Tuesday, August 18, 2015

የልጅነቱ ሰለባ - ናትናኤል

‹‹3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ አበራ ከግንቦት 2004 ዓ.ም ጀምሮ ካልተያዙት ግብረአበሮች ጋር በመሆን በሕቡዕ በመደራጀትና የሕቡዕ ድርጅቱ የሀገር ውስጥ አስተባባሪ በመሆን በሥሩ በሚንቀሳቀሱት አባላት የሥራ ክፍፍልና መመሪያ በመሰጠት እራሱን የግንቦት ሰባት ብሎ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት በመፍጠር የግንቦት ሰባት ልሣን ለአባላት የሚሰጥ የሥራ መመሪያ [እና] (sic) በመቀበል ለአባላቱ በመስጠት ለአመፅና የሽብር ተግባር መፈፀም (sic) በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ስልጠና በመውሰድ በህቡዕ ቡድኑ መካከል የሚደረገውን የመልዕክት ልውውጥ የመንግስት የፀጥታ አካላት እንዳይደርሱባቸው በመደበቅና በስውር በመገናኝት Security in box (sic)  የህቡዕ ቡድኑ አመራሮች የሚሰለጥኑትን ስልጠና በመሰልጠን፡ ለአባላቱ ሥልጠና እንዲወስዱ በማመቻቸት ለዚሁ የአመፅ ተግባር እንዲውል ውጭ ሀገር ከሚገኙ የቡድኑ አባላት 48,000.00 ብር የተላከትን (sic) ገንዘብ ለቡድኑ አባላት በማከፋፈል የአመፅ ቡድኑ እና የሽብር ቡድኑን በመምራት […] (sic)፤››
ይህ ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ ‹የህብረተሰቡን ሰላም ወይም ጤና ለመንሳት በማሰብ የሽብርተኝነት ድርጊት ሞከሯል፣ አቅዷል፣ አሲሯል፣ አነሳስቷልና ተዘጋጅቷል› በሚል ስለ ፀረ-ሽብርተኝነት የወጣውን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 3(2) እና አንቀፅ 4 ጥሷል በሚል በከሳሽ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ የቀረበበት ክስ ነው፡፡
ጉዳዩን እያየ ያለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ 19ኛ ወንጀል ችሎትም ከሳሽ ያቀረባቸውን ‹የሰነድ ማስረጃዎች› (በነገራችን ላይ ከሳሽ በአጠቃላይ ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎችን ብቻ ነው፡፡ የቀረቡት የሰው ምስክሮች የሰነድ ማስረጃዎቹን ትክክለኛነት ለማስረዳት ብቻ የቀረቡ ናቸው) መርምሮ ናትናኤል ፈለቀ መከላከል ሳያስፈልገው በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ሕግ 141 መሰረት ‹ከክሱ በነፃ መሰናበት አለበት› ወይስ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ሕግ 142 መሰረት ‹ክሱን ሊከላከል ይገባዋል› የሚለውን ለመወሰን ቀጠሮ ይዟል፡፡ እኛም ናትናኤል ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎች ከቀረበበት ክስ አንፃር መመልከቱ የክሱን ምንነትና ሊጠበቅ የሚችለው/የሚገባው ብይን ምን መሆን አለበት የሚሉትን ጉዳዮች ለመመለስ ይህን ፅሁፍ አቅርበናል፡፡
***
የ16 ዓመቱ ናቲ ዘሚካኤልና ጓደኞቹ ክፍል ውስጥ የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሱ መበሻሸቅ አንዱ የትምህርት ቤት ጨዋታቸው ነበር፡፡ ናቲ ዘሚካኤልም ጓደኞቹን ለማብሸቅ በማሰብ አንድ ቀን ርዕስ የሌለው ግጥም ፅፎ ወስዶ ጓደኞቹን አበሸቀ፡፡ ደስ አለው፡፡ ይህ ባለ 16 መስመር ግጥሙ አጀማመሩ አስቂኝ ነው፤ እንዲህ፡
‹‹ኢትዮጵያ ሀገሬ፣ ማንም አይደርስብሽ፣
 ማሰብ የማይችሉ፣ ወታደሮች አሉሽ፡፡››
ግጥሙ ሲጠናቀቅ ደግሞ ‹ገጣሚው› የሚኖርበት ሰፈር በተለምዶ ‹አዲሱ ሚካኤል› የተባለው ሰፈር በመሆኑ ራሱን ‹ናቲ ዘሚካኤል› ብሎ ሰይሞ፤ የግጥሙ ፀሃፊ ‹ናቲ ዘሚካኤል› ብሎ የልጅነት ፊርማውን ‹ልማት የተጠሙ ኢትዮጵያዊያን› ከሚል በእጅ የተሳለ ማህተም ጋር አስቀምጧል፡፡ ልጅነት ደስ ይላል፡፡ ይህ ከሆነ ከ10 ዓመትበኋላ ግን ይህች ግጥም መዘዝ ይዛ መጣች፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት 6 ጦማርያንን እና 3 ጋዜጠኞችን ‹ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለማፍረስ በመሞከር ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ› በማለት ሚያዚያ 17 እና 18/2006 ባሰረበት ወቅት ከስድስቱ ጦማርያን አንዱ የሆነው የናትናኤል ፈለቀን ቤት በተፈተሸበት ወቅት ይህች ግጥም በዛኔው ናቲ ዘሚካኤል በአሁኑ ናትናኤል ፈለቀ የልጅነት ደብተር ውስጥ ተገኘ፡፡ ናትናኤል ላይም ‹የሽብር ተግባርን የምታስረዳ አንድ ገፅ የሽብር ሰነድ› ተብላ ‹በማስረጃነት› ቀረበች፡፡ እነሱ ‹ማስረጃ› የሚሉት እንግዲህ እንዲህ ነው፡፡

የሩቅ የሩቁ የሚከተለው ናትናኤል

ናትናኤል ከ10 ዓመት በፊት በልጅነት ዕድሜው የፃፈው ግጥም ‹ማስረጃ› ሆኖ እንደቀረበበት ሁሉ ሌላም በዋነኛ ማስረጃነት የቀረበበት ከ7 ዓመታት በፊት የተከሰተ ጉዳይ አለ፡፡ የግንቦት ሰባት ድርጅት ኒውስሌተር፡፡ ናትናኤል ኢሜል ውስጥ ግንቦት ሰባት የተባለ ፓርቲ መመስረቱን የሚገልፅ በኖቬምበር 02/2008 ከወዳጁ የተላከ የግንቦት ሰባት ኒውስሌተር፡፡ ይሄን የሚመለከት ሰው ኢሜሉ ውስጥ አንድ የፖለቲካ ድርጅትን አስመልክቶ የተፃፈ ፅሁፍ አንድ ሰው ቢገኝበት ታዲያ ምኑ ነው ወንጀል የሚሆነው; ብሎ መጠየቁ አይቀርም፡፡ ጉዳዩ ግን ከዚህም ያልፋል፡፡
  1. ይህ ኢሜል የተላከው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በነሃሴ 22/2001 ከመውጣቱ ከ9 ወራት በፊት በጥቅምት 22/2001 ነው፡፡ ሕግ ወደኋላ ሄዶ አይሰራም (Nonretroactivity of the law) የሚለውን የሕግ መርህ እያሰብን፡፡
  2. ይህ ኢሜል የተላከው ግንቦት ሰባት ለፍትህ እና ለነፃነት ድርጅት ከሌሎች 4 ድርጅቶች ጋር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀፅ 25 መሰረት ‹የሽብርተኛ ድርጅት› ተብሎ ከመፈረጁ ከ2 ዓመት ከ9 ወራት በፊት ነው፡፡
  3. እሺ ይሁን እንኳን ቢባል ናትናኤል አንድ ኢሜል እንዳይላክለት የማድረግ ምን አቅም አለው; ለዚህ የሚሆን ቴክኖሎጂስ አለን;
  4. ናትናኤል ኒውስሌተሩ ኢሜሉ ውስጥ ከመገኝቱ ውጭ ምን አደረገ; ምንም የቀረበበት ማስረጃ የለም፡፡

በአጠቃላይ ናትናኤል ከልጅነቱ እስከ ወጣትነቱ ድረስ የተከሰሰበት ሕግ ባልወጣበት ጊዜ የፃፈው/ያነበበው እየተከታተለ ዛሬ ‹ማስረጃ› ተብሎ ቀርቦበታል፡፡ አንድን ጉዳይ ወንጀል የሚያደርግ ሕግ በሌለበት አንድ ድርጊት ወንጀል መሆኑስ እንዴት ይታወቃል; ከናትናኤል ነቢይነት ይጠበቅ ነበር ማለት ነው?

‹ባንከር› የመሆን ጣጣ

ከሳሽ ክሱን እውነት ለማስመሰል የተለመደውን ‹ከውጭ ሀገር የተላከለትን ገንዘብ ተጠቅሞ…› የሚል ሀረግ ጦማርያኑና ጋዜጠኞቹ ላይ ያቀረበው ክስ ላይም ተጠቅሟታል፡፡ ናትናኤል ደግሞ የገንዘቡ ተቀባይ ተብሏል፡፡ ክሱ እንዲህ ይላል፡
‹‹…ለአባላቱ ሥልጠና እንዲወስዱ በማመቻቸት ለዚሁ የአመፅ ተግባር እንዲውል ውጭ ሀገር ከሚገኙ የቡድኑ አባላት 48,000.00 ብር የተላከለትን (sic) ገንዘብ ለቡድኑ አባላት በማከፋፈል…››
ለዚህ ማስረጃ ሁኖ የቀረበበት ደግሞ ናትናኤል ከሚሰራበት የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ለፌደራል ፖሊስ የተፃፈ እና ለናትናኤል ፈለቀ ኬኒያ ከሚገኝው የአርቲክል 19 የምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ  የተላከ 48,000.00 ብር ነው፡፡ ናትናኤል ለፖሊስ ‹በነፃ› ሰጠው የተባለው ቃሉም ላይ ‹‹እኔ የኮንስትራክሽ ቢዝነስ ባንክ ውስጥ ስለምሰራ አርቲክል 19 የተባለ የእንግሊዝ ግብረ ሰናይ ድርጅት በችግር ላይ ያሉ ጋዜጠኞችን የሚረዳ በመሆኑና ርዕዮት አለሙ ያለአግባብ ታስራ ችግር ላይ በመሆኗ በቤተሰቦቿ አማካኝነት እርሷን መርዳት ስለፈለገ በምሰራበት ባንክ በኩል ገንዘቡ ቢላክ በቀላሉ አውጥቼ ለቤተሰቦቿ መስጠት እንደምችል ስለገለፅኩላቸው 48,000.00 የኢትዮጵያ ብር በስሜ ልከውልኝ እኔም አውጥቼ ለርዕዮት ቤተሰቦች ሰጥቻለሁ›› ይላል፡፡ እንግዲህ ይህ ገንዘብ ነው ‹…ለአመፅ ተግባር እንዲውል…› የተባለው፡፡ እንግዲህ አርቲክል 19 ነው ‹…ውጭ ሀገር ከሚገኙ የቡድኑ አባላት…› የተባለው፡፡ ናትናኤል ባንክ መስራቱ ያመጣበት ‹ጉድ› እንግዲህ ይህ ነው፡፡

“እስክንድር ነጋ፣

ርእዮት አለሙ፣ ውብሸት ታዬ፣ አንዷለም አራጌ እና በቀለ ገርባ የተባሉ እስረኞችን ለማስፈታት ሰላማዊ ሰልፎች ላይ እና ድረ ገፅ ተሳትፎ በማድረጌ ጥፋተኛ ነኝ”
ይላል የናትናኤል ፈለቀ ‹የጥፋተኝነት› እምነት ቃል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአዋጅ ቁጥር 454/1997 በተሰጠው አስገዳጅ ትርጉም የመስጠት ስልጣን በመዝገብ ቁጥር 77842 እና 77097 ላይ እንዳስረገጠው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 27 (2) መሰረት ለፖሊስ ተሰጠ የተባለ ‹ጥፋተኛ ነኝ› የሚል ቃል፤ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 35 ለጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት የሚሰጥ ‹ጥፋተኛ ነኝ› የሚል ቃል እንዲሁም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 134 መሰረት ለመደበኛ ፍርድ ቤት የሚሰጥ ‹ጥፋተኛ ነኝ› የሚል ቃል ‹‹ተጠርጣሪው/ተከሳሹ ‹ጥፋተኛ ነኝ› ስላለ ብቻ ጥፋተኛ ነው ማለት አይደለም› ይልቁንም ቃሉን የሰጠበት መንገድና ጥፋተኛ ነኝ ያለበት ጉዳይ ተመርምሮ ነው ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባው›› በማለት አመክኖያዊውን ጉዳይ የሕግ መሰረት አስይዞታል፡፡ ናትናኤልም እንግዲህ በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ በቆየባቸው ሰማኒያ አራት ቀናት ውስጥ እጅግ በተራዘመ እና ሃይል በተቀላቀለበት ሁኔታ አንዲፈርም የተደረገበትና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 27 (2) መሰረት ለፖሊስ ተሰጠ የተባለ ‹የእምነት ቃል› ከዚህ የሰበር ሰሚ ችሎቱ ውሳኔ አንፃር መታዮት ያለበት ነው፡፡ ይህ የኢፌደሪን ሕገመንግስት አንቀፅ 19 (5) በጣሰ መንገድ በሃይል እና በማሰቃየት የተገኝ ‹ቃል› በይዘቱም እንደሌሎች ተከሳሾች ቃል ሁሉ አስቂኝና አስገራሚ ነው፡፡
‹በግፍ የታሰሩ ሰዎች መታሰር አይገባቸውም በማለት በድረገፅ በመፃፌ ጥፋተኛ ነኝ› የሚል ቃል ምኑ ታምኖ ነው ‹ማስረጃ› የሚሆነው? ‹የአሜሪካ እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን በማግኝቴና የውጭ ሃይሎችን ድብቅ አጀንዳ ሳላውቅ እነሱ ጋር በመስራቴ ጥፋተኛ ነኝ› በማለት ‹ወንጀሉን› አምኗል ብሎ ለፍርድ ቤት ከሳሽ ‹በማስረጃነት› ቃሉ እንደሆነ የገለፀው ሰነድ የቀረበበት ናትናኤል በዚህ ሰነድ ንፁህ መሆኑን ከሚያረጋግጥ በቀር ሰነዱን ሽብርተኝነትን ያስረዳል ብሎ ማቅረብ ለፍትህ ስርዓቱ ትልቅ ስድብ ነው፡፡
እንግዲህ እነዚህ ‹ማስረጃዎች› እና ናትናኤል ዞን 9 ላይ የፃፋቸው ሰባት ፅሁፎች ናቸው ናትናኤል ላይ ‹የሕብረተሰቡን ወይም የሕብረተሰቡን ክፍል ደህንነት ወይም ጤና ለመንሳት በማሰብ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም አቅዷል፣ ተዘጋጅቷል፣ አነሳስቷል፣ አሲሯልና ሞክሯል› ለሚለው ክስ ‹ማስረጃ› ሆነው የቀረቡበት፡፡ ታዲያ ናትናኤል ነፃ ከመባል ውጭ ምን ሊባል ይችላል? ምንም! ናትናኤል ነፃ ሰው ነው!
ናትናኤል ፈለቀ

No comments:

Post a Comment