Wednesday, April 6, 2016

ኢትዮጵያና የአስር ዓመታት የኢንተርኔት አፈና

በአጥናፉ ብርሃኔና በዘላለም ክብረት

ሐሙስ ጠዋት ግንቦት 10፣ 1998 መንግስታዊው የቴሌኮም ድርጅት የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ በጊዜው አሉኝ ካላቸው አንድ መቶ አስራ ሶስት ሽህ የኢንተርኔት ደንበኞቹ መካከል ጥቂቶቹ ከምርጫ 97 ማግስት የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ በተወሰደው አፈና ምክንያት አማራጭ እየሆኑ ከመጡት ጥቂት ጦማሮችና የዜና ድረ ገፆች ላይ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ለማየት ከኮምፒውተሮቻቸው ላይ በተደጋጋሚ ቢሞክሩም አብዛኞቹ ሊሰሩላቸው አልተቻላቸውም ነበር፡፡ በጊዜው  በአንድ ሌሊት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ከተዘጉት አስር ገደማ ጦማሮችና ድረ ገፆች መካከል አንዱ የሆነው ሰምና ወርቅ ጦማር ግንቦት 09፣ 1998 አመሻሹ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን ሰምና ወርቅ ጦማርን ጨምሮ ሌሎች ጦማሮችንና ድረ ገፆችን በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ማድረጉን ገልፆ ነበር፡፡

ይህ ከሆነ ከአስር ዓመታት በኋላ አያንቱ የተባለውና የኦሮሞ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚፅፈው ድረ ገፅ የካቲት 24፣ 2008 ባወጣው ፅሁፍ ምንም እንኳ እየጨመረ የመጣውን የአንባቢዎቹን ቁጥር ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ አቅሙን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ቢሆንም ከየካቲት 23፣ 2008 ጀምሮ ድረ ገፁ በኢትዮጵያ ውስጥ በድጋሚ እንዳይታይ መታገዱን ዘግቦ ፅፏል፡፡

የኢንተርኔት አፈናው (Internet Censorship) ከተጀመረ አስር ዓመታት ቢያስቆጥርም ትናንት ዛሬን፣ ዛሬ ደግሞ ትናንትን በእጅጉ ይመስላሉ፡፡

የአፈናው አፍሪካዊ ፈር ቀዳጅ

ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት አንፃር በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከዓለም ጭራ ሀገራት አንዷ እንደሆነች ዓለማቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት (International Telecommunication Union) በየዓመቱ የሚያወጣውን ሪፖርት ብቻ በመመልከት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሃያ አመታት ውስጥ ከሶስት በመቶ በላይ መሔድ ያልቻለው የኢትዮጵያዊያን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ሀገሪቱ በዚህ ዘርፍ ያለችበትን አሳዛኝ ሁኔታ የሚገልፅም ነው፡፡

ምንጭ፡ ዓለማቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት (International Telecommunication Union)
ነገር ግን በዚህ ትንሽ የተጠቃሚዎች ቁጥር ላይ ያለው ቁጥጥርና ክልከላ ሃገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ የበለጠ አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ከአስር ዓመታት በፊት በግንቦት 1998 የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ አመለካከታቸውን ያልወደዳቸውን ድረ ገፆች በሀገር ውስጥ እንዳይታዩ በማገድ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የመጀመሪያዋ የኢንተርኔት አፋኝ ሀገር  ያደረጋት ሲሆን፤ ዓለም ላይ ደግሞ ከቻይና እና ከሳኡዲ አረቢያ ቀጥሎ በሶስተኝነት የኢንተርኔት አፈናን በመጀመር የአፈናው ፈር ቀዳጅ ሁኗል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ሚንስትር የነበሩት አቶ ብርሃነ ሐይሉ  ሰጡት መልስ ‹በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታይ የተደረገ ምንም አይነት ድረ ገፅም ሆነ ጦማር የለም› የሚል ሲሆን፤ ይሄም ከእውነታው ጋር በግልፅ የሚጋጭ ነበር፡፡

ድረ ገፆቹ ለምን ይታፈናሉ?

የተለያዩ ሃገራት በተለያዩ ምክንያቶች አንዳንድ ድረ ገፆች በሀገራቸው እንዳይታዩ ያደርጋሉ፡፡ ከነዚህ ምክንያቶች ውስጥም ሐይማኖታዊና ግብረ ገባዊ ምክንያቶች (religious and moral reasons) የብዙ ሀገራት መነሻዎች ሆነው ይታያሉ፡፡ ሀገራት ‹አንድ ድረ ገፅ ሐይማኖቶችን ያጎድፋል፤ የሕብረተሰቡን ስነ ምግባር ደንብም ያውካል› በሚሉ ምክንያቶች የተለያዩ ድረ ገፆች በሀገራቸው ዜጎች እንዳይታዩ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ጥቂት አምባገነን መንግስታት በፖለቲካዊ ምክንያት የተቃውሞ ድምፀት ያላቸውን ድረ ገፆች በሃገራቸው ዜጎች እንዳይታዩ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው መንግስት ድረ ገፆቹን ለመዝጋት ምንም ያስቀመጠው ግልፅ ፖሊሲ ካለመኖሩም ሌላ በግልፅ የሚታወቀውን የኢንተርኔት አፈና የለም በማለት ሁሌም ይክዳል፡፡ ነገር ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ድረ ገፆችን ጦማሮች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ መደረጉ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፖለቲካ ቀመስ ድረ ገፅ   ሳይበር  ኢትዮጵያን ከሌሎች ዘጠኝ ድረ ገፆች ጋር ግንቦት 09/1998 በኢትዮጵያ እንዳይታዩ በማድረግ በየተጀመረው አፈና እያደገ መጥቶ ማንኛውንም በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚዘግብ ድረ ገፅ እስከ መዝጋት ድረስ ሂዷል፡፡ አፈናው ጣራ በነካበት  2005 በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን (የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ድረ ገፆች ተዘግተው የነበረ መሆኑን ልብ ይሏል) ድረ ገፆች ሳይቀር በሃገር ውስጥ እንዳይታዩ በማድረግ አይን ያወጣ አፈና ይካሄድ ነበር፡፡

ከዚህም ተነስተን በኢትዮጵያ ያለው መንግስት ዋነኛ የኢንተርኔት አፈና የሚያተኩረው ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ድረ ገፆች፣ ጦማሮች እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ አድራሻዎች ላይ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን፡፡ ይሄም በዋናነት መሰረት የሚያደርገው ዜጎች አማራጭ ሃሳቦችን እንዳይሰሙ በማድረግ እና የፖለቲካ ትርክቱን መቆጣጠርን ነው፡፡ የተለያዩ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ ተቋማትም ‹የአፈናው ዋነኛ መገለጫ ፖለቲካ ነው› በማለት በየዓመቱ በሚያወጧቸው ሪፖርቶች ይገልፃሉ፡፡


የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊዎች መጋቢት 27/2008 ባደረግነው ሙከራ ከላይ በምስሉ ለናሙና የተመለከቱትን http://aayyantuu.comhttp://ethsat.comhttp://gadaa.com እና http://zehabesha.com ጨምሮ ሌሎች ብዙ ድረ ገፆችን ጦማሮች በአዲስ መልክ በመዝጋት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ መደረጋቸውን ለመገንዘብ ችለናል
ነገር ግን አፈናዎቹ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ኢላማ ማድረጋቸው ደግሞ የአፈናው ሌላው ገፅታ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ድረ ገፆች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ በተደረገበት በግንቦት 1998 የአፈናው ዋነኛ ዓላማ የምርጫ 97 የፖለቲካ ትኩሳት ላይ ውሃ መቸለስ መሆኑ ግልፅ ነበር፡፡ አፈናው ለአምስት ዓመታት ብዙም ለውጥ ሳያሳይ ቀጥሎ በአረቡ ዓለም አቢዮት ማግስት ግን እጅግ በተጠናከረና ማህበራዊ ሚዲያዎችን ባካተተ መልኩ በ2004 እና በ2005 በመቶዎች የሚቆጠሩ ድረ ገፆችንና ጦማሮችን በማፈን ወደ አዲስ ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡ ይሄም እንግዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግስት ተመሳሳይ የለውጥ እንቅስቃሴ ይደረጋል የሚል ስጋት ይዞት እንደነበር ያሳያል፡፡

ምርጫ 2007 መዳረሻ ላይም እንዲሁ ድረ ገፆቹና የጦማሮቹ አፈና ከፍ ብሎ እንደነበር ጉዳዩን በቅርቡ የሚከታተሉ ዓለማቀፍ ተቋማት ዘግበውት ነበር፡፡ በቅርቡ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ከሕዳር ወር የጀመረውን ሕዝባዊ ተቃውሞ አስመልክቶ የተለያዩ ድረ ገፆችን በኢትዮጵያ እንዳይታዩ ከመደረጋቸውም በላይ፤ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊዎች በምስራቅ ሸዋ እና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ተንቀሳቅሰን ለማረጋገጥ እንደቻልነው ባለፉት አራት ሳምንታት ውስጥ ይሄ ፅሁፍ እስከተፃፈበት ጊዜ ድረስ በክልሉ ውስጥ መተግበሪያዎችን (Applications) ተጠቅሞ ድረ ገፆችን መጎብኝት እንዳይቻል ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም መጋቢት 21 እና 22/2008 ምሽት በመላው ሀገሪቱ ለተከታታይ አስር ሰዓታት እነዚህ መተግበሪያዎች ተጠቅሞ ድረ ገፆችን መጎብኝት አይቻልም ነበር፡፡ ይሄም የኢንተርኔት አፈናው እያደገ እና በቴክኖሎጅም በእጅጉ እየተራቀቀ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ከዚህ ተነስተን የምንደርስበት ድምዳሜም በኢትዮጵያ ያለው መንግስት መሬት ላይ ያለን ማንኛውንም አይነት የፖለቲካ ትኩሳት ለማዳፈን ሲባል የመረጃ ስርጭትን መገደብን እንደ ውጤታማ አካሔድ እየተጠቀመበት እንደሆነ ነው፡፡

ድረ ገፆቹን ማን ነው የሚዘጋቸው?

አስር ዓመታት ያስቆጠረው የኢንተርኔት አፈና እጅግ እየጠነከረና የተለያዩ ሰበቦችን እየያዘ ቀጥሏል፡፡ ከላይ እንደጠቀስነውም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግስት ይሄን ግልፅ አፈና እንኳን ለማመን አይፈልግም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የመንግስት ባለስልጣናት የሚሰጡትም ምላሽ ‹ቴክኒካል ችግር ሊሆን ይችላል እንጂ እኛ አልዘጋንም› የሚል ነው፡፡ ግልፅ የኢንተርኔት የሳንሱር ፖሊሲ በሌለበት (በመስከረም 2004 ወጣው ‹የኢፌዴሪ ሃገራዊ የኢንፎርሜሽን ደህንነት ፖሊሲ› በጉዳዩ ላይ ምንም የሚለው ነገር የለም) ሁኔታ ድረ ገፆቹና ጦማሮቹ በሀገር ውስጥ እንዳይታዩ የሚያደርጋቸው አካል ይሄ ነው ብሎ ለመደምደም ቢከብድም ያሉትን የሕግ ማዕቀፎች እና አንዳንድ ተግባራትን ተመልክተን ግን ለእርግጠኝነት የቀረበ መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን፡፡

የኢትዮጵያን የኢንተርኔት አፈና ገና ከጅምሩ ጀምሮ ሲከታተሉ የነበሩ ዓለማቀፍ ተቋማት አፈናውን የሶስት ተቋማት ተግባር እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ አፈናውን የሚመራው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ሲሆን፣ በሃገሪቱ ብቸኛው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር ደግሞ የአፈናው ተባባሪዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ ተቋማት ጉዳዩ ዋነኛ ተጠያቂ ተጠሪነቱን በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረገው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

ኢትዮጵያ ድረ ገፆችን ማፈን ከጀመረችበት ግንቦት 1998 ስድስት ወራት በኋላ በሕዳር 1999 የተቋቋመው ኢመደኤ በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የኢንተርኔት የመረጃ ፍሰት የመቆጣጠር ስልጣን ተሰጥቶትና ተጠሪነቱን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማድረግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 130/1999 ተመስርቷል፡፡ ኢመደኤ በተመሰረተበት ደንብ መሰረት ዓላማው ‹ … ሀገሪቱ የኢንፎርሜሽንና የኢንፎርሜሽን መረብ ቴክኖሎጅንና ቴሌኮሙኒኬሽንን ለብሄራዊ ደህንነቷ ስጋት ሳያስከትል የሰላም የዴሞክራሲና የልማት መርሃ ግብሮቿን ተግባራዊ ለማድረግ እንድትጠቀምበት ማስቻል … ›  እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፤ በዚህ ዓላማ ከለላ ስር ሆኖም ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የተቃውሞ ድምፀት ያላቸውን ድረ ገፆች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ 

ኢመደኤ የአረቡ ዓለም አብዮት በተፋፋመበት ወቅት በነሃሴ 2003 በድጋሚ በደንብ ቁጥር 250/2003 በመመስረቻ ደንቡ አለው ከተባለው ዓላማ በተጨማሪ ‹በሀገሪቱ ጥቅሞች ላይ የሚሰነዘሩ የኢንፎርሜሽን ጥቃቶችን መከላከልና አፀፋዊ ምላሽ መስጠት› የሚል አላማ ደርቦ በድጋሚ ተመስርቷል፡፡ በዚህ ወቅት ኢመደኤ ከአረቡ ዓለም አብዮት ጋር በተያያዘ ዘገባ የሚሰሩ ዓለማቀፍ የዜና ተቋማትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድረ ገፆችንና ጦማሮችን እንዲሁም የማህበራዊ ድረ ገፅ አድራሻዎችን በፀና ሁኔታ (aggressively) በኢትዮጵያ እንዳይታዩ እገዳ ማድረግ ችሏል፡፡ ይሄም ጊዜ መንግስት የኢንተርኔት ምህዳሩንየስልጣን ስጋቱ እንደሆነ የፈረጀበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢመደኤን በድጋሚ የመሰረተው ደንብም ኤጀንሲው ተግባሩን ሲፈፅም ማንኛውም አካል የመተባበር ግዴታ እንዳለበት ማስፈራሪያ አዘል አንቀፅን ጨምሮ የመጣ ሲሆን፤ የኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስትርም የአፈናው ተሳታፊነት ከዚህ የደንቡ ክፍል የመነጨ ይመስላል፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ በአዋጅ ቁጥር 808/2006 በታህሳስ 2006 የተመሰረተው ኢመደኤ ስልጣኑን እጅግ አስፋፍቶ መጥቷል፡፡

ለሶስተኛ ጊዜ የተመሰረተው ኢመደኤ ለየት የሚያደርገው ድረ ገፆችን ከማፈን ባለፈ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን የጥቃት ኢላማ አድርጎ አስፈሪ አካሔድ መጀመሩ ነው፡፡ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (Reporters Without Borders) በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር 2013 ባወጣው ‹የኢንተርኔት ጠላቶች› (Enemies of the Internet) ሪፖርት፤ ዓለም ላይ ለኢንተርኔት ቀንደኛ ጠላቶች ናቸው በማለት ከጠቀሳቸው አምስት ድርጅቶች ማለትም የእንግሊዙ Gamma Group፣ የጀርመኑ Trovicor፣ የጣሊያኑ Hacking Team፣ የፈረንሳዩ Amesys  እና የአሜሪካው Blue Coat System መካከል የመጀመሪያዎቹ ሶስቱ (Gamma GroupTrovicor እና Hacking Team) ለኢመደኤ የተለያዩ የስለላ (surveillance) መሳሪያዎችን በማቅረብ ለአፈናው ዋነኛ ተባባሪዎች እንደሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ተመልክቶ ነበር፡፡ ኢመደኤ በአሁኑ ወቅት ድረ ገፆችን ከመዝጋት ባለፈ እጁን አስረዝሞ የግለሰቦችን መረጃ መሰብሰብ የሚያስችል አቅም ለመገንባት እጅግ ውድ የሆኑ መሳሪያዎችን እየሰበሰበ ይገኛል፡፡

ከዳታ ክልከላ ወደ ድምፅ እቀባ

የህንድ ትልቅ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ (Internet Service Provider) የሆነው ኤርቴል (Airtel) በታሕሳስ 2006 ደንበኞቹ እንደ Skype, WhatsApp, Viber, imo ወዘተ አገልግሎቶችን ኢንተርኔት ተጠቅመው ለሚያገኙት ማንኛውም የድምፅ አገልግሎት (Voice over Internet Protocol - VoIP) ተጨማሪ ክፍያ ማስከፈል በወራት ውስጥ እንደሚጀምር ገልፆ ነበር፡፡ ከመግለጫው በኋላ ግን የወርልደ ዋይድ ዌብ (World Wide Web) ፈጣሪ የሆነውን ቲም በርነርስ ሊን ጨምሮ ከመላው ዓለም ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ የተቃውሞው ዋነኛ መነሻም ‹የዚህ አይነት ተግባር የመረብ ገለልተኝነት መርህን (The Principle of Net Neutrality) የሚጥስ ነው› የሚል ነበር፡፡ የመረብ ገለልተኝነት (Net Neutrality) በተለያዩ ፀሃፍት የተለያየ ትርጉም የሚሰጠው ሲሆን ሁሉም የሚስማሙበት ግን ‹የኢንተርኔት አቅራቢዎች ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን አይነት አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ፣ እቀባም ሆነ ለይተው ተጨማሪ ክፍያ ሊጠይቁ አይገባም፤ ገለልተኛ መሆን አለባቸው› የሚለውን ሃሳብ ነው፡፡ የህንድን የቴሌኮም አገልግሎት የሚያስተዳድረው ‘Telecom Regulatory Authority of India (TRAI)’፤ ይሄን የኤርቴል መግለጫ ተከትሎ ሕንዳዊያን በሃሳቡ ላይ እንዲወያዩ የውይይት ሰነዶችን ከበተነ በኋላ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የተቃውሞ ኢሜሎችና የተለያዩ ዘመቻዎችን ተገንዝቦ ከሁለት ወራት በፊት ጥር 30፣2008 የመጨረሻ ሃሳቡን ‹ማንኛውም የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጭ ተቋም የመረጃ መረብ ገለልተኝነትን (Net Neutrality) በሚጋፋ መንገድ እቀባም ሊያደርግ አይችልም፤ ተጨማሪ ክፍያም መጠየቅ አይገባውም› በማለት ብዙሃኑን የሕንድ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የሚያስፈነድቅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ኢንተርኔት ካመጣቸው ፀጋዎች አንዱ የስልክ አገልግሎትን በርካሽ መልክ እንድንጠቀም ማድረጉ ነው፡፡ ይሄም መደበኛውን ለኢንተርኔት አገልግሎት የሚከፈል በአንፃሩ አነስተኛ ዋጋ በመክፈል የስልክና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን ለማግኝት ያስችላል፡፡ አግልግሎቱ በተለምዶ ‹ኦቨር ዘ ቶፕ› (Over-the-top - OTT) አገልግሎት እየተባለ የሚጠራ ሲሆን ዓላማውም የቆዩትን የመደበኛ ስልክ አሰራሮች የበለጠ ማቅለልና በርካሽ ዋጋ ማቅረብ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተመሳሳይ በ2004 የመጨረሻ ወራት የኢትዮጵያን ማህበራዊ ድረ ገፆችን አጣቦ የነበረው “ኢትዮጵያ አፋኝ የሆነ የቴሌኮም አዋጅ ልታፀድቅ ነው” እና ‹አዋጁ ፀድቆ ሊተገበር ነው› የሚሉ ለኢንተርኔትተጠቃሚዎች አስደንጋጭ የሆነ ወሬዎች ነበሩ። (በጊዜው በጉዳዩ ላይ የዞን ዘጠኝ ጦማር ይሄን ፅሁፍ ፅፎ ነበር) በወቅቱ ቢቢሲንና አልጀዚራን ጨምሮ ዓለማቀፍ የሚድያ አውታሮች ‹‹ኢትዮጵያ ስካይፒን የመሳሰሉ በኢንተርኔት የድምፅ አገልግሎት (Voice over Internet Protocol- VoIP) የሚጠቀሙ ሰዎችን፤ እንዲሁም በቴሌኮሙ ያልታወቀ ግንኙነት መሳሪያ የያዙ ግለሰቦችን ለረጅም ዓመታት እስርና ለገንዘብ መቀጫ የሚዳርግ አዲስ አዋጅ አረቀቀች” የሚሉ ሰፋፊ ዜናዎችን ሲያስነብቡ፤ ሀሳብን በነፃነት መብት ላይ የሚሰሩ እንደ የጋዜጠኞች ጠባቂ ድርጅት (Committee to Protect Journalists)፣ አርቲክል 19 (Article 19) እና ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (Reporters Without Borders) የመሳሰሉ ዓለማቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በበኩላቸው ‹የኢትዮጵያ መንግስት ሀሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትና ጋዜጠኞችን ለማፈን ሆን ተብሎ የወጣ አዋጅ ነው› ሲሉ ኮንነውት ነበር፡፡ በወቅቱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር የሕዝብ ግንኙነት ሐላፊ የነበሩት አቶ ሽመልስ ከማል ‹አዋጁ የስካይፒን የድምፅ ግንኙነት አያግድም፤ ይልቅም ይህ አዋጅ በ1994 የወጣውን የስካይፕ ተጠቃሚነትን የሚከለክል ህግ እንዲሻር አድርጓል› ብለው ነበር።

አወዛጋቢው አዋጅም ከረቂቁ ምንም መሻሻል ሳይደረግበት በተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ከነሃሴ 2004 ጀምሮ አዋጅ ቁጥር 721/2004 በመሆን በተግባር ላይ ውሏል፡፡ በአዋጁን አንቀፅ 10 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ ‹‹ኢንተርኔትን በመጠቀም የስልክ ጥሪ አገልግሎት የሚሰጥ ማንኛውም ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከ 3 እስከ 8 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ሊያገኝ ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ገቢ አምስት እጥፍ የሚሆን መቀጮ ይቀጣል› ተብሎ መደንገጉም የብዙዎቹ ስጋት እውነትነት ያዘለ እንደነበር አመላክቶ ነበር፡፡

ይህ ከሆነ ከሶስት ዓመታት በኋላ በቅርቡ የኢትዮ ቴሌኮም የሥራ ሃላፊዎች በአገሪቱ ብቸኛ የሆነውና በመንግስት ደረጃ ‹እንደማትነጥፍ ላም› የሚቆጠረው የቴሌኮም ድርጅት የድምፅ ግንኙነት አገልግሎት የሚሰጡ (VoIP) ወይም የሚጠቀሙ ደንበኞቹን ተጨማሪ ገንዘብ ለማስከፈል የሚያስችል ቴክኖሎጂ በስራ ላይ ሊያውል እንደሆነ እየገለፁ ይገኛል፡፡ በተለምዶ ይሄን የድምፅ አገልግሎት የሚጠቀሙ እንደ Skype፣ WhatsApp፣ Viber፣ imo ወዘተ ያሉ የኮምፒውተር ወይም የስልክ መተግበሪያዎች (Applications) ለመጠቀም የዳታ ወይም የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያስፈልግ ሲሆን፤ ደንበኞች ይህን አገልግሎት ለማግኘት ለቴሌኮም ድርጅቱ ይከፍላሉ። ኢትዮ ቴሌኮም አሁን አገልግሎት ላይ ላውለው ተዘጋጅቻለው የሚለው ቴክኖሎጂ ደንበኞች ለኢንተርኔት ከሚከፍሉት በተጨማሪ የድምፅ አገልግሎት ለሚሰጡ መተግበሪያዎች በመጠቀማቸው (over the top) ብቻ ሌላ ተጨማሪ ክፍያ እንዲፈጽሙ ይገደዳሉ ማለት ነው።

ይሄን አስመልክተው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አንዷለም አድማሴ ለካፒታል ጋዜጣ  ሲገልፁ ድርጅቱ እነዚህን አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ የመዝጋት ዕቅድ እንደሌለው፤ ነገር ግን እነዚህን አገልግሎት የሚጠቀሙ ደንበኞችን ‘Policy Charge and Control system (PPC)’ በተባለ አዲስ ቴክኖሎጂ አማካኝነት እንቆጣጠራለን ብለዋል። የኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ አብዱረሒም አሕመድ በበኩላቸው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሰኞ መጋቢት 26/2008 እንደተናገሩት ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ከአጠቃላይ ገቢው ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን ገቢውን የሚያገኝው ከመደበኛ የስልክ አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹ከኢንተርኔት አገልግሎት የሚገኝው ገቢ ግን ሃያ በመቶው ብቻ ነው› ብለዋል፡፡ ‹በመሆኑም ይሄን ገቢ ለማሳደግ አዲስ አይነት የአገልግሎት አሰጣጥ እንጀምራለን› በማለት የዋና ሃላፊውን ሃሳብ አጠናክረዋል፡፡

(በጉዳዩ ላይ ኢትዮ ቴሌኮም ዘግየት ብሎ ‹ሐላፊው ይሄን አልተናገሩም፤ የተጠቀሱት አገልግሎቶችም ክፍያ ሊጠየቅባቸው አልታሰበም› በማለት ጉዳዩን ይዞት የወጣው ጋዜጣ (ካፒታል ጋዜጣ) እርማት እንደሚያደርግ  ቢገልፅም፤ የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊዎች በስልክ ለማረጋገጥ እንደቻልነው እስከ አሁን ድረስ (እስከ ዛሬ ጠዋት መጋቢት 28/2008) ከኢትዮ ቴሌኮም ለካፒታል ጋዜጣ የደረሰ ምንም አይነት የእርማት ጥያቄ እንደሌለና፤ ጋዜጣውም የሐላፊውን ንግግር የድምፅ ቅጅ እንዳለው ጠቅሶ የሚታረም ነገር እንደሌለ ለማወቅ ችለናል)

ይሄም ጉዳይ አገልግሎቶቹን ሙሉ ለሙሉ ከማገድ ይልቅ በተዘዋዋሪ ታሪፍን በመጨመር የዜጎችን ከአግልግሎቶቹ ተጠቃሚነት ማስቆምን ዓላማ ያደረገ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ከላይ ያነሳነውን የመረብ ገለልተኝነት (Net Neutrality) መርህንም አፈር ድሜ የሚያበላ ተግባር ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ አንድ ሲም ካርድ ለአንድ የተንቀሳቃሽ ስልክ ብቻ እንዲሰራ የሚያደርግ ኢክዊፕመንት አይደንቲቲ ሪጂስተር (Equipment Identity Register - EIR) የተባለ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ላይ ለማዋል እየሰራ መሆኑን ሐላፊዎቹ ገልፀዋል። ይህ ቴክኖሎጂ በእያንዳንዱ የስልክ ቀፎ ላይ የሚገኘውን የመለያ ቁጥር እየመዘገበ አንድ ሲም ካርድ ለአንድ ቀፎ ብቻ እንዲሰራ የሚያደርግ ነው፡፡ ቴክኖሎጅው የትኛው ግለሰብ የትኛው የሞባይል ቀፎን እንደሚጠቀም የሚየሳውቅ ነው ማለት ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ለዚህ ቁርጠኝነቱም ‹አሁን ገበያ ያሉ ያልተመዘገቡ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ሰብስቤ የራሴን አዳዲስ ስልኮች ለተጠቃሚዎች አድላለሁ› እስከማለት ደርሷል፡፡ ነገር ግን መንግስት የሚታማበትን ዜጎችን የመሰለል ተግባር ያቀላጥፍለታል የሚለው ደግሞ አዲስ ስጋት ነው፡፡ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ‹ይህን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ የምናደርገው ሳይቀረጡ የገቡ ስልኮችን አገልግሎት እያንዳይሰጡና የሞባይል ስልክ ስርቆትን ለመቀነስ ነው› ቢሉም፤ ካለፈው ልምድ ተነስተን ‹የቁጥጥር አባዜ ያለበት በኢትዮጵያ ያለው መንግስት ዜጎቹን መሰለያ አዲስ መረብ እየዘረጋ ነው› ብንል ስህተት አይሆንም፡፡

እንግዲህ ‹የጀመርናቸውን ትላልቅ ፕሮጀክቶች የምንደጉምበት ስለሆነ ለግል ተቋማት ክፍት አናደርገውም› ተብሎ በመንግስት በኩል የሚሞካሸው ኢትዮ ቴሌኮም፤ ብቸኛ በመሆኑ የሚያስተዳድረው አካልም (Regulatory Organ) ሆነ ‹ተው› የሚለው የበላይ የሌለበትና ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር እንደፈለገ የሚሰራ ተቋም ነው ማለት ነው፡፡

መጭው ዘመን

የቴክኖሎጂው ተደራሽነት እየጨመረና እየረከሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያዊያንም የኢንተርኔት ተጠቃሚነት ቀስ በቀስ እያደገ ነው፡፡ ምንም እንኳ የተጠቃሚው ቁጥር ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነፃፀር አሁንም እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም ያለው የኢንተርኔት ተጠቃሚነት ሁሉንም ተቃውሞ በወንጀልነት ለሚፈርጅ መንግስት የሚያስደነግጥ መሆኑ አልቀረም፡፡ ለዛም ነው የድረ ገፅ አፈናው በአስር ዓመቱ እጅግ ገዝፎና አስፈሪ ሁኖ የሚታየው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ከአራት ወራት ለሚልቅ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ሕዝባዊ ተቃውሞ በይነ መረቡ (በተለይም ማሕበራዊ ሚዲያዎች) ትኩስ መረጃን በርካሽ ዋጋ ተጠቅሞ የሕዝብ ጥያቄን ዓለም ላይ እንዴት ማድረስ እንደሚቻል ያስገነዘበ ሂደት ነው፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛው ተቃውሞዎች የተዘገቡት በማሕበራዊ ሚዲያዎች ቢሆኑም መንግስት ግን በኢትዮጵያ እንዲታዩ ትቷቸው የነበሩትን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚፅፉ ድረ ገፆችን (በተለይም የኦሮሚያውን ተቃውሞ ላይ ትኩረት አድርገው ሲዘገቡ የነበሩ ድረ ገፆችን) በድጋሚ እንዳይታዩ ማድረግ ጀምሯል፡፡ ዝነኛ የሆኑ የማሕበራዊ ድረ ገፆችን በተለመደው መልኩ መጠቀም እንዳይቻል ከአንድ ወር ለሚልቅ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል የተደረገው እቀባ ግን የአፈናውን ሌላ ጎን ይነግረናል፡፡ መንግስት አሁን ትኩረቱን ወደ ማህበራዊ ሚዲያዎች ማድረጉን፡፡


አሁን አፈናው እጅግ ብዙ ዘርፎችን ይዟል፡፡ በአንድ በኩል የተለመደውና የተቃውሞ ድምፀት ያላቸውን ድረ ገፆችንና ጦማሮች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ማድረጉ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የማሕበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎችን በመዝጋት እና አሁን ደግሞ የድምፅ አገልግሎት የሚሰጡ መተግበሪያዎችን የሚጠቀሙ ግለሰቦች ከሌሎች አገልግሎቶች በተለየ (discriminatory) ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ ለማድረግ አዲስ አሰራር በመዘርጋት ላይ መሆኑን በመግለፅ የመረጃ ፍሰቱን ማስተጓጎል ተጀምሯል፡፡ ከዚህ ዜጎች መረጃ እንዳያገኙ ከሚደረገው የመከላከያ (defensive) የአፈና ስልት ባለፈ ደግሞ፤ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ምስጢራት ለመበርበር የሚያስችሉ መሳሪያዎችን እና ዘዴዎችን ከውጭ ድርጅቶች በውድ ዋጋ በመሸመት የማጥቃት (offensive) ስልት በመጠቀም የአፈናውን ስልት ከፍ ብሏል፡፡ ይህን የአፈና ስልት ለማለፍ እንደ ኢንክሪፕሽን ያሉ የተለያዩ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ግለሰቦችን ደግሞ ወደ እስር በመወርወር የኢንተርኔቱን ምሕዳር ጠቅልሎ የመያዝ ስልት አስፋፍቶ እናገኛለን፡፡ አሁን ዓለምን የበለጠ እያገናኝ እና ክፍት እያደረገ ያለው ኢንተርኔትም በኢትዮጵያና መሰል ሀገራት ታላቅ ፈተና ገጥሞታል፡፡ ከዚህም ተነስተን ዜጎችን መጠበቅ ሲገባው በሚያጠቃው መንግስት ምክንያት መጭው ጊዜ ለኢትዮጵያዊያን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ፈታኝ መሆኑን መገንዘብ ብዙ የሚቸግር ጉዳይ አይደለም፡፡ 

***
የፅሁፉን የራስጌ ምስል ያገኝነው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (Reporters Without Borders) ካወጣው የ2014 ‹የኢንተርኔት ጠላቶች› ሪፖርት ነው::


No comments:

Post a Comment