Thursday, January 21, 2016

ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ፡ የግማሽ ምዕተ ዓመት ጉዞ

በዘላለም ክብረት

ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ ይሄው 25 ዓመታት እየሆነው ነው፡፡ ይሄም በጆን አቢኒክ ቋንቋ ኢሕአዴግን በኢትዮጵያ የሪፐብሊክ ታሪክ (ከዘውዱ አገዛዝ በኋላ) ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ የቆየው ስርዓት ያደርገዋል፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ስልጣን በወጣበት ወቅት የዓለም ፖለቲካዊ ምህዳር ከግራ ወደ ቀኝ ያደረገው ሽግግር ኢሕአዴግ ይዞት የመጣውን ቀይ የፖለቲካ ጥብቆ ባንዴ አውልቆ የምዕራቡ ዓለም መለያ የሆኑትን ባለ ነጭ፣ ሰማያዊና ቀይ የፖለቲካ ጥብቆ በግድ እንዲለብስ የተገደደበት ነበር፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና ይሄን የኢሕአዴግን የርዕዮተ ዓለም ግርታ (confusion) ‹የግራ ፍሬቻ እያሳዩ ደብረ ብርሃን የደረሱት የኢሕአዴግ መሪዎች በፍጥነት ወደ ቀኝ ታጥፈው አዲስ አበባ ገቡ› በማለት ውብ አድርገው ይገልፁታል፡፡ ይህ ድንገተኛ የፖሊሲ ለውጥ ነው በመጀመሪያዎቹ አስር የስልጣን ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱን ‹በግምት› ሊባል በሚችል መልኩ  ያለወጥ ፖሊሲ እንዲመራት ያደረገው፡፡ ዴሞክራሲን በሚመለከት ግን ከዚህም በባሰ ደረጃ እስከ አሁን ድረስ ወጥ ሊባል የሚችል ፖሊሲም ሆነ እርምጃ ማግኝት ከባድ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡

እንግዲህ የመንግሥት ፖሊሲ የሌለ ወይም ግልፅ ባለሆነ ጊዜ መንግሥቱን የሚመሩት ግለሰቦች የሚሰጡት አስተያየትና ሐሳብ ውስጥ ነው ፖሊሲውንና ርምጃውን የምናገኝው፡፡ ኢሕአዴግን በሚመለከትም ይህ የመሪውን ግለሰብ ቃል መከተል የፖሊሲውን አመላካች ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የግል ስሜትና ፍላጎትም የኢትዮጵያ ፖሊሲ ሆኖ ለረጅም ጊዜ ዘልቋል ማለት ይቻላል፡፡ ችግሩ ግን የመለስ ስሜትና ፍላጎት በየጊዜው ተቀያያሪ መሆኑ ነበር፡፡

መለስ አንድ ኢትዮጵያን ከ1983 እስከ 1993 ለዐሥር ዓመታት የገዙ ሲሆን በዚህ ጊዜ በብቸኝነት ሥልጣን ለመቆጣጠር የማያስችሉ ውስጣዊ ሁኔታዎች የነበሩ በመሆኑ በአፍ ደረጃ የዚህ ጊዜው መለስ ‹ዴሞክራት› መስለው ይታዩ ነበር፡፡ መለስን አንድን ከዴሞክራሲ ጋር በተገናኝ በሚገባ የሚገልፃቸው በጥር 1983 በኢሕአዴግ የመጀመሪያው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ እንዲህ በማለት የተናገሩት ንግግር ነው፡ 
ሕዝቡ ያልተገደበ የዴሞክራሲ መብት አለው እስካልን ድረስ ይህ መብት የመናገርን መብት፣ የመደራጀት መብት፣ የመጻፍን መብት፣ የመቃወምን መብት ሁሉ ያካተተ መሆን አለበት፡፡ የፈለገውን ፖርቲ መመሥረት መብቱ ነው፡፡ አንድ ብቻ ይበቃሀል፣ ሦስት ብቻ ይበቃሀል ወይም አርባ አራት ብቻ ይበቃሀል ተብሎ የሚገደብ ነገር አይደለም፡፡ እንደፈለገው ራሱን በነጻ ማደራጀት ይችላል፡፡ የራሱን አቋም የሚያራምድበት፣ የፈለገውን ሀሳብ ይዞ ቢያስፈልገው ፓርቲ መመሥረት ይችላል፡፡ ይሄ የዴሞክራሲ መብቱ ነው፡፡

መለስ ሁለት ደግሞ ኢትዮጵያን  ከ1983 እስከ 1998 ድረስ የገዙ ሲሆን በዚህ ጊዜም የውስጥ የፓርቲ ሽኩቻውን በድል አጠናቀው ዴሞክራሲን ለውስጠ ፓርቲ የመታገያ/የማጥቂያ ዘዴ በማዋል ለውጭ ተመልካቾች ደግሞ ራሳቸው ዴሞክራት አስመስለው ያቀረቡበት ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው መለስ በነሐሴ 16፣ 1993 በኢሕአዴግ አራተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ፡ 
ዴሞክራሲን የመከተል ጉዳይ የተሻለ አሠራር መከተል ወይም ያለመከተል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የጥገኛ ዝቅጠትን ለመመከት የሚያስችል ኃያል ትጥቅ የመያዝ ወይም ያለመያዝ ጉዳይ ነው፡፡
በማለት የተናገሩት ንግግር ነው፡፡

መለስ ሦስት ደግሞ ከምርጫ 97 ማግስት ጀምሮ እስከ 2004 መጨረሻ ወይም እስከ አሁን ድረስ በሥልጣን ላይ የነበሩት/ያሉት (እንደተመልካቹ ነው) ሲሆኑ ዴሞክራሲ ይሉት ጉዳይ የማይሆን ነገር ነው በማለት ከምዕራባዊያን ጋር በዴሞክራሲ ጉዳይ ላይ ፍጥጫ ውስጥ የገቡት ናቸው፡፡ ለዚህም ማሳያ ይሄን ዘንድ መለስ በኢሕአዴግ ስድስተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፡ 
በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ አጀንዳችን ሌሎች ስላሉት (ምዕራባዊያኑን ለማለት ነው) የምናደርገው አጀንዳ አይደለም። ለራሳችን ለአገራችን ህልውና ፤ ለልማታችን ቀጣይነት ወሳኝ ነው ብለን በማመናችን ነው።
ብለዋል፡፡

መለስ ሦስት ከምርጫ 97 ወዲህ ከተለያዩ የውጭ የሚዲያ ተቋማት ይቀርብላቸው ለነበረው የሃገሪቱ የዴሞክራሲያዊነት ጉዳይ ጥያቄ ሲመልሱ አንዴ “To impose democracy from outside is inherently undemocratic” እያሉ ምዕራቡን ዓለም በተዘዋዋሪ ሲጎሽሙ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በቀጥታ ምዕራቡን ዓለም “Democratic transformation for us is not mimicking some facets of Western governance” እያሉ ሲያስጠነቅቁ፤ ሲያሻቸው ደግሞ የምዕራቡን ዓለም መሪዎች “We will democratize Ethiopia not to please Tony Blair or anybody else; we will democratize Ethiopia because it is good for us” በማለት በቀጥታ ስም እየጠቀሱ ሲገረምሙ፤ ባስ ሲል ደግሞ የምሁራኑን ረጅም ጊዜ የፈጀውን የዴሞክራሲና - ዕድገት ግንኙነት ምይይጥን “There is no direct relationship between democracy and growth” በማለት ቁርጥ እያደረጉ ዴሞክራሲን የርዕዮተ ዓለም አጀንዳ በማድረግ ቀጥተኛውን ጥያቄ አዟዙረው ጠያቂውን በተከላካይነት ቦታ በማስቀመጥ ‹ይመልሱ› የነበሩ ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ መለስ አንድም ሆኑ መለስ ሁለትን አናገኝም፡፡

መለስ 1.0 እንዲህ ብለው ቢያልፉም፤ እርሳቸውን የተኩት (በራሳቸው ቋንቋ የመለስን ውርስ አስቀጣዩ) መለስ 2.0 ወይም ኃይለማርያም ደሳለኝ ከመለስ ሦስት ብዙም የተለየ ሃሳብ ባይኖራቸውም ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ያደረጓቸውን ቃለ ምልልሶች ስንመለከት ከመለስ ሦስት ትንሽ በተለየ መልኩ የመለማመጥ ባህሪን እናያለን፡፡ ምሳሌ ብንመለከትም፡
Something has to be understood that this is [we have] a fledgling democracy. Democracy cannot be built within a few years of time. We have to learn lots of things. But the thing is, we believe we are on the right track. [Though] there are number of [adequate] rooms for improvement [parties].
ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከተለያዩ አምስት የውጭ እና የሃገር ውስጥ የሚዲያ ተቋማት በሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የዴሞክራሲ ሁኔታ ተጠይቀው የመለሱት በጣም ተቀራራቢ የሆነ መልስ በአንድ አንቀፅ ሲጠቃለል ነው፡፡ መልሳቸውን ስንመለከት ከተጠየቁት ጥያቄ ተከትሎ ለሚመጣ ሌላ ‹አፋጣጭ› ጥያቄ መከላከያ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ‹ዴሞክራሲያችን ገና ጨቅላ ነው፣ ብዙ ማደግ እንዳለበት እንረዳለን - ነገር ግን ትክክለኛውን መሠረት አስቀምጠናል› የሚል ሆኖ እናገኛለን፡፡

እንግዲህ ‹ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ነች ወይስ አይደለችም› የሚለው ጥያቄ አሁን ብዙም የሚያጨቃጭቅ ጉዳይ ባይሆንም፤ ኢሕአዴግ በተለያዩ ጊዜያት ከላይ በተጠቀሱት አግባብ መልስ እየሰጠ ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ሥልጣን ላይ ያሉት ዋናዎቹ ሹመኞች በግፍ አገዛዝ ተማረው ትግል ውስጥ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ (ከ1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ) ያለውን የሃገሪቱን ዴሞክራሲ ‹ኦዲት› ማድረጉ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ከጨቅላነት መች ይወጣል? በርግጥስ ሶስቱ (የዘውዱ፣ ወታደራዊውና የአሁኑ) ስርዓቶች ዴሞክራሲን በሚመለከት ያሳዩት ይህ ነው የሚባል ልዩነት አለን? ለመሆኑ ዴሞክራሲ ነብስ የሚዘራው ምን ሲከሰት ነው? የሚሉትን እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን እንመልስ ዘንድ ያለፉት 45 ዓመታትን መረጃ (data) (የ45 ዓመታት ዳታን ለምን እንደመረጥኩ ከታች አስረዳለሁ) በማየት ከላይ የተጠየቁትን ጥያቄዎች ለመመለስ ይሞክራል ፅሁፉ፡፡

 ‹ሰምና ወርቅ ዴሞክራሲ›

በዚህ ጽሑፍ የዴሞክራሲ ምንነትና የትርጉም አተካራ ውስጥ ለመግባት አልተሞከረም፡፡ የተለያዩ ሊቆች በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ ትርጉሞች ሲሰጡት የነበሩ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በዜጎች ይሁንታ ተመርጦ የዜጎችን መብት የሚያስከብር ስርዓት መዘርጋት የዴሞክራሲ ምንነት ተደርጎ ቢወሰድ የማይስማማ ቢኖር እንኳ እዚህ ግባ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ይሄም ሆኖ ‹አንድ ሀገር ምን አይነት ዴሞክራሲ ያስፈልጋታል?› ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ‹ዴሞክራሲ ምንድን ነው?› ከሚለው ጥያቄ በላቀ ደረጃ አወዛጋቢና ዘመናትን ተሻግሮ የመጣ ጥያቄ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከትናንት እስከዛሬ (በተለይ በገዥዎቿ) ‹የምዕራቡን ዓለም አይነት ዴሞክራሲ ገልብጠን የምናመጣ አይደለንም፤ (ምንም እንኳን በሕገ መንግስቶቿ ከምዕራብ የዴሞክራሲ እና የነፃነት አስተሳሰብ የተለየ ነገር ባትደነግግም) እኛ ዴሞክራሲን የምናየው በራሳችን አውድ (context) እና አግባብ ነው› በሚል ‹ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ› አሰፍናለሁ በሚል በዓለም መድረክ እየታየች ትገኛለች፡፡ ‹ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ› ምን አይነት እንደሆነ ገዥዎቹ ማብራራት ባይችሉም፤ ምሁራን ግን ይሄን ጉዳይ ለመግለፅ ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም፡፡

የዳውሰን ኮሌጅ የፍልስፍና ዶክተሩ መምሬ መናሰማይ ይሄን ‹የኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ› ጉዳይ ‹ሰምና ወርቅ ዴሞክራሲ› በማለት ይገልፁታል፡፡ ሰሙ ከላይ የሚታየው መሠረቱን ምዕራቡ ዓለም ያደረገው የምርጫ ዴሞክራሲ (Electoral Democracy) (በአሁኗ ኢትዮጵያ የምርጫ አምባገነንነት (Electoral Authoritarianism) ሆኗል ይሉታል) ሲሆን፤ ወርቁ ደግሞ ‹ኢትዮጵያዊያን ከምዕራቡ ዓለም የሚስተካከል የራሳችን የሆነ ታሪክና ባሕል ስላለን ዴሞክራሲያችን ያን የራሳችን የሆነን ማንነት ማንፀባረቅ አለበት የሚል ነው› በማለት ያስረዳሉ፡፡ ይህ ሐሳብ ከነኔሬሬ እና ኑኩሩማህ ‹African Democracy› የሚጠቅስ ቢሆንም፤ በዚህ አግባብ ወርቁ ምን ማለት እንደሆነ ብዙም ግልፅ አይደለም፡፡ ‹ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ› ኖረም አልኖረም ኢትዮጵያ የአሁኑን ጨምሮ ባለፉት ሦስት መንግሥታት ስር የተለያዩ የዴሞክራሲ አመላካች የሆኑ ጉዳዩችን (ምርጫ እና የዜጎች መብትን በዋነኛነት) በሕግ ደንግጋለች፡፡ ከነዚህ ዴሞክራሲን አመላካች ከሆኑ መብቶች አንፃር የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ርምጃ ወደፊትና ወደኋላ ማየቱ ከምን ዓይነት ዴሞክራሲ? ውዝግብ ጀርባ ያለውን እውነታ ይነግረናልና እሱን እንመልከት፡፡

የግማሽ ምዕተ ዓመት የዴሞክራሲ ጉዞ

ዴሞክራሲ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ረጅም ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ ጉዳይ ቢሆንም ዓለማቀፋዊው የዴሞክራሲ መስፋፋት (democratization) ግን በዋናነት ያለፉት 60 ዓመታት ውጤት ነው ማለት ለብዙኃኑ የሚስማማ ሐሳብ ነው፡፡ ይሄን መስፋፋት ተከትሎም የተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት ሀገራትን እርስ በርስ በግልፅ በተቀመጡ መስፈርቶች በመገምገም ደረጃ መስጠትና ትችት ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ከነዚህ ዓለማቀፍ የዴሞክራሲ ደረጃ አውጭ ድርጅቶች መካከል Polity IVVanhanen’s Index of Democracy እና The Economist Intelligence Unit (EIU) ወዘተ የሚያወጧቸው ዓመታዊ ሪፖርቶች በብዙ አካዳሚያዊ ዓለም እንደ ዋነኛ ምንጭነት እየተጠቀሱ የብዙ ጥናታዊ ጽሑፎች ግብዓት በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሪፖርቶችም ሆኑ ብዙ ምሁራን ከሁሉ በላቀ የሀገራትን የዴሞክራሲ የዕድገት ደረጃ እንደ አሜሪካዊው ድርጅት ፍሪደም ሃውስ (Freedom House) በታማኝነት (ዴቪድ ካምቤል እንዳሉት)፣ በብቃት (EIU በዓመታዊ ሪፖርቶቹ እንደሚገልፀው)፣ በቀዳሚነትና በተመራጭነት (ፍራንሲስ ፉኩያማ እንዳሉት) እና በአስደናቂ ሁኔታ (ፋሪድ ዘካሪያ እንዳሉት) ለረጅም ጊዜ በግልፅነት እያስቀመጠ ያለ ድርጅት የለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሃገራትን የዴሞክራሲ ደረጃ ለመለካትም እንደ ፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ‘Freedom in the World’ ያለ መመዘኛ ማግኝት ከባድ ነው፡፡

የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ልክም ለመመዘን ከዚሁ ከፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ‘Freedom in the World’ አንወጣም፡፡ ነገር ግን ይሄን መመዘኛ ስንጠቀም አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንደ ቀድሞው ወታደራዊ መንግሥት ሁሉ ‹ፍሪደም ሃውስ የራሱን አጀንዳ ይዞ በሃገራችን [የቀለም] አብዮት ለማስነሳት ይጥራል› በማለት እንደሚከሰውና በውጤቱም ሊስማማ እንደማይችል እየታወቀ ነው፡፡ እንዲያውም የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊና ዘጠኝ ጓደኞቹ ላይ ‹በፍሪደም ሃውስ የሽብርተኝነት ድርጊት ሥልጠና ወስዳችኋል› የሚል አስገራሚ ክስ መቅረቡ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሒደት ለመመዘን የፍሪደም ሃውስን ዓለማቀፍ መመዘኛ የተጠቀምኩት በተለያዩ ምክንያቶች ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ፡

1. መመዘኛው ‘peer reviewed ጥናት ከመሆኑም ሌላ አንድ ጥናት ሊያሟላ የሚገባውን ገለልተኝነት፣ ግልፅነትና አጠቃላይ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑ፣

2. ላለፉት 45 ዓመታት (በኢትዮጵያ ደረጃ የሦስት መንግሥታትን የዴሞክራሲ ሪከርድ ማለት ነው) በዝርዝር ሁኔታ የተለያዩ ሀገራትን ሪከርድ በመመዝገብ ደረጃ የሚሰጥ በመሆኑ (ከፍሪደም ሃውስ በተሻለ ለዚህን ያህል ጊዜ የዴሞክራሲ መረጃ የያዘ ሌላ ተቋም አለ ማለት ይከብዳል)፣

3.  የዴሞክራሲ መለኪያ መስፈርቶቹ ግልፅና ውጤቱም ከነዝርዝሩ ግልፅ የሚደረጉ መሆኑ፣

4. ምዘናው በዋናነት ከተፃፉ ሕጎች ይልቅ መሠረት የሚያደርገው በተግባር ዜጎች ያሏቸውን ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመሆኑና

5. የፍሪደም ሃውስ መለኪያ መሥፈርቶች መሠረታቸው በ1948 በወጣው የዓለም አቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) ሲሆን፤ ኢትዮጵያም የዚሁ ድንጋጌ ፈራሚ አባል እና ባለፉት ሦስት ሕገ መንግሥቶቿም የድንጋጌውን ዋነኛው መብቶች ያካተተች መሆኑ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ፍሪደም ሃውስ ከ1972 (ከዚህ በታች ያለው የዘመን አቆጣጠር እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር ነው) ጀምሮ በከፍተኛ ትጋት የሁሉንም የዓለም ሀገራት የዴሞክራሲ ሪከርድ ፖለቲካዊ መብቶች (Political Rights) እና የሲቪል መብቶች (Civil Liberties) በሚሉ ሁለት መስፈርቶች በመክፈል፤ የፖለቲካ መብቶችን በአስር መጠይቆች እንዲሁም የሲቪል መብቶችን በዐሥራ አምስት መጠይቆች በመመዘን ከአንድ እስከ ሰባት ባሉ ደረጃዎች ይመድባል፡፡ (እያንዳንዱ ደረጃዎች ምን ማለት እንደሆኑ እዚህ ላይ መመልከት ይችላሉ) በዚህም መሠረት አንድ ያመጣ ሀገር ነፃና ዴሞክራሲያዊ ሀገር ሲሆን ሰባት ያመጣ ሀገር ደግሞ ጨቋኝ እና አፋኝ ስርዓት ያለበት ሀገር ነው ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ወደ አንድ የተጠጉ ሀገራት ዴሞክራሲያዊና ለዜጎቻቸው መልካም የሆኑ ስርዓቶች ያሉባቸው ሲሆን፤ ወደ ሰባት የተጠጉት ደግሞ ኢ-ዴሞክራሲያዊና ለዜጎቻቸው ጭቆናን ያሸከሙ ስርዓቶች ያሉባቸው ሀገራት ናቸው፡፡ አጠቃላይ ምደባውም ነፃ/ዴሞክራሲያዊ (Free)፣ ከፊል ነፃ/ዴሞክራሲያዊ (Partly Free) እና ነፃ ያልሆነ/ኢ-ዴሞክራሲያዊ (Not Free) በሚሉ ሦስት መደቦች ይመድባል፡፡

የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ከፍታና ዝቅታም ከዚሁ የፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ሪፖርት አንፃር ስንፈትሸው፤ ፍሪደም ሃውስ የዴሞክራሲ ደረጃውን ማውጣት በጀመረበት 1972 የኢትዮጵያ ተማሪዎች ከዐሥር ዓመት የሚበልጥ እንቅስቃሴ ፍሬ በማፍራት ላይ የነበረ ሲሆን፤ የዘውዱ ስርዓትም ለመውደቅ እየተንገዳገደ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡

ፍሪደም ሃውስ ሪፖርቱን ማውጣት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የዘውዱ ስርዓት የቆየው ለሦስት ዓመታት ሲሆን በነዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ ከውጭና ከውስጥ በነበረበት ጫና ትንሽ ላላ የማለት አዝማሚያ በማሳየት በሦስቱ ዓመታት ውስጥ በፖለቲካዊ መብቶች ረገድ በ1972 እና በ1973 ያስመዘገበው 5 ሲሆን፣ በሲቪል ነፃነት ረገድ ደግሞ በነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ 6 አስመዝግቧል፡፡ በቀጣዩ 1974 በተገላቢጦሽ በፖለቲካ መብቶች ዙሪያ 6 በማምጣት ያሽቆለቆለ ሲሆን በሲቪል መብቶች ረገድ ደግሞ በማሻሻል 5 ነጥብ አስመዝግቧል፡፡ ይሄም የዘውዱን ስርዓት ከጨቋኝ አምባገነናዊ ስርዓት የሚያስመድበው ሁኖ አልፏል፡፡


በፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ልኬት አንፃር የዘውዱ ስርዓት የመጨረሻ ዓመታት የዴሞክራሲ ደረጃ

የዘውዱን ስርዓት የተካው ወታደራዊው መንግሥት በዴሞክራሲ ረገድ በ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› ልፈፋ እየተመራ በ1975 እና በ1976 ከንጉሡም ስርዓት በባሰ ወደ ታች በመውረድ በማምራት  7 ነጥብ በማስመዝገብ ፍፁም አምባገነንነቱን ማረጋገጥ ጀምሮ (በዚህ ጊዜ ውስጥ በሲቪል መብቶች ዙሪያ 6 ነጥብ አስመዝግቧል)፤ አቢዮቱ ‹ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት› በተሸጋገረበት 1977 ፍፁም አምባገነናዊነቱን በሚያሳይ መልኩ ዴሞክራሲን አርቆ በመቅበር በፖለቲካም ሆነ በሲቪል ነፃነቶች ረገድ የመጨረሻውን 7 ነጥብ አስመዝቧል፡፡


በፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ልኬት አንፃር የወታደራዊው ስርዓት የ17 ዓመታት የዴሞክራሲ ደረጃ

ወታደራዊው መንግሥት ለቀጣዮቹ ዐሥራ አንድ ዓመታት (ከ1977 – 1987) ዓለም ላይ የመጨረሻውን ደረጃ በመያዝ በፖለቲካዊ መብቶችም ሆነ በሲቪል ነፃነቶች ዙሪያ ዝቅተኛውን 7 ነጥብ አስመዝግቦ በመቀጠል፤ የ1987ቱን ሕገ መንግሥት ተከትሎ በ1988 እና በ1989 በፖለቲካዊ መብቶች ረገድ ትንሽ ተሻሽሎ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት 6 ነጥብ አስመዝግቦ በሥልጣኑ የመጨረሻ ዘመን 1990 ተመልሶ ወደ መጨረሻው 7 ነጥብ በማሽቆልቆል ዙፋኑን ተገዶ አስረክቧል፡፡ ወታደራዊው መንግሥት በዴሞክራሲያዊነቱ ላይ ይቀርቡበት የነበሩትን ተቃውሞዎች አንዴ ‹ዴሞክራሲያዊ መብት ለጭቁኖች አሁኑኑ ማለት ትጥቅ አስፈቺ መፈክር ነው› (አዲስ ዘመን፣ ጥር 1970) እያለ፣ ሌላ ጊዜ ሌኒናዊውን ‹የጭቁኖች ዴሞክራሲ ከጭቁኖች አምባገነንነት ተለይቶ አይታይምን› በአደባባይ እያተጋባ (አዲስ ዘመን፤ ታሕሳስ 1970)፣ ሲያሻው ‹የአሁኑ ዓለም የዴሞክራሲ ጥያቄ የቀኝ መንገደኞች ሸፍጥ ነው› (አዲስ ዘመን ሕዳር፣ 1970) በማለት በግርድፉ ዴሞክራሲን የምዕራቡ ዓለም ሃሳብና ሴራ አድርጎ በማቅረብ ለትክክለኛ የመብትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ቅንጣት ታክል ጥረት እንኳን ሳያደርግ በማያስቆጭ ሁኔታ ከሥልጣን ተወግዷል፡፡

ወታደራዊውን ስርዓት በኃይል አስወግዶ ወደ ሥልጣን የመጣው ኢሕአዴግ በሽግግሩ ዘመኑ (1991 - 1994) ወቅት ከወታደራዊው ስርዓት በተሻለ ሁኔታ ከተጠበቀው ያነሰ ቢሆንም (ከሶሻሊስቱ ዓለም ሽንፈት ጋር ተያይዞ ጊዜው ዓለም ላይ ዴሞክራታይዜሽን ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተስፋፋ የነበረበት ወቅት በመሆኑ) የተሻለ ሆኖ በመገኘት በፖለቲካዊ መብቶች ረገድ 6 ነጥብ በማስመዝገብ በሲቪል ነፃነቶች ዙሪያ ደግሞ 4 እና 5 ነጥቦችን አስመዝግቦ አጀማመሩን ያሳመረ ሲሆን፤ ይህ አካሔድ ተሻሽሎ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መፅደቅን ተከትሎ ባሉት ሦስት ዓመታት (1995 – 1997) በፖለቲካዊ መብቶች ዙሪያ 4 ነጥብ በማስመዝገብ፤ በሲቪል ነፃነቶች ደግሞ በሽግግሩ ጊዜ የነበረውን የ5 ነጥብ ውጤት ይዞ ቀጥሏል፡፡ ይህ ሂደት ቀጥሎ በ1998 በ45 ዓመታት የዴሞክራሲ ሂደት ውስጥ በጣም ጥሩ የሆነውን በፖለቲካዊም በሲቪል ነፃነቶች 4 ነጥብ አስመዝግቧል፡፡


በፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ልኬት አንፃር የኢሕአዴግ የ25 ዓመታት የዴሞክራሲ ደረጃ

ነገር ግን ይህ ሂደት ብዙም ሳይቆይ ከ1999 እስከ 2009 ባሉት ጊዜያት በፖለቲካዊም ሆነ በሲቪል መብቶች ረገድ መጀመሪያ ካሳያቸው በጎ ዝንባሌዎች በመውረድ 5 ነጥብ ያስመዘገበ ሲሆን፣ የዚህ ማሽቆልቆል ሳያንስ ከ2010 ጀምሮ እስከ 2015 ድረስ በሁለቱም ጎራዎች (በሲቪልም ሆነ በፖለቲካዊ መብቶች) አሽቆልቆሎ ወደ 6 ነጥብ ወርዷል፡፡ ይሄም ኢሕአዴግ በሥልጣን ዘመኑ የመጀመሪያ ዘመናት ላይ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ ይመራል ተብሎ ተጥሎበት የነበረው ተስፋ በገመምተኝነት ቆይቶ አሁን እንደ ቀደምቱ ስርዓቶች ወደ ፍፁማዊ ጭቆና ስርዓትነት ራሱን አውርዷል፡፡

ይህ ውጤት ምን ይነግረናል?

ከላይ ያየነው ምዘና እና ውጤት በዋናነት አሁን ስላሉ የዴሞክራሲ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ምን ይነግረናል? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድደን ሲሆን፤ ከላይ በግርድፉ ያቀረብነው መረጃ በተለያየ ዓይን ስናየው የተለያዩ እውነታዎችን ይነግረናል፡፡

‹ኢሕአዴግ ራሱን ካለፉት ስርዓቶች ጋር እያወዳደረ ዴሞክራሲያዊ ነኝ ከሚል ለምን ከሌሎች ሀገራት ጋር አወዳድሮ አይነግረንም?›

የሚለው ጥያቄ በብዙ ሰዎች ዘንድ ሁሌም ‹ኢሕአዴግ አስከፊውን የደርግ መንግሥት ገርስሼ …› ማለት ሲጀምር የሚሰጥ አስተያየት ነው፡፡ ነገር ግን ከላይ ባየነው ዳታ መሠረት በዴሞክራሲያዊነት ረገድ የኢሕአዴግ ልጆች ‹መረረን› ብለው ከጠሉት የዘውድ ስርዓትና ሊፋለሙ በርሃ ከወረዱበት ‹ወታደራዊ መንግሥት ይሻላሉን?› ለሚለው ጥያቄ መልሳችን አሉታዊ ነው፡፡ ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት (ከ2013 – 2015) ያስመዘገበችው የዴሞክራሲያዊነት ውጤት (በፖለቲካዊ መብቶችም ሆነ በሲቪል ነፃነት ረገድ 6 ነው ያስመዘገበችው) ኢትዮጵያ በዘውዱ አገዛዝ የመጨረሻ ዓመታት (1972 – 1974) ካስመዘገበችው ውጤት (በፖለቲካዊ መብቶችም 6 እንዲሁም በሲቪል ነፃነት ረገድ 5 ነበር ያስመዘገበችው) ያነሰ እንዲሁም ከወታደራዊው መንግሥት ጋር ተቀራራቢ/እኩል የሆነ የዴሞክራሲ ደረጃን ነው፡፡


በሌላ በኩል የኢሕአዴጓን ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለውን የዴሞክራሲያዊነት ልክ ስናነፃፅረው እጅግ አሳፋሪ ውጤት ላይ ያደርሰናል፡፡ የ2015ን ምዘና ብቻ እንኳን ብናየው የዛሬዋ ኢሕአዴግ እያስተዳደራት ያለችው ኢትዮጵያ ኢሕአዴግ አርዓያና አጋር የሆነው የቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ከሚያስተዳድራት ቻይና ቀጥላ እንዲሁም የፑቲኗን ሩስያ በሶስተኝነት አስከትላ በዓለም ላይ ብዙ ሕዝብ የሚኖርባት ሁለተኛዋ አምባገነን ሀገር (The second largest dictatorship) ሁና እናገኛታለን፡፡ በሌላ አነጋገር ሕንድ በዓለም ትልቋ ዴሞክራሲ (ከሕዝብ ቁጥር አንፃር) ነች እንደምነለው ሁሉ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በዓለም ላይ ሁለተኛዋ ኢ-ዴሞክራሲ ነች እንደማለት ነው፡፡ ይህ በፍፁም ደስ የሚል ሪከርድ አይደለም፡፡

በፍሪደም ሃውስ ዓመታዊ ልኬት አንፃር የኢትዮጵያና የጋና የዴሞክራሲ ዕድገት በንፅፅር

በአጠቃላይ ኢሕአዴግ ከሌሎች ሀገራት (በተመሳሳይ አጀማመር የጀመሩትን የኢትዮጵያንና ጋናና የዴሞክራሲ ሂደት በንፅፅር መመልከት እንችላለን) ብቻ ሳይሆን ካለፉት የኢትዮጵያ ስርዓታት ጋርም ቢሆን ራሱን ቢያወዳድር ዞሮ ዞሮ ከላይ ከደረስንበት መደምደሚያ ላይ መድረሳችን አይቀርም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ መች የመዳን ተስፋ ያያል? መችስ በጠና ይታመማል?

ምንም እንኳን ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም፤ ከላይ የቀረበውን መረጃ ተመልክተን ኢትዮጵያ ውስጥ ለዜጎች በዴሞክራሲ ረገድ ምቹ የሚሆነው ጊዜና አስከፊ የሚሆነው ወቅትስ የትኛው ነው? ለሚለው ጥያቄ በግርድፉም ቢሆን ምላሽ መስጠት ያስችለናል፡፡ የውጤቱን ከፍታና ዝቅታ ተመልክተን ለዴሞክራሲ ምቹ የሆኑት ጊዜያት በዋናነት የሽግግር ጊዜያት (ለምሳሌ 1972 – 1974 ያሉት ጊዜያት)፤ እንዲሁም ሀገሪቱ አጠቃላይ ትኩረቷን ወደ ሌላ ጉዳይ (ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት - 1998 እና ተከታዮቹ ዓመታት) እንደሆኑ የሚታይ ሲሆን፤ ጭቆናውና የዴሞክራሲ እጦቱ ደግሞ የሚባባሰው ሥልጣን ሙሉ ለሙሉ በአንድ ሰው እጅ በምትገባበት ጊዜ ሁኖ እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ ኮሎኔል መንግሥቱ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ወደ ሞት አሰናብተው ሊቀመንበር ከሆኑበት 1977 ጀምሮ እስከ ደርግ ውድቀት ጊዜ ድረስ እንዲሁም መለስ ዜናዊ የውስጥ ጠላቶቻቸውን በግምገማ ጠራርገው - ተቃዋሚዎቻቸውን ደግሞ ከአደባባዩ ጠራርገው ካስወገዱበት ከ2010 በኋላ ያለው ጊዜ ማንሳት እንችላለን፡፡ ይሄም ዴሞክራሲ ስርዓታቱ ሥልጣንን እስኪያጠናክሩ ድረስ ትንፋሽ መያዣ (buffer) ሐሳብ እንጅ በዘላቂነት እንደ ሕልም ሲይዙት ያልነበረና አሁንም ያልያዙት መሆኑን ነው፡፡

ዴሞክራሲስ በኢትዮጵያ ተቀልብሷል?

ኢትዮጵያን ከአርባ ዓመታት በላይ ያጠኑትና በቅርቡ በሞት የተለዩት ኖርዌጅያኑ ሴግፍሬድ ፓውስዋንግ በ2004 በጻፉት “Aborted or nascent Democracy? Structural reasons for the failure of democratization in Ethiopia” የተባለ ጽሑፋቸው በኢትዮጵያ የተካሔዱትን ምርጫዎች ገምግመው ‹ኢትዮጵያ በቀዝቃዛው ጦርነት ማግስት ያገኘችውን ‹ዴሞክራሲያዊ› የመሆን ዕድል ለዲሞክራሲ አስፈላጊ የሆነውን የተቋማት (institutions) ግንባታ ማካሔድ ሳትችል በመቅረቷ ተጀምሮ የነበረው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ የመሆን ጉዞ ተቀልብሷል› ብለው ነበር፡፡ ፓውስዋንግ ይሄን ከጻፉ በኋላ ኢትዮጵያ ሦስት ‹ምርጫዎችን› ያካሔደች ብትሆንም ፓውስዋንግ ከታዘቧቸው ሁለት ምርጫዎች በባሰ መልኩ ሄዶ ሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ በአንድ ፓርቲ እጅ ስር ወድቃለች፡፡ ፓውስዋንግ ከዐሥራ አንድ ዓመታት በፊት ‹ያለ ተቋም ዲሞክራሲ የለም› በማለት የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ መቀልበሱን የነገሩን ሲሆን አሁን ደግሞ ዴሞክራሲ መንፈሱ እንኳን የተሰደደ ይመስላል፡፡ ከላይ ባየነው መረጃ መሠረትም ኢሕአዴግ በ1990ዎቹ ያስመዘገበውን የራሱን የዴሞክራሲ ከፍታ ቁልቁል ገፍቶ አሁን ከዘውዱ አገዛዝ የመጨረሻ ዘመናት እንኳን ባነሰ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ይህ በመግቢያችን የጠቀስናቸው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ‹fledgling democracy› ካሉት በተቃራኒው የሆነ እውነታ ነው፡፡ ታዲያ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ተቀልብሷል ማለት ያንሳል እንዴ?

ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁን ያለው የዴሞክራሲ ቅልበሳ (democratic reversal) ለተንታኞች አስቸጋሪ መሆኑ አልቀረም፡፡ የዴሞክራሲ መጠናከር (democratic consolidation) እና የዴሞክራሲ ቅልበሳ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ‹ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ከፓርላማዊ ስርዓት በባሰ መንገድ በቀላሉ የዴሞክራሲ ቅልበሳ ያጋጥመዋል› እንዲሁም ‹ለዴሞክራሲ ቅልበሳ ዋነኛው ምክንያት ደካማ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው› በማለት ሃሳባቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ፓርላማዊ ስርዓት ዘርግቻለሁ ባለችበት እና የኢኮኖሚ ዕድገቴ ከዓለም ቀዳሚ ነው በምትልበትና አንዳንድ ዓለማቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ ‹እውነት› ነው ባሉበት ጊዜ ይህ ቅልበሳ ሲያጋጥም ፓርላማዊ የተባለው ስርዓትን እውነተኛነት (genuineness) መጠራጠራችን አይቀርም፤ እንዲሁም አወዛጋቢውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጉዳይ የበለጠ እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡

‹ግን እኮ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት አለ›

ኢሕአዴግ ስለዴሞክራሲ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ‹ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሕገ መንግሥት ቀርፀን በተግባር ላይ አውለናል፤ የዘመናት ጭቆናም ከሕገ መንግሥታችን መፅደቅ ጋር ተያይዞ ላይመለስ ተወግዷል› ይላል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ምንጭ በማድረግ የፍሪደም ሃውስን ዓመታዊ ሪፖርት ለመጠቀም የተፈለገበት አንዱ ምክንያት መለኪያው በዋናነት ትኩረቱ የተጻፉ ሕጎች እና መብቶች ላይ ሳይሆን የመብቶች ተግባራዊነት ላይ መሆኑን ከላይ የጠቀስን ሲሆን፤ ውጤቱም በተግባራዊነት ረገድ ኢሕአዴግ ካለፉት ስርዓቶች ያልሸሸ መሆኑን ማየት ያስችለናል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ካሉት 106 አንቀፆች መካከል 31 የሚሆኑት ስለ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚደነግጉ ናቸው፡፡ ይሄ በጣም የሚያስደስት ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የተሻሻለው የዘውዱ ስርዓት ሕገ መንግሥትም (1955) ከነበሩት 131 አንቀፆች መካከል 29 የሚሆኑት፤ እንዲሁም የ1987 የኢሕዴሪ ሕገ መንግስት ከነበሩት 119 አንቀፆች መካከል 28 የሚሆኑት ስለ ዜጎች ሰብኣዊና ዴሞክራሲያው መብቶች የሚደነግጉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሦስቱም ስርዓቶች ሕገ መንግሥታዊነት (constitutionalism) በሌለበት ሕገ መንግሥት ምንም እንደሆነ ነው የሚያስረዱን፡፡

ከላይ እንደጠቀስነው 1998 ኢትዮጵያ በ45 ዓመታት የዴሞክራሲ ታሪኳ መልካም ውጤት ያሳየችበት ዓመት ነበር፡፡ በዓመቱ የመጀመሪያ ወራት ደግሞ መቀመጫውን ኒው ዮርክ ያደረገው የፎሪን አፌርስ ጆርናል በዳን ኮኔል  በፍራንክ ስሚዝ የተፃፈ ‹Africa’s New Bloc› የተባለ ጽሑፍ አስነብቦ ነበር፡፡ ጽሑፉ በዋናነት ‹የአፍሪካ የጨለማው ዘመን እያበቃ ነው፤ ዴሞክራሲ በአፍሪካ ማበብ ጀምሯል ለዚህም ተግባር አዲሱ የአፍሪካ የመሪዎች ትውልድ (የኢትዮጵያው መለስ፣ የኤርትራው ኢሳያስ፣ የዩጋንዳ ሙሴቬኒ እንዲሁም የሩዋንዳው ካጋሜ) ሊመሰገን ይገባል› በማለት አብስረው ነበር፡፡ ከዚህ ጽሑፍ በኋላ በመጋቢት 1998 ‘Democracy in Africa: The New Generation of African Leaders’ በሚል ርዕስ በአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ ‹ሂሪንግ› ቀርቦ ነበር፡፡ በሂሪንጉ ወቅት በጊዜው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ የነበሩት ዶ/ር  ሱዛን ራይስ  ስለ አዲሱ የአፍሪካ የመሪዎች ትውልድ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡ ሲሆን ከጥያቄዎቹ አንዱ ለሆነውና በሚዙሪው ሴናተር እና በሂሪንጉ መሪ ጆን አሽክሮፍት ለቀረበላቸው ‹ለመሆኑ እነዚህ አዳዲስ መሪዎች ከሀገራቸው ውጭ ያላቸው ተፅዕኖ ምን ያክል ነው? ከአሜሪካስ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን ይመስላል?› ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ፡
Let me mention in particular in this regard Prime Minister Meles of Ethiopia, President Isaias of Eritrea, and President Museveni of Uganda. These leaders have come together with a vision for not only Eastern and Central Africa, but the continent as a whole, that we largely support. It is a vision of self reliance, of sustained economic growth and prosperity, and of a sustainable form of democracy that takes into account the particular histories of individual countries but does not compromise on fundamental principles of respect for human rights.

በማለት ነበር የመለሱት፡፡ ሱዛን ራይስ ይሄን ባሉ በሁለት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያና ኤርትራ እስከ ዛሬ ድረስ ያላለቀውን ጦርነት ጀምረው ብዙ እልቂት ተከስቷል፡፡ ሱዛን ‹ዘላቂ የዴሞክራሲ ችግኝ ተክለዋል፤ ለአፍሪካም ምሳሌ ሁነዋል› ቢሏቸውም፤ ኤርትራም ወደ አዘቅት ወርዳለች የኢትዮጵያም የዴሞክራሲ ጉዞ ዘላቂ መሆን አይደለም ያለውን እንኳን ማስጠበቅ አቅቶት አፈር መልበሱን እያየን ነው፡፡

ሲጠቃለልም የመሪ ግለሰቦች ስሜት በፖሊሲነት ሲመራው የነበረውና እየመራው ያለው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ‹መሪዎቻችን› የሚምሉበት የተቀደሰ ቃል ከመሆን አላለፈም፡፡ የግማሽ ምዕተ ዓመት የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞም በዜሮ ተባዝቶ ዛሬ ብዙ ነገሮች እያስፈሩ ሄደዋል፡፡ ተስፋ እንዳናደርግ ደግሞ አዳዲስ ቀናት አዳዲስ መከራን እንጂ ዴሞክራሲያዊነትን ይዘው እየመጡ አይደለም፡፡

1 comment:

 1. Good morning, how are you?

  My name is Emilio, I am a Spanish boy and I live in a town near to Madrid. I am a very interested person in knowing things so different as the culture, the way of life of the inhabitants of our planet, the fauna, the flora, and the landscapes of all the countries of the world etc. in summary, I am a person that enjoys traveling, learning and respecting people's diversity from all over the world.

  I would love to travel and meet in person all the aspects above mentioned, but unfortunately as this is very expensive and my purchasing power is quite small, so I devised a way to travel with the imagination in every corner of our planet. A few years ago I started a collection of used stamps because through them, you can see pictures about fauna, flora, monuments, landscapes etc. from all the countries. As every day is more and more difficult to get stamps, some years ago I started a new collection in order to get traditional letters addressed to me in which my goal was to get at least 1 letter from each country in the world. This modest goal is feasible to reach in the most part of countries, but unfortunately, it is impossible to achieve in other various territories for several reasons, either because they are very small countries with very few population, either because they are countries at war, either because they are countries with extreme poverty or because for whatever reason the postal system is not functioning properly.

  For all this, I would ask you one small favor:
  Would you be so kind as to send me a letter by traditional mail from Ethiopia? I understand perfectly that you think that your blog is not the appropriate place to ask this, and even, is very probably that you ignore my letter, but I would call your attention to the difficulty involved in getting a letter from that country, and also I don’t know anyone neither where to write in Ethiopia in order to increase my collection. a letter for me is like a little souvenir, like if I have had visited that territory with my imagination and at same time, the arrival of the letters from a country is a sign of peace and normality and an original way to promote a country in the world. My postal address is the following one:

  Emilio Fernandez Esteban
  Calle Valencia, 39
  28903 Getafe (Madrid)
  Spain

  If you wish, you can visit my blog www.cartasenmibuzon.blogspot.com where you can see the pictures of all the letters that I have received from whole World.

  Finally, I would like to thank the attention given to this letter, and whether you can help me or not, I send my best wishes for peace, health and happiness for you, your family and all your dear beings.

  Yours Sincerely

  Emilio Fernandez

  ReplyDelete