Wednesday, September 2, 2015

ሠላማዊ ትግል ስንል?

ሠላማዊ ትግል ደርዘ ብዙ ትንቅንቅ ነው፡፡ አንዳንዶች ‹ሕጋዊ መንገዶችን ብቻ መጠቀም ነው› ብለው የምናሉ፤ ነገር ግን በዚህ የማይወሰንበት ጊዜ አለ፡፡ ሠላማዊ ትግል ከነፍስ ማጥፋት፣ አካላዊ ጉዳት ከማድረስ እና ንብረት ከማውደም መቆጠብን ብቻ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው ‹ሠላማዊ› የተባለው፡፡ ለምሳሌ ሕዝባዊ እምቢተኝነት (Civil disobedience) አንድ የሠላማዊ ትግል ዘርፍ ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ (ትንሹ) ‹‹ኢ- ፍትሐዊ ሕጎች፤ ሕጎች አይደሉም›› ይል ነበር፡፡ በዚህ ፍልስፍና ነው ለሕግ አለመታዘዝ የሚወለደው፡፡ ለምሳሌ በአፓርታይድ ስርዓት ውስጥ ያሉትን አግላይ ሕጎች በሠላማዊ ትግል ለመቃወም የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ከነደፋቸው ስልቶች አንዱ ለአግላይ ሕጎች የማይታዘዙ (እና በዚያ ሳቢያ ለመታሰር ፈቃደኞች የሆኑ /እስር እንደትግል/ ) ሰዎችን መልምሎ ማሰማራት ይገኝበታል፡፡ ተግባሩ ሠላማዊ ነው ግን ሕጋዊ አይደለም፡፡ ሕጉ ኢ-ፍትሐዊ ነውና፡፡

በኢትዮጵያ፣ በአብዛኛው የሚስተዋሉ ከኢ-ፍትሓዊ ሕጎች ይልቅ የሕግ የበላይነት ማጣት ነው፡፡ የማበላለጥ ጉዳይ ሆኖ እንጂ ኢ-ፍትሓዊ ሕጎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ሕዝብን ለማደንቆር (እንዳይነቃ) የወጣው የመያድ ሕግ እና ሁሉን ነገር ሽብር ያሰኘው የፀረ- ሽብርተኝነት ሕግጋት በዚህ ረገድ ሳይጠቀሱ አይታለፉም፡፡ 
ሆኖም የሕግ የበላይነትን ባለማክበር የሚፈፀሙ ጥፋቶች ይህንን አምባገነን ስርዓት የበለጠ ይገልፁታል፡፡ ለምሳሌ መደራጀት ይፈቀዳል (በሕግ)፣ በተግባር ግን ይደናቀፋል፡፡ ይህንን በሠላማዊ መንገድ መታገል የሚቻለው ከስርዓቱ ጆሮ ጠቢዎች በላይ የሆነ (ነገር ግን በሕግ ያልታወቀ) ሠላማዊ ድርጅት በመፍጠር ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት በሕግ ተፈቅዷል፤በተግባር ግን አይቻልም፡፡ ከቴክኒካዊ ማደናቀፊያ እስከ ጋዜጠኛ ማሰር በሚደርሱ ሕገወጥ ተግባሮች ነው ይህ የሚሆነው፡፡ ዘመኑ ይህን ለማሸነፍ ምቹ ነው፡፡ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከአፈናውም ከእስሩም በላይ የሆነ (በእነዚህ እርምጃዎች የማይደናቀፍ) የመረጃ ማቅረብ ወይም ሕዝባዊ ንቃት የመፍጠር ስራ መስራት ድርጅታዊ መረብ መፍጠር ይቻላል፡፡ የአገራችን የሰላማዊ ትግል ፈቀቅ አለማለት አማራጭ መንገድ ከማጣት ይልቅ ያለመፈለግ የፈጠረው ይመስላል፡፡ ኢሕአዴግ ‹‹ሠላማዊ ትግል አልፈልግም›› እያለ ቢሆንም እየሄዱ ፊት ለፊት መላተም ብቻ (አስፈላጊ ቢሆንም) በቂ አይደለም፡፡ አስፈላጊነቱ የስርዓቱን ሕገ-ወጥነት ለማሳየት ሲሆን በቂ የማይሆነው በዚህ የኢሕአዴግ ባሕሪ ፊት ለፊት መላተም ለውጥ ማምጣት ስለማይችል ነው፡፡ ፊት ለፊት መላተም ሲበዛ፣ መጠቃት ስለሚበዛ ሰዎች ትግሉን ከመቀላቀል ይልቅ በፍርሓት እንዲርቁት ያደርጋል፡፡ ይህን ችግር፣ በትጥቅ ትግል ቋንቋም ቢሆን ሲያስረዱ አቶ ገብሩ አስራት (‹ሉአላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ › ላይ) እንዲህ ብለዋል፡፡
‹‹አንድ አባት ገበሬ ‹‹ልጆቼ እንታረዳለን፣ መሬት ቀውጢ ትሆናለች እያላችሁ አትቀስቅሱ፡፡ የዚህ ዓይነት ቅስቀሳ ሰው ወኔው እንዲሞት፣ ተስፋ እንዲቆርጥና አንገቱን እንዲደፋ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ እናቸንፋለን፣ ተቃርበናል፣ አይዟችሁ፣ በርቱ፣ ብላችሁ ብትቀሰቅሱ ይሻላል›› ብለው መክረውን ነበር፡፡››
ቢያንስ በእኔ እምነት፣ ያውም ለቆረጠ እና ዓላማውን በቅጡ ለሚያውቅ ሰው ሠላማዊ ትግል ከአመፃዊ ይልቃል፡፡ እርግጥ የፍትሕ እጦት ትውልድ እየበላ የምንታገስበት አንጀት አይኖረን ይሆናል፡፡ ሆኖም አመፃዊ ትግል ፍትሕ የምናገኝበትን መንገድ ማሳጠር አይችልም፡፡ የካርል ማርክስ ‹‹There is no short cut to history›› (የታሪክ አቋራጭ መንገድ የለም ብሒል) እዚህ ይሰራል፡፡ ሚስተር ኪንግ በሠላማዊ ትግል ጎዳና ሦስት ደረጃዎች አሉ ይላል፡፡ መንቃት (Awareness) ፣ መደራጀት (Organize) እና መተግበር (Action) በቅደም ተከተል የሚመጡ የሠላማዊ ትግል ሒደቶች መሆናቸውን ይናገራል፡፡  የመጀመሪያዎቹ ሁለቱን (ምንጬ አጠገቤ ስለሌለ) አቀያይሬያቸው ይሆናል፡፡ አሁን ችግር የሆነብን ተግባር ተግባሩ እየቀደመ ነው፡፡ ጥቂት የነቁ እና የተደራጁ (ሁለቱንም ያሟሉ) አደባባይ ሲወጡ ወይም በሆነ የትግል ተግባር ሲጠመዱ ገዢው በቀላሉ ይጨፈልቃቸዋል፡፡ ለተመልካችም ሕዳጣን ያስመስላቸዋል፡፡ በሠላማዊ ትግል ሕዝብ ኃይል የጨበጠውን ገዢ የሚያሸንፈው በብዛት ነው፡፡ ብዙዎችን በኃይል መጨፍለቅ አይቻልም፡፡ እንግዲህ ስለመደራጀት ቀደም ሲል ለመጥቀስ ሞክሬያለሁ፤ አስፍቶ ማሰብ የእያንዳንዳችን ቀጣይ ድርሻ ይሆናል፡፡

መንቃት ለምንና ለማን?
‹ለውጥ› የሚፈልጉ ለውጥ አማጪዎች (Activists) ሕልማቸውን ብቻቸውን ይዘውት ምንም ማድረግ አይችሉም፡፡ ለሌሎች ማጋራት አለባቸው፡፡ በዚህ መንገድ ነው ተከታይ ማፍራትም ሆነ፣ ያፈሩት ተከታይ ሕልማቸውን ማስቀጠል የሚቻላቸው፡፡ ሕልማቸው ከራሳቸው አልፎ ሌሎች ላይ መጋባት ከቻለ ነው ከራስ ስዩምነት ወደ ሕዝበ ስዩምነት መሸጋገር የሚችሉት፡፡ ብዙኃን የሚመሩት/የሚሳተፉበት ትግል የመክሸፍ እድሉ አነስተኛ ነው፡፡ የ1953ቱን ሰዓረ መንግስት እንደምሳሌ እናስታውሰው፡፡ በወቅቱ የንጉሡ ደጋፊዎች እና የስዓረ መንግስቱ ደጋፊዎች ያደረጉትን ውጊያ ጣልያናዊው አንጄሎ ዴል ቦካ (la negus ባሰኘው መጽሐፋቸው) እንዲህ ተርከውታል፡-
‹‹ለሰዐታት የዘለቀ ውጊያ መንገዱ ላይ ተካሂዶ ነበር፤ ሕዝቡ ግን በወታደሮቹ መካከል የነበረውን ጦርነት ያለውገና (indifference) ይመለከተው ነበር፡፡›› (እንግሊዘኛው ትርጉም ገጽ 260)
በዚህ ታሪክ የምናስታውሰው ብዙኃኑ ለአመፃ የሚኖረውን ምላሽ ብቻ ሳይሆን ውጊያው ለምን እየተካሄደ እንደሆነ እንኳን ግንዛቤ እንዳልነበረው ነው፡፡ ደራሲው ሲቀጥል፡-
‹‹ . . . ግርማሜ ንዋይና ወርቅነህ ገበየሁ [የወቅቱ የደኅንነት ሹም]፣ ሁለቱም የአሮጌው መንግስት መውደቅ ብዙ ነገር ማግኘት እንደሚችል በቂ ግንዛቤ አለው ብለው የአዲስ አበባን ሕዝብ በመገመታቸው የምር ስህተት ፈፅመዋል፡፡››
ይሁን እንጂ የንጉሡ መንግሥት ከዚያ በኋላ የቆየው 13 ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ያ በኢትዮጵያ ታሪክ በአግባቡ የተደራጀ እና ዘመናዊ ሠራዊት እና የደኅንነት ተቋም የመሰረተው የመጀመሪያው መንግሥት የወደቀው ያለመሣሪያ ጩኸት ነው፡፡ በሕዝቡ መንቃት እና በሐሳብ መበለጥ፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ‹ሕዝቡ/ተማሪዎች ‹‹መሬት ላራሹ›› ሲሉ በወቅቱ መሬት የባላባቶች በመሆኑ መንግስት በሐሳብ ተበለጠ . . . ወደቀ› ይላል፡፡ አንጄሎ ዴል ቦካ ለዚህ ለውጥ የስዓረ መንግስቱ ሙከራ አስተዋፅዖ እንደነበረው አልሸሸገም፡፡ ከሙከራው በኋላ ሕዝቡ ነቃ ይላል፡-
‹‹ [ከዚያ በፊት የነበሩት] ሌሎች አማፂዎች፣ እነባልቻ፣ ጉግሳ ወሌ፣ እና ኃይሉ ተ/ሃይማኖት በማዕከላዊው ኃይል ላይ ያመፁት በጥላቻ፣ vendetta ወይም ምኞት ብቻ ተነድተው ነበር፡፡ ለአገሪቱ ያቀረቡት አማራጭ ራዕይ አልነበራቸውም፡፡›› (ገጽ 264)
የስዓረ መንግሥቱ ሞካሪዎች ግን ነበራቸው፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ያንን ራዕይ ከአፈሙዝ ፉክክሩ ነጥለው መመልከት ችለዋል፡፡ በወቅቱ አመፁን የደገፉ 200 ተማሪዎች ሰልፍ ወጡ እና ከትምህርታቸው ታገዱ፡፡ ቆይተው ግን ይቅርታ ጠየቁና ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመለሱ፡፡ እኔ የቅድመ እና ድኅረ ምርጫ 97ን ጉዳይ እንደዚህኛው ሰዓረ መንግስት ሙከራ ነው የምመለከተው፡፡ ያኔ ተማሪዎቹ ይቅርታ ጠይቀው ትምህርት ቤት ሲመለሱ የተከሰተው ዝምታ የተቀረፈው የአብዮቱ ሰሞን ነው፡፡ ዝምታቸው የተገፈፈው ሕዝባዊ ንቃቱን ተከትሎ ነው፡፡ ሕዝብ የነቃ ለታ ምንም እንኳን ወታደራዊው ጁንታ (ደርግ) ቢነጥቃቸውም ለውጥ መጥቶ ነበር፡፡ አሁን ሕዝብ መንቃት ያለበትን ያህል ሲነቃ ለውጥ ይመጣል፡፡ እኛ ዘብ ሆነን መጠበቅ የሚኖርብን የደርግ ዓይነቱ የለውጥ ሌባ እንዳይዘርፈን ነው፡፡
…ይቀጥላል፡፡

ይህ ጽሁፍ በፍቃዱ ዘ ኃይሉ ‹‹ ጨዋ›› ነዎት ‹‹ባለጌ››? በሚል ርዕስ ከሚያወጣቸው ተከታታይ ጽሁፎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

2 comments: