Tuesday, October 27, 2015

‹ዞን ፱› ከትላንት እስከ ዛሬ

ይህ ጽሁፍ የዞን፱ ጦማርን አስልክቶ በቀለም ቀንድ ጋዜጣ ላይ የወጣ ነው ፡፡ አርታኢው በጠየቁን መሰረት ለዞን9 ነዋርያን ይነበብ ዘንድ እዚህ አትመነዋል፡፡

በሙሉቀን ተስፋው

ብዙዎቻችን ስለ ዞን ፱ ጦማርያን እንጅ ስለ ‹ዞን ፱› ብሎግ ያለን ግንዛቤ ውስን ሊሆን ይችላል፡፡ እንዴት ተመሰረተ? ለምን ዞን ፱ ተባለ? ጦማርያኑ ተጠራርገው ወደ እስር እስኪወርዱ ድረስ ምን አከናወኑ? ለምን ሁሉም ሊታሰሩ ቻሉ? እንዴት ተፈቱ በሚለው ላይ ዘርዘር አድርገን ለማዬት ወደድን፡፡
በ2004ዓ.ም. ከወደ ቤሩት አንድ መጥፎ ነገር ተከሰተ፡፡ ‹ዓለም ደቻሳ› የተባለች ኢትዮጵያዊት በአሰሪዎቿ ተገደለች፡፡ የሚያሰሯት ሰዎች ታማ ነው የሞተች ቢሉም የሊባኖስ ቴሌቪዥን በአሰሪዎቿ በገመድ ስትጎተት የሚያሳይ ምስል ለቀቀ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያንን አስቆጣ፡፡የበለጠ የሚያሳዝነው ደግሞ ‹ዓለም› የሁለት ልጆች እናት ስትሆን ወደ ቤሩት የሄደችውም ገንዘብ ተበድራ ነበር፡፡ ‹ልጆቼንና ቤተሰቦችን ከችግር አድናለሁ› የሚል ተስፋን ይዛ የተጓዘችው ዓለም የተበደረችውን ገንዘብ እንኳ ሳትከፍል ሕይወቷ ማለፉ ሀዘኑን የከበደ አደረገው፡፡‹ዓለምን› ዓለም ከዳቻት፡፡ በማህበራዊ ሚዲያው በሰፊው ተራገበ፡፡
ከአስር በላይ የሆኑ ሰዎች በፌስ ቡክ ‹‹የዓለምን ቤተሰቦች ለምን አንረዳም›› የሚል እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ አንዳንዶቹ በርግጥም ቀደም ሲል ጀምሮ የራሳቸው ብሎግ ነበራቸው፡፡ ብዙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ሰው ሐሳቡን ደገፈው፡፡ ምናልባትም ማህበራዊ ሚዲያ መሬት የነካ ስራ በኢትዮጵያ የተሰራበት የመጀመሪያ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ዘመቻው ፍሬ አፈራና በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ለዓለም ደቻሳ ቤተሰቦች ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰብ መርሐ ግብር በሚያዚያ 2004 ዓ.ም ተዘጋጀ፡፡ አዘጋጆቹ ደግሞ እኚሁ ከደርዘን በላይ የሆኑ ልጆች፡፡ ገቢማሰባሰቡ ውጤታማ ሆነና የተፈለገው ድጋፍ ለዓለም ቤተሰቦች ተሰጠ፡፡
ከአዘጋጆቹ ጥቂት የሚሆኑ ልጆች ለምን ይህ ሆነ? የሚል ጥያቄ አንስተው በሰፊው ተወያዩ፡፡ የሥርዓቱ ብልሹነት ዜጎችን ለዚህ እንደሚዳርጋቸው ለማወቅ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ አማካሪም ቀጥረውም ማስጠናት የሚጠይቅ አልነበረም፡፡ ከብላቴናዎቹ የእሳቤ አድማስ በላይም አልሆነም፡፡ለሁሉም ግልጽ የሆነ ነገር ነው፡፡ ሥርዓቱ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል የሆነች፣ ዜጎች በአገራቸው ሰርተው የሚያድጉበት መንገድ ዝግ የሆነባት፤ ዜጎቿ በሰው ሀገር እንደ ዓለም ደቻሳ ኢሰብዓዊ በሆነ መልኩ ሲገደሉ እንኳ መጠየቅ የማይችል እንደሆነ ለማወቅ የመጠቀ አእምሮ ባለቤት መሆን አይጠይቅም፡፡ ግልጽና ግልጽ ፍንትው ብሎ የሚታይ እውነታ ነው፡፡
ብላቴናዎቹ የችግሩን ምንጭስ አወቅን፤ ከዚህ በኋላ ምንድን ነው ማድረግ የምንችለው? የሚል ወሳኝ ጥያቄ አነሱ፡፡ የዚህን ጥያቄ መልስ ማገኘት ቀላል ነው፤ ግን መስዋትነት ይጠይቃል፡፡ ለዚያውም የወጣትነት የጌጥ ዘመንን የሚበላ መስዋትነት፡፡ መስዋትነቱ ወንጀል ስለሆነ አይደለም-ግን በአፋኝ ሥርዓት ውስጥ ለመብት ቦታ የለም፡፡ ሀገራችን የጋራ እናድርጋት፤ ስለሚያገባን ስለሀገራችን እንነጋገር፤ አማራጭ ሐሳብ እናቅርብ ማለት ያስወነጅላል፡፡ በሞት ፍርድ አሊያም በእድሜ ልክ እስራት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡ የማን ደፋሮች ናቸው ፈርዖንን የሚናገሩ? በፈርዖን ላይ ማነው ከቶ ምላሱን የሚያነሳ? እንደሙሴ ኮልታፋ ለመሆን ካልሆነ በስተቀር? ያስብላል፡፡ ለፈርዖን የሰው ልጆች ደምናስቃይ የሰርግና የምላሽ ያክል ይጥሙታል፡፡ የጨቋኝነት ባህሪው ይኸው ነውና፡፡
ብላቴናዎቹግን ይህን አስበው ፈርተው ወደ ኋላ አላፈገፈጉም፡፡ የዓለምን ቤተሰቦች ለመርዳት ዝግጅቱን ካስተባበሩት 5 ልጆች፣ ፌስ ቡክ ላይ በንቃት ይከታተሉ ከነበሩት ደግሞ 4 ልጆች ሲደመሩ 9 ያክል ልጆች ሆነው የ‹አክቲቪዝም› ሥራ ለመስራት ዝግጅታቸውን አጠናቀቁ፡፡የፖለቲካ እስረኞችን በፕሮግራም ለመጠየቅ የእቅዳቸው አካል አደረጉት፡፡ በፌስ ቡክ፣ ቲዊተርና በየነ መረብ ዘመቻ ጀመሩ፡፡ በ2005ዓ.ም. ከእለታት በአንደኛው ቀን ‹ርዕዮት አለሙን› ለመጠየቅ 9 ሆነው ቃሊቲ ወረዱ፡፡ ርዕዮት አለሙ ጋር እያወሩ አንዲት ‹አሸባሪ› ሴት ‹‹እንዴት ናችሁ ዞን ፱ኞች?›› አለቻቸው፡፡ ስሟ ሒሩት ክፍሌ ይባላል፤ በግንቦት 7 አባልነት ቃሊቲ የወረደች ‹አሸባሪ ሴት› ናት፡፡ ብላቴናዎቹ ግራ ገባቸው፤ ‹ይህች ሴት እብድ ናት እንዴ?› ሳይሉ አይቀሩም፡፡ በእርግጥ በጠባብ አጥር ውስጥ ከብዙ ቶርቸርጋር መኖር ሊያሳብድ እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ባሕታዊ እንዳይሏት ቃሊቲ ገዳም አይደለም፡፡
ርዕዮት አለሙ ብዙ እንዲጨነቁ አልፈቀደችም፡፡ በዝርዝር የ‹አሸባሪዋን ሴት› ንግግር ተረጎመችላቸው፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ቃሊቲ ማረሚያቤት በስምንት ዞን የተከፋፈለ ነው፡፡ ለካ የቃሊቲ ታሳሪዎች እኛን ከማረሚያ ቤቱ አጥር ውጭ የምንኖረውን ዜጎችን ‹ዞን ፱ኞች› እያሉ ነው የሚጠሩን፡፡ ስለዚህ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ አንድ የጠቅላላ እውቀት ጥያቄና መልስ ‹ልማታዊው አርቲስት ሸዋፈራው ደሳለኝ› ቢያዘጋጅ እንዲሁም ለተወዳዳሪዎቹ ‹‹ሰፊውና ብዙ እስረኛ ያለበት ዞን የትኛው ነው?›› ብሎ ቢጠይቅ መልሱ ‹‹ዞን ፱››የሚል ይሆናል፡፡ ሚስጥሩ ግልጽ ነው፤ በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ሁሉም ዜጋ እስረኛ ነው፤ ሁሉም ዜጋ የፈርዖን ግዞተኛ ነው፡፡
በበየነመረብ ለሚያደርጉት ዝግጅት ማን እንበለው? እያሉ ሲያነሱ ከብላቴኖቹ አንዱ ጆማኔክስ ‹የአሸባሪዋን ሴት› ቃል ‹‹ለምን ዞን ፱አንለውም?›› የሚል ሐሳብ አቀረበ፤ በሙሉ ድምጽ ጸደቀ (እንደ ኢህአዴግ ፓርላማ እንዳትሉ አደራ)፡፡ ብላቴኖቹ ‹‹ስለሚያገባን እንጦምራለን!›› የሚል መሪ ቃል ይዘው ዘመቻቸው ጀመሩ፡፡ ዘመቻው ፍጹም ሰላማዊ፣ ብዕር እንጅ ጥይት ያልያዘ፣ ሰላምን እንጅ ጥፋትንያልሻተ፣ በፊትም በኋላውም ምንም ኮልኮሌ የሌለው ነበር፡፡
ልጆቹ በጋራ ‹‹የሚያገባው ትውልድ ፍለጋ›› የሚል በጋራ ስለሀገራችን እንነጋገር፤ የጋራ ትርክት እንፈለግ የሚል ይዘት ያለው ጽሁፍ ጻፉ፡፡ድረ ገጹ በተከፈተ በ15ኛ ቀኑ ሀገር ውስጥ ያሉ ሰዎች እንዳያዩት ታገደ፡፡ ለፈርዖን ምን ይሳነዋል? ጌታውን አመስግኖ ማደር ያለበትን ምስኪን ሕዝብ ስለምን የእነዚህን ብላቴኖች ወግ ያነባል? በቃ ተከለከለ፡፡ ያም ሆኖ አራት ተከታታይ የበየነ መረብ ዘመቻዎች ተካሄዱ፡፡አንደኛው ሕገ መንግሥቱ የጸደቀበትን 18ኛ ዓመት በዓል ሲዘከር ‹‹ሕገ መንግሥቱ ይከበር›› ያልተከበሩ የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች ዘርዝረው ተቹ፡፡ ‹‹ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት አሁኑኑ ለሁሉም!›› በማለት አንቀጽ 29ን መሰረት በማድረግ ዘመቻውን ደገሙት፡፡ሦስተኛም ‹‹የሰላማዊ ሰልፍ መብታችን ይመለስ!›› ሲሉ ሠለሱት፡፡ 4ተኛም ‹‹ኢትዮጵያዊ ሕልም ኑ አብረን እናልም!›› ሲሉ ድምጻቸውን አሰሙ፡፡
የልጆቹ ድምጽ ቀልቃላ ነበር፤ ብዙ ርቀት ብዙ በጣም ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ የሚሰማ፡፡ እንቅልፍ የሚቀሰቅስ ድምጽ! ፈርዖንን የማያስተኛ፡፡እነዚህ ነገረኞች ‹‹የዞን ፱ ዐመታዊ መጽሐፍ›› ብለው በነጻ አደሉ፡፡ አዲስ ራዕይ በገንዘብ በሚቸበቸብበት አገር በነጻ አንብቡብሎ መስጠት ምን ይሉታል? ግን ሆነ፡፡ መጽሐፉ በደረ ገጻቸው በነጻ ተለቀቀ፡፡
ከዚህ በኋላ ፈርዖን ትዕግዙ አለቀ፡፡ በመጀመሪያ በጓደኞቻቸው ማስፈራሪያ ተላከባቸው፡፡ ‹ፈርዖን አምርሯል፤ ከዚህ በኋላ ውርድ ከራሴ›ተባሉ፡፡ በ2006 ዓ.ም. ሁለቱን ብላቴኖች ከመላእክት የፈጠኑ ደህንነቶች ጠርተው ‹‹ስለምን አትሰሙም? ጌቶቻችን ስለምን ታስደነብራላችሁ? ካላረፋችሁ ቀሳፊ መልኣክ እንልካለን›› አሏቸው፡፡
መደናገጥ ተፈጠረ፡፡ ልጆቹ አሁንም ጠየቁ- የሠራነው ወንጀል ምንድን ነው? አሉ፡፡ መልሱ ግን ምንም ነው፡፡ ሙሴስ ቢያንስ ወገኖቹን ለማዳን የሌላ ሰው ሕይወት አጥፍቶ ነው የተሰደደ፤ እኛ ግን ምንም አልሰራንም፡፡ ስለዚህ የጌቶች ንዴት እስኪበርድ እንጠብቅና እንቀጥል ሲሉ መከሩ፡፡ ያም ሆኖ ምርጫ 2007 እየቀረበ መጣ፡፡ ይህ ምርጫ ዝም ብሎ መሆን የለበትም፤ ምንም እንኳ ጌቶች ባይወዱትም ዜጎች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ሕዝብ የማንቃት ሥራ እንጀምር አሉ- በምክር ቤታቸው፡፡ የነዚህ ልጆች ምክር ቤት 547 ወንበር ላይ ከተጎለቱ ሰዎች በላይ ማነቃቃት የሚችል ከቶ ምን አይነት ታምር ቢሆን ነው? ያስብላል፡፡
በሚያዚያ2006 ዓ.ም በብሎጋቸው ምርጫ 2007ን በተመለከተ በሰፊው እንደሚሰሩ ባበሰሩ በሳምንቱ ከሚያዚያም በ17ኛው ቀን ከፈርዖን ዘንድ የጥፋት መልእክተኞች 9 ልጆችን ለቃቅመው ወሰዱ፡፡ ስድስቱ ከጦማርያን ወገን ሲሆኑ ሦስቱ ደግሞ ሐሳባቸውን የሚደገፉ ጋዜጠኞች(ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃይሉና ኤዶም ካሳዬ) የጥፋት መልእክተኞች ሰለባ ሆኑ፡፡ ከጦማርያኑ ሦስቱ ደግሞ ከጥፋት ውሃ እንዲድኑ እግዚአብሔር ስለፈቀደ ከነነዌ ወጥተው ነበር፡፡ ለወሬ ነጋሪ ሶልያና ሽመልስ፣ ጆማኔክስ ካሳዬና እንዳልካቸው ኃ/ሚካኤል ቀሩ፡፡ ‹ሙሴም ከምድያም ምድር የተመለሰው ፈርዖን እንደማይጎዳው ባወቀ ጊዜ ነው፤ እኛም የፈርዖን ብርታት እስኪደክም ወደ ነነዌ አንመለስም› ብለው ይመስላል እንደወጡ ቀሩ፡፡
የታሰሩት ግን የእድሜያቸው 84 ቀን በማዕከላዊ አለፈ፤ አንዲት አራስ ሴት ልጇን ወልዳ ክርስትና አስነስታ እንግዶቿን ሸኝታ ወደ ባሏ የምትመለስበትን ጊዜ ያክል፡፡ 75 ቀናት ግን በጨለማ ክፍል ውስጥ ፀሀይ የማታውቀው ሀገር - ማዕካላዊ ሳይቤሪያ፡፡ በሳይቤሪያ ጥፊና በትር የእለትምግባቸው ሆኖ ስድብ እንደ ምርቃት እየቆጠሩት ቶርቸር ከፈጣሪ የተላከላቸው መና ሆኖ፣ ከባድ ስፖርት እየሰሩ ያን ያክል ጊዜ ቆዩ እንጅ እንደ አራስ አጥሚት እየጠጡ ገንፎ እየሰለቀጡ አልነበረም፡፡
በ2006 ሐምሌ በገባ 11ኛው ቀን ሲሆን ክስ ተፈጠረባቸው፡፡ ሲያንስ 15 ዓመት በእስር በሚያቆየው ሲበዛ ደግሞ ከመሬት በሚስወግደው በሐሙራቢ ሕግ ጨካኝ አንቀጽ ‹ሽብር ማነሳሳት፣ ለማነሳሳት ማሰብ፣ ማሴር…› በሚለው ተወንጅለው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ‹‹የቀለም አቢዮት ለማስነሳትአስባችኋል›› አሏቸው፡፡ ምስክሮች ቀረቡ፡፡ ሠልስቱ ደቂቃን በናቡከደነፆር ዙፋን በቀረቡ ጊዜ ምስክሮቹ የተናገሩትን የመሰለ ነበር፡፡እነዚያ ምስክሮችስ ቢያነስ ለቆመው ምስል እንደማይሰግዱ ያውቃሉ፡፡ አለመስገድም ወንጀል የሆነበት ዘመን ነበር፡፡
ፍርዱ እየተጓተተ አንድ አመት አለፈ፡፡ እድሜም እንደዋዛ ቆጠረ፡፡ የጓጉለት ምርጫ ድራማ በቃሊቲ ሆነው አለፈ፡፡ በየጊዜው ፍርድ ቤት ይመላለሳሉ ግን ምንም ውሳኔ የለም፡፡ ምርጫ ካለፈ በኋላ ለብይን ለሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ተያዘ፡፡ ቀደም ብሎ ግንሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ክሱ ተቋርጦ 5ቱ ልጆች ማለትም በክስ መዝገብ 4ኛ ተከሳሽ ማህሌት ፋንታሁንና 6ኛ ተከሳሽ ዘላለም ክብረት (ሁለቱም ጦማርያን) እንዲሁም 8ኛ ተከሳሽ አስማማው ኃ/ጊወርጊስ፣ 9ኛ ተከሳሽ ኤዶም ካሳየና 10ኛ ተከሳሽ ተስፋለም ወልደየስ(ሁሉም ጋዜጠኞች) ወጡ፡፡
ጥቅምት5 ቀን 2007 ዓ.ም. ደግሞ ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር በኋላ 1ኛ ተከሳሽ ሶልያና፣ 3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል፣ 5ኛ ተከሳሽ አጥናፍ እና 7ኛ ተከሳሽ አቤል በነጻ ተሰናበቱ፡፡ 2ኛው ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ ጽሑፎችህ ሽብር ያነሳሳሉ ተብሎ ተለይቶ ቀረ፡፡ የበፍቃዱ ክስ ወደ ወንጀል ተቀይሮ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 257/ ሀ ከአስር ቀን እስከ 6 ወር እስር ሊያስቀጣ በሚችል ወንጀል ተቀየረ፡፡ ምንም እንኳ የተከሰሰበት ወንጀል ሊያስቀጣ የሚችለውን ሦስት እጥፍ በእስር ቢያሳልፍም በ20000 ብር (ሃያ ሽህ ብር) ዋስ ከ544 ቀናት በኋላ በቂሊንጦ የተሰጠውን የሊዝ ቦታ ለተረኛ አስረክቦ ወጥቷል፡፡
ዞን ፱ኞች በአንድ ዓመት ከ5 ወር ጊዜ ውስጥ 39 ጊዜ ፍርድቤት ተመላልሰዋል፡፡ በፈቃዱ ለ40ኛ ጊዜ የፊታችን ህዳር 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡

በጨረሻም አልን ‹‹ኢትዮጵያዊ ህልም ኑ አብረን እናልም!››

አበቃሁ

(ይህጽሁፍ የተዘጋጀው ከእስር የወጡ የዞን 9 ጦማርያን ጋር በተደረገ ውይይት ነው፡፡) 

No comments:

Post a Comment