  “they may arrest me” ይላል መልእክቱ ፡፡በድንጋጤ ወደ ኢንተኔት ስመጣ ሶሊ በሁሉም በኩም መልእክት ስትልክ ደረስኩ ፡፡ አብረው የነበሩት አጥኔክስ እና የበፍቄ ስልካቸው አይመልስም፣ ማሂ ከቢሮ ተወሰደች፣ አቤልም እንደዛው፡፡ የሆነ የከፋ ነገር እየተከናወነ ነው ዘግይተው ነው አንጂ እኔ መድረሳቸው እንደማይቀር ተስማማን፡፡


የዚያን ሰሞን ወከባችን ሲበዛና ምን ይሻላል የሚለው ውይይት ሲደጋገም ዞላ ‹‹ምንም በሌለበት ኢሕአዴግ እኛን ካሰረ አብዷል ማለት ነው›› ብሎ ይከራከር ነበር፡፡አሁን በአይኔ የማየው የመታሰር ስጋት መልእክት የመጣው ከዞላ ነው፡፡ የማህበራዊ ሚዲያን ፈጽሞ የማያውቀው ደህንነት ናቱን ሲያዋክበው “ናቲ ለደህንነት የትውውቅ ኮርስ እየሰጠ ነው” ብለን አንቀልድበትም ነበር ፡።  ናቲን አብረኽን ስራ የሚል ማስፈራራትም ጉትጎታም ሳይቀር ሲያዋክበው ነበር ፡፡ ጓደኞቹን አሳፎ ከሰጠ እሱ ምንም እንደማይሆን ሊወተውተውም ሞክሯል፡፡  አሁን የዞላን ንግግር እና እርግጠኝነት ሳስበው በእኛ እስኪደርስ ጠበቅን እንጂ ካበዱስ ቆይተው ነበር እላለሁ፡፡ 

የዛው ሰሞን  የዞን 9 አባላት የተጠናከረውን የደህንነቶች ክትትል ተንተርሶ ከፍተኛ እና ዝቅተኛ የመታሰር እድል ያላቸው በሚል ከፋፍለን  ለማስቀመጥ ሞክረን ነበር ፡፡ አገር ቤት ካለነው የመጀመሪያውን ደረጃ አጥናፍ እና በፍቄ ሲይዙ ማሂ እና እኔ መታሰር ስጋታቸው  የመጨረሻው ላይ ነው ብለን ታስበን የነበርነው ነን ፡፡ ማሂ መያዝ ዜና ይሄንን ግምታችን አፈር ድሜ ያበላ ነበር፡፡ ከዚህ ዜና በኋላ ኦን ላየን ካሉ ጓደኞቼ ነገሩን በማጣራት  ፈላጊዎቼ እስኪመጡ ሳልጠብቅ  ከስራ ቦታ ላፕቶፔን ብቻ ይዥ ተነስቼ ወጣሁ ፡፡ ስራ ቦታ ሰው ድንገት ከፈለገኝ ለስራ ወደ አዋሳ መሄዴን እና ቶሎ አንደምመለስ ተናግሬ ነበር ፡፡ ወደቤት መሄድ የማይቻል ሃሳብ ሆነ ቀኑም እየተገባደደ በመሆኑ ከስራ ቦታዬ ዞር ያደርገኛል ወዳልኩት አካባቢ ላፕቶፔን ይዥ በፍጥነት አቀናሁ ፡፡ ሥልክ ማጥፋት እና መቀየር፣ በሌላ ሥም አልጋ መከራየት፣ እንቅልፍ አልባ እጅግ በጣም ረጅም ሌሊት በአምባገነኖች በትር በሃዘን ልባችን የተሰበረበት ምሽት ነበር፡፡ የእኔ ነገር ያንን ምሽት ገና ስላለየለትም የኤዶም ስልክም ዝግ በመሆኑ ግራ እየተጋባንም( እስሩ ለዞን9 ብቻ ነው የመጣው የሚል የዋህ ሃሳብም ነበረን)  አንቅልፍ በአይናችን ሳይዞር ነጋ፡፡ ይህ ሌሊት ባለፈ በማግስቱ በእለተ ቅዳሜ አንዲት ነጭ ሸሚዝ እንደለበስኩ ላፕቶፔን ብቻ አንጠልጥዬ የጎረቤት አገር ኤርፓርት ላይ ሶል ተቀበለችኝ ምንም አይነት ኮምንኬሽን ስላልነበረኝ የኤዶምን መታሰር እርግጥ ዜና እና  የአስማማውን መታሰርም እዛው ሰማሁ፡፡  ቶሎ እርምጃ ወስደን ነገሮች በፍጥነት ባይከናውኑ ኖሮ ይህንን መልአክት አሁን ከቅሊንጦ ሆኜ የምጽፈው ይሆን ነበር፡፡  (በመትረፌ ብዙ ባለማድረጌ ከእነሱ ጋር መሆንን ብናፍቅም)፡፡  No comments:

Post a Comment