Wednesday, February 3, 2016

የአንድ ሰው ኃይል፤ በአንዲት ሴት ገድል ሲፈተሽበበፍቃዱ ኃይሉ

አንድ ሰው ብቻውን የሚወስደው እርምጃ፣ እሺታው ወይም እምቢታው ለብዙኃን ለውጥ ያመጣ ይሆን?

ልክ የዛሬ 97 ዓመት (ጥር 26፣ 1905) አላባማ/አሜሪካ ውስጥ ሮዛ ፓርክስ ስትወለድ፣ ከ97 ዓመት በኋላ እና ከትውልድ አገሯ ብዙ ሺሕ ማይሎች እና ሦስት ትውልዶች በላይ ርቄ የምገኘው እኔ ታሪኳን በጨረፍታ ለመጻፍ የኮምፒዩተር የቁልፍ ሰሌዳ እንደምነካካ ማን ሊገምት ይችላል? የአንዲት ነጠላ ሮዛ፣ የአንዲት ነጠላ ቀን፣ ነጠላ እምቢታዋ ግን ይህንን የማይገመት ታሪክ ሊፈጥር ችሏል፡፡

ሮዛ ፓርክስ የዛን ዕለት “እምቢ” ባትል ኖሮ፣ ምናልባትም የጥቁሮች የሲቪል መብቶች ትግል ባልታወቀ አቅጣጫ ሊጓዝ ይችል ነበር፡፡ ምናልባትም ደግሞ ዛሬ በሠላማዊ ታጋይነቱ አርኣያ የምናደርገው ማርቲን ሉተር ኪንግ (ትንሹ) ጭራሹን ይህንን መክሊቱን የሚያወጣበት አጋጣሚ ሳያገኝ ተድበስብሶ ያልፍ ነበር፡፡

ቀኑ ኅዳር 21፣ 1948 ነበር፤ ሐሙስ ዕለት፡፡ ጀምበር ስታዘቀዝቅ ሮዛ ከሥራዋ ወጥታ ወደቤቷ ለመሄድ የሞንቶጎምሪ ከተማ የሕዝብ አውቶቡስን ክሊቭላንድ ጎዳና ላይ ተሳፈረች፡፡ የአውቶቡሱ ሹፌር “እሱ በሚነዳው አውቶቡስ ሁለተኛ አልሳፈርም” ብላ የማለችለት ጄምስ ብሌክ መሆኑን ሮዛ አላወቀችም ነበር፡፡ ከ12 ዓመት በፊት ሮዛ፣ ጀምስ በሚነዳው አውቶቡስ ውስጥ ገንዘቧን ከፍላ በመሳፈር ለጥቁሮች በተከለለው ቦታ ሄዳ ስትቀመጥ፣ ‹የገባሽበት የፊተኛው በር የነጮች መግቢያ ነው ውጪና መልሰሽ በኋላ በር ግቢ› ሲላት “አላደርገውም” በማለት በዝናብ ውጪ ቆማ ጥሏት ሄዷል፡

የሞንቶጎምሪ ከተማ አውቶቡሶች በዘመኑ ሕግ መሠረት የአውቶቡስ ውስጥ መቀመጫዎች የጥቁሮች እና የነጮች ተብለው ተከፋፍለው ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ አራት መደዳዎች ለነጮች ብቻ የተከለሉ ናቸው፡፡ ለጥቁሮች ወደኋላ ላይ አንዳንድ ወንበሮች ይተዉላቸው ነበር፡፡ ምንም እንኳን 75 በመቶ የሚሆኑት ተሳፋሪዎች ጥቁሮች ቢሆኑም መሐል አካባቢ ያሉት ወንበሮች ነጮች የራሳቸውን መደዳ እስኪሞሉ ድረስ ጥቁሮች እንዲቀመጡ ይፈቀድ ነበር፡፡ በልምድ ግን የአውቶቡስ ውስጥ ተቆጣጣሪዎች ባሱ ውስጥ ያሉ ነጮች በሙሉ መቀመጫ እስኪያገኙ ድረስ ጥቁሮችን ከወንበራቸው ያስነሷቸው ነበር፡፡ ይህ ልምድ እና ኢፍትሓዊ ሕግ ግን ለእምቢ ባይዋ ሮዛ ፓርክስ እያደር የማይለመድ ነገር ነበር፡፡ ለሮዛ ፓርክስ በልጅነቷ አውቶቡሶች “የጥቁር” እና “የነጭ” ሁለት ዓለም መኖሩን ያረዷት የልዩነት ማሳያዎቿ ናቸው፡፡

ጄምስ ብሌክ ዝናብ ላይ ጥሏት ከሄደ ከ12 ዓመታት በኋላ ሹፌሩ እሱ መሆኑን ሳታውቅ ሮዛ ፓርክስ ጄምስ በሚያሽከረክራት አውቶቡስ ውስጥ ገባች፡፡ ለ“Colored” (ነጭ ያልሆኑ) ተሳፋሪዎች መቀመጥ የሚፈቀድላቸው ቦታ ላይ ሄዳ ተቀመጠች፤ ከሷ ሌላ ሌሎች ሦስት ጥቁሮችም እዚያው ተቀምጠዋል፡፡ ሌሎች ሁለት ነጮች ባሱ ከሞላ በኋላ ገቡ እና ቆሙ፡፡ ጀምስ ብሌክ መጥቶ “Colored” የሚል ምልክት ያለበትን ተንቀሳቃሽ መጠቆሚያ ወደኋላ አንቀሳቀሰውና ሮዛ ፓርክስና ሌሎቹ ጥቁሮች ለነጮቹ ወንበራቸውን እንዲለቁ ጠየቃቸው፡፡ ሮዛ ፓርክስ ያንን ቅፅበት ከዓመታት በኋላ ስታስታውሰው እንዲህ ነበር ያለችው፤

“When that white driver stepped back toward us, when he waved his hand and ordered us up and out our seats, I felt a determination cover my body like a quilt of a winter night.” (“ያ ነጭ ሹፌር ወደእኛ መጥቶ ከወንበራችን ሊያስነሳን እጆቹን እያወናጨፈ ሲያዘን፣ የቁርጠኝነት ስሜት ልክ እንደክረምት ድሪቶ እላዬ ላይ ሲከመር ነው የተሰማኝ፡፡”)

“ተነሱ” ለሚለው ትዕዛዝ ሌሎቹ ሦስት ጥቁሮች በእሺታ ወንበራቸውን ለቀቁ፡፡ ሮዛ ፓርክስ ግን በመነሳት ፈንታ ወደመስታወቱ ጥግ ወዳለው ወንበር ፈቀቅ አለች፡፡

ጄምስ፤ “አንቺስ ለምንድን ነው የማትነሺው?”

ሮዛ፤ “መነሳት ያለብኝ አይመስለኝም፡፡”

ጄምስ፤ “የማትነሺ ከሆነ ፖሊስ ጠርቼ ነው የማስጠረንፍሽ!”

ሮዛ፤ “ያንን ማድረግ ትችላለህ፡፡”

ጄምስ ብሌክ ፖሊስ ጠራ፤ ታሰረች፡፡ ፖሊሱ ሮዛ ፓርክስን ወደማቆያ ቤት እየወሰዳት እያለ የተወሰኑ ቃላት ተለዋወጡ፡፡

ሮዛ፤ “ለምን እንዲህ ትገፉናላችሁ?”

ፖሊሱ፤ “አላውቅም፤ ግን ሕግ ሕግ ነው፡፡ እናም በቁጥጥር ስር ውለሻል፡፡”

ያንን ሁኔታ ስታስታውስ ሮዛ እንዲህ ትላለች፤ “እንደታሰርኩ ሳውቅ፣ ከዚያ በኋላ በእንደዚያ ዓይነቱ ውርደት የምሳፈርበት የመጨረሻው ጊዜ የዛን ዕለቱ እንደሆነ እርግጠኛ ሆንኩ፡፡”

ሮዛ ፓርክስ “እምቢ” ስትል መንገላታት እንደሚከተል ጠፍቷት አልነበረም፡፡ የሚያሳስባት ኑሮ ስላልነበራትም አልነበረም፡፡ እንዲያውም ጥሩ ሥራ ያላት፣ ባለትዳር እና የልጆች እናት የሆነች የ42 ዓመት ጎልማሲት ነበረች፡፡ ሮዛ ፓርክስ በኋለኛው ዘመኗ ልዩ ክብርና ዝና ብትቀዳጅም በወቅቱ ግን፣ በዚያች እርምጃዋ ብዙ ተገፍታለች፡፡ ከልብስ ሰፊነት ሥራዋ ተባርራለች፡፡ የግድያ ዛቻም ደርሶባት ያውቃል፡፡ እምቢተኝነቷ አስከፍሏታል፤ መልሶም በሰፊው ከፍሏታል፡፡

እምቢተኝነቶች ሁሉ ውጤታማ ላያደርጉ ይችላሉ፡፡ ሌሎች ጥቁሮችም ከዚያ በፊት እምቢ ብለዋል፡፡ እሷም ብትሆን ከዚያ ቀን በፊት በብዙ አጋጣሚዎች እምቢ ብላለች፡፡ እምቢተኝነቷ ግን እንደዚያን ዕለት ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖላት አያውቅም፡፡ ‹ያ ገጠመኝ ማንም በዚያ መንገድ ሊያናጥበኝ እንደማይገባ የማሳይበት ዕድል ነበር› ነው ያለችው የኋላ ኋላ ስትጠየቅ፤

“ለመታሰር አላቀድኩም፡፡ ሳልታሰር ብዙ መሥራት የነበሩብኝ ነገሮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ያንን ውሳኔ መወሰን ሲኖርብኝ፣ አላቅማማሁም፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን ነገር ከሚገባን በላይ ታግሰነዋል፡፡ እጅ በሰጠን ቁጥር፣ የበለጠ እንዋረዳለን፤ የበለጠ እንጨቆናለን፡፡”

ማርቲን ሉተር ኪንግ ስለዚያ እምቢተኝነቷ ቅፅበት በአውቶባዮግራፊው ላይ እንዲህ በማለት ነበር የጻፈው፤

“የትግስት ፅዋው ሞልቶ ሲገነፍል የሚመጣው ‹ከዚህ በላይ መታገስ አልችልም› የሚለው ስሜት ምን እንደሆነ የማይገባው ሰው የወይዘሮ ሮዛ ፓርክስን እርምጃ ሊረዳው አይችልም፡፡”

በወቅቱ ጉዳዩን የሰሙት፣ አባል የሆነችበት ለጥቁሮች ሕይወት መሻሻል የሚሠራ ማኅበር መሪዎች ኢ.ዲ. ኒክሰን እና ክሊፎርድ ደር ዋስ ሆነው አስለቀቋት፡፡ ከአራት ቀናት በኋላ ሮዛ ፓርክስ ፍርድ ቤት ቀርባ በሠላሳ ደቂቃ ውስጥ የ10 ዶላር ቅጣት የአካባቢ ሕግ በመተላለፍ እና የችሎቱን ወጪ 4 ዶላር እንድትከፍል ቅጣት ተበየነባት፡፡ ሮዛ በጀመረችው መንገድ ፀንታ ቅጣቱን በእምቢታ ይግባኝ በማለት ጥቁር እና ነጮችን ከፋፍሎ የሚመለከተው ሕግ ፍትሐዊ አይደለም በማለት ተሟገተች፡፡

ያንን አጋጣሚ ተከትሎ የሴቶች የፖለቲካ ካውንስል የተባለ ማኅበር የሞንትጎምሪ የከተማ አውቶቡሶች ውስጥ ጥቁሮች እንዳይሳፈሩ ጥሪ የሚያቀርቡ 35,000 በራሪ ወረቀቶችን አዘጋጅቶ ሮዛ ፍርድ ቤት የቀረበች ዕለት አሰራጨ፡፡ ዜናው ተሰራጨ፡፡ የዛን ዕለት እየዘነበ ነበር፤ ነገር ግን ጥቁሮች በአቋማቸው ፀኑ፡፡ አንዳንዶች በእግራቸው ከ10 ኪሎ ሜትሮች በላይ ተጓዙ፤ ጥቁሮች በሚነዷቸው መኪኖች ላይ ብቻ የተሳፈሩም ነበሩ፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ዕለቱን በከተማ አውቶቡሶቹ ሳይሳፈሩ አሳለፉ፡፡ የመሳፈር ዕቀባው ተሳካ፡፡ ነገር ግን ይህም በቂ ስላልነበር በወቅቱ የነበሩት አራማጆች ተሰብስበው ‹የሞንትጎምሪ ማሻሻያ ማኅበርን› መሠረቱ፡፡ ማኅበሩ ወጣቱን እና በወቅቱ እምብዛም የማይታወቀውን ማርቲን ሉተር ኪንግ ሊቀመንበር አድርጎ ይዞ መጣ፡፡

በማኅበሩ መሪነት በሞንትጎምሪ አውቶቡስ ያለመሳፈር አድማው ከ381 ቀናት በላይ ቀጠለ፡፡ የአውቶቡስ ኩባንያዎቹ ኪሳራ ተጋረጠባቸው፡፡ የከተማዋ አስተዳደር በመጨረሻ እጁን ሰጠ፡፡ ሕጉን ተገዶ አሻሻለው፡፡ በአሜሪካ የጥቁሮች የዕኩል መብት ትግል ውስጥ የሞንትጎምሪ የአውቶብስ አለመሳፈር አድማ ጉልህ ስፍራ አለው፡፡ አድማው ማርቲን ሉተር ኪንግንም ኮትኩቶ ያበቀለ የሠላማዊ ትግል “ኮሌጅ” ነው፡፡

ሮዛ ፓርክስ “ወንበሬን ለዘር መድልዎ አልለቅም” ስትል የመጀመሪያዋ አልነበረችም፤ ሌሎችም ከዚያ በፊት ሞክረውት ተድበስብሰው የቀሩ አሉ፡፡ ነገር ግን በኪንግ ቋንቋ “ፅዋው ሞልቶ ሲገነፍል” ከዚያ በፊት የሞከሩት እና እምቢታቸው ሰሚ ያጣው ሰዎች ጩኸት ሁሉ በሮዛ ፓርክስ እምቢታ ውስጥ ተስተጋብቷል፡፡ ሮዛ ፓርክስ “ጥያቄውን አቀጣጠለችው እንጂ አልጀመረችውም” ይላል ኪንግ፡፡ አሻራዋ ግን ዘመን፣ ርቀት እና ትውልድ ሳያግደው እያስተጋባ ይገኛል፡፡

የሮዛ ፓርክስ እና የጄምስ ብሌክ ሥም ይኸው እስከዛሬ ተያይዞ እየተነሳ ይገኛል፡፡ ሁለቱም ግለሰቦች ናቸው፡፡ የየግል ምርጫቸው ታሪክን በየፊናው ተጭኗል፡፡ እሷ የታሪክ ባለውለታ ስትሆን፣ እሱ የታሪክ ባለዕዳ ሆኗል፡፡ እሷ ጭቆናን እምቢ በማለቷ ስትታወስ፣ እሱ በደሉን በማስተባበሩ አብሯት ይታወሳል፡፡ የአንድ ሰው እርምጃ፣ ቢጻፍም ባይጻፍም፣ በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ መልኩ የራሱን አሻራ እያሳረፈ ማለፉን ይቀጥላል፡፡

የሮዛ ፓርክስ እና እንደርሷ ያሉ ፅኑዎች ታሪክ የአንድ ሰው ኃይልን እየዘከረ ይኖራል፡፡

No comments:

Post a Comment