Monday, September 19, 2016

ማኅበራዊ ሚዲያው እና የመንግሥት ስጋትበተስፋዬ ዓለማየሁ

የማኅበራዊ ሚዲያውን አጠቃቀም በተመለከተ ተከታታይ ዘመቻዎች እና ማጥላላቶች በተለያዩ ግዜያት በሕትመት ሚዲያው ሳነብ፣ በብሮድከስት ሚዲያውም ሳደምጥ ቆያቻለሁ፡፡ እነዚህን የአጠቃቀም ጉድለቶች ላይ ያተኮሩ ዘመቻዎች ታዲያ እንደ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስመለከታተቸው ነው የሰነበትኩት፡፡ ምክንያቱም መሰል ፈራጅ ዘጋቢ ፊልሞች በሕትመት ሚዲው ላይ ይሠሩ እና ጠንከር ያለው እርምጃ ይከተል ስለነበር ነው፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በመጀመሪ የኮረኮረኝ ጽሑፍ "ከማኅበራዊ ሚዲያው በስተጀርባ" በሚል ርዕስ በሪፖርተር ገዜጣ ላይ ከወጣ በጣም ቆየት ብሏል፡፡  የጽሑፉ ዋና ዓላማ የነበረው ከማኅበራዊ ሚዲያ ጠቀሜታ ‹በስተጀርባ ያለውን አደጋ ነው ማመመልከት› ነበር፡፡ የጽሑፉ አዘጋጅም በሚገባ አስረጅ ምሳሌዎችን አስቀምጠው ጠቀሜታውንም ለመዳሰስ ሞክረው ጽሑፋቸውን ቢያበቁም፣ ከዚያ በኋላ በተከታታይ እንዲሁ በተለያዩ ግዜያት ቅኝታቸው ማኅበራዊ ሚዲያው ከጥቅሙ ባሻገር ጉዳቶቹ ላይ ያተኮሩ ጽሑፎችን አንብቤያለሁ፡፡ እርግጥ ነው በተነሱት ሐሳቦች ዙሪያ የማኅበራዊ ሚዲያው፣ በዋነኛነትም ፌስቡክ ከጥቅሙ በዘለለ ባሉት አሉታዊ ተፅዕኖዎች ላይ መሠረታዊ ልዩነት ከጸሐፊዎቹ ጋር የለኝም፡፡ "የጥላቻ ንግግሮችን ማስተላለፊያ ነው""አሉባልታ ማሰራጫ ነው""የሠራ ግዜን ይሻማል"፣ "በቅርባችን ካሉ ወዳጅ ጓደኞቻቸችን ጋር ይለያየናል"፡፡ ሌሎችም የፌስቡክ እንከኖችን እያስታወስን መዘርዘር አንችላለለን፡፡
  
ማኅበራዊ ሚዲያው ግን በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ልንዘነጋው አይገባም፡፡ የማኅበራዊ ሚዲውን ችግሮች ማሳየቱ ለተጠቃሚው አጠቃቀሙን እንዲፈትሽ ስለሚያደርጉ መልካም ሊባል ቢሆንም፡፡ ችግሮቹን ማጉላቱ ላይ ግን አልስማማም፡፡ ከሚጠቀሱት ችግሮች ውስጥ ለራሳችን በጣም ተስማሚ የሆኑ ችግሮች አይጠፉምና በአግራሞት ወይም በድንጋጤ "ይህማ የእኔም ችግር ነው" የምንለው እና ለችግሩም ተጋላጭ እንደሆንን፣ በደንብ እንዲሰማን የሚያደርጉን ማሳያዎች ስለሚዘረዘሩ ሊያሸማቅቁን ይችላለሉ፡፡ ይህንን ስሜት ከመፍጠር ተሻግረው ግን በሕትመት ሆነ በብሮድካስት ሚዲያ የሚተላለፉት መልዕክቶች ውጤታቸው  (ኢፌክታቸው) ምን ያህል እንደሆነ ትዝብቱን ለየግላች ልተወውና፣ ማኅበራዊ ሚዲያው ንበማስተዋል መጠቀም የሚለው ምክር ላይም እንስማማና፣ ፌስቡክ በአሁኑ ሰዐት ሁነኛ አማራጭ ሚዲያ እንደሆነ ለማሳየት የሚከተለውን እጽፋለሁ፡፡

መነሻ፤ በአገራችን የሕትመት እና የብሮድካስት ሚዲያ ሁኔታ ወፍ በረር ቅኝት

በአገራችን ውስጥ ያለት የብሮድካስት እና ሕትመት ሚዲያዎች ከሚጠበቅባቸው አንፃር ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ በአግባበቡ እያገለገሉን አይደለም፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶችን ልንደረድር እንችላለለን፤ የጋዜጠኞች ብቃት ማነስ፣ የጋዜጠኞች የሥነ ምግባር ጉድለት፣ የጋዜጠኞች እና የሚዲያ ባለቤቶች የፖለቲካ ፍላጎት እና አመለካከከት፣ የገበያው ትርፋማነት እያልን በርካታ ምክንያቶችን ብንደረድርም "የእናቴ መቀነት…" ከመሆን አይዘልም፡፡  ምክንያቱም በእነዚህ ሰበቦች ወይም ችግሮች ውስጥ እንኳን የጋዜጠኝነት መርሖዎችን ለማክበር ከመሞከር ይልቅ ሲጥሷቸው በግልጽ ይስተዋላሉ እና ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ጠንከር ባሉ ሁሉን ዐቀፍ ተሳትፎ እና ውይይት በሚፈልጉ አገራዊ፣  ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም በዕኩል ደረጃ አያሳትፉም አያገልግሉም፡፡ አብዛኛዎቹ የአገራች ሚዲያዎች በጣም የተካኑባቸው እና የሚሽቀዳደሙባቸው ዘገባዎች በጣም ለስለስ ያሉ ማኅበራዊ፣ የመዝናኛ እና የስፖርት፣ የኪነ ጥበብ፣ የፊልም እና የፋሽን ጉዳዮች ናቸው፡፡

ጋዜጠኞች ማንም ደሞዝ ቢከፍላቸው፣ አገልጋይነታቸው ለዜጎች፣ ጥብቅናቸውም ለእውነት መሆን ሲገባው፣ በእኛ አገር ዐውድ ግን አብዛኞቹ ጋዜጠኞቻችን ሥራቸው ኅልውናቸው ስለሆነ የዜጎች አገልጋይነታቸው እና የእውነት ፍለጋቸውን ዘንግተውታል፡፡ በአንድ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ሠራተኛ ይለቅበት (turn out) የነበረው የሚዲያ ተቋም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን በጣም ሳቢ የሆነ የደሞዝ ማሻሻያ እና ጥቅማ ጥቅሞችን በማድረግ ሠራተኞቹን ከማቆየቱም በላይ ሌሎችንም ለመሳብ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ የበጀት ምንጩ ምንም እንኳን ከማስታወቂ የሚገኘው ገቢ ቢሆንም ከዜጎች ግብር የሚሰበሰበው ገንዘብም ቀላል አይደለም፡፡ የጋዜጠኞቻችን ትኩረት ግን የቀጣሪያቸው ትኩረት እና ፍላጎት መሳብ ብቻ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ ልማት እና ዕድገት ብቻ፡፡ በልማቱ ምክንያት እና ለልማት ሲባል ዜጎች ከአንድ አካባቢ ሲፈናቀሉ ወይም በልማታዊ ቋንቋ ለልማት ሲነሱ፣ የት ይድረሱ? ተመጣጣኝ የካሣ ክፍያ ያግኙ አገኙ? ቀጣይ ኑሮአቸውስ እንዴት ነው የሚሆነው? የሚለው ጉዳይ ከሚሰጠው ትኩረት ይልቅ ሰዎቹ ተነስተው ስለሚተከለው ግንባታ የሚወራው ይበዛል፡፡

የዚህ ዓይነቱ ጋዜጠኝነት ትኩረቱ ሰው ሕያው ፍጡር ሳይሆን ሕይወት አልባ ግዑዙ ነገር ነው፡፡ ቶማስ ሙር የተባለ እንግሊዛዊ  ባለ ቅኔ በኢንድስትሪ አብዮት ወቅት ለሱፍ ልብስ የሚሆን የበጎች ፀጉር በብዛት ለማምረት ሲባል ጭሰኞች ከቦታቸው እየተፈናቀሉ በጎች ሲረቡ ሲመለከት "በጎች ሰዎችን በሏቸው" እንዳለው የልማታችንን ትክክለኛ ገጽታ ለመተቸት አልቻልንም፡፡ እንዳንተችም ተደርገናል፡፡ ሚዲያዎቻችንም ነፃ መድረክ በመሆን እንድንወቃቀስ እና እንድንተራረም ክፍት ስላልሆኑ ሌላ መንገድ፤ ሌላ መድረክ አስፈልጎናል፡፡ በዋነኛነት ማኅበራዊ ሚዲያ ግንኙነታችንን የምናጠናክርበት የቴክኖሎጂው ውጤት ቢሆንም ቅሉ ማኅበራዊ ግንኙነትን ከማገዝ ቢሆንም ባሻገር ግን ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን "ችግር በቅቤ ያስበላል" እንደሚባለው፣ የሁነኛ ሚዲያ እና የግልጽ እና የነጻ መድረክ መጥፋት የማኅበራዊ ሚዲያውን እንደ ሁነኛ ሚዲያ ለመረጃ ማግኛ ምንነችነት እና የመወያያ መድረክነት እንድንጠቀመው ተግደናል፡፡
 
ከምርጫ 97 በኋላ የጋዜጦች መዘጋት እና የጋዜጠኞችም መሰደድ በመረጃ ፍሰት እና የሕዝብ ውይይት ላይ ትልቅ ክፍተት ፈጥሯል፡፡ እንደ እኔ ዕይታ ታዲያ ፌስቡክም ይህን የሚዲያ ክፍተት ሊሞላ በሚፈለግበት ወቅት የተገኘ የቴክኖሎጂው ትሩፋት ነው፡፡ ምክንያቱም የወቅቱ የጋዜጣ አንባቢ እና የሕዝብ ውይይት ተሳታፊ፣ ታዳሚ፣ የለመደውን የሕትመት ሚዲያ ሲያጣ ወደ አዲሱ ሚዲያ ፈልሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ማኅበራዊ ሚዲያው ጠንክራ የውይይት መድረክ የሆነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው በባሕርይው የሁሉም ነው፡፡ ሁሉንም አካታች ነው፡፡ ሁሉንም አካታች ሲባል አዲሱ ሚዲያ፣ ማኅበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ ኢንተርኔት ማግኘት ለሚችል እና መሠረታዊ የኮምፒውተር ዕውቀት ላለው፣  እንዲሁም ሐሳቡን እና አመለካከከቱን ለሌሎች ማካፈል ለሚፈልግ በሙሉ ክፍት ነው፡፡ ሚዲያው በባሕርይው ለግለሰቦች አንፃራዊ ነጻነትን ስለሚሰጥም ተመራጭ ገበታ (ፕላት ፎርም) ሆኗል፡፡ በተጨማሪም የሞባይል ስልክ ቴክኖለጂ ዕድገት ዜጎችን ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም እንዲችሉ የሚታይ አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡   

የመረጃ ምንጭ እና ነጻ መድረክ፤ የማኅበራዊ ሚዲያ

ማኅበራዊ ሚዲያው መንግሥት በተለያየ መልኩ ቁጥጥር ቢያደረግበትም፣ በተለይም ዋነኛ ተጠቃሚዎቹን ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ጅምላ ማስፈራራት እና እስራት ድረስ ቢሔድም፣ በሚገባ ለተመለከተው፣ ማኅበራዊ ሚዲያው ከመወያያ መድረክነቱ ባሻገር ተመራጭ እና ዋነኛ አማራጭ ሚዲያ እየሆነ ነው፡፡ በዋነኛው የመንግሥት ሚዲያ የሚቀርቡ ትርክቶችን ሚዛን መጠበቂያ እና  የተገለሉ እና የታፈኑ ድምፆች የሚደመጡበት መድረክም ሆኗል፡፡ ከዓመታት በፊት አሁን ከሕትመት ውጭ የሆነቸው "አዲስ ጉዳይ" መጽሔት በአንድ እትሟ ማኅበራዊ ሚዲያው አማራጭ የመረጃ ምንጭ እና የሐሰብ መድረክ እንደሆነ የሚያትት ጽሑፍ አስነባባን ነበር፡፡ የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት ማኅበራዊ ሚዲያው የሆነበት ምክንያት በፈቃድ አሰጣጥም ይሁን በስርጭት ወቅት እንደ ዋነኛው ሚዲያ በቀጥታ እና በቀላለሉ መቆጣጠር ስለማይቻለው ነው፡፡

ማኅበራዊ ሚዲያው ከማጠልሸት፣ ከማንቋሸሽ እና ከማንኳሰስ ይልቅ በማኅበራዊ ሚዲያው የሚወጡ መረጃዎች በአግባቡ እያጣራ እና እያጠራ ሚዛን የሚያስጠብቅ ሁነኛ እና ታማኝ ሚዲያ ያስፈልግ ነበር፡፡ ሚዲያው ሥራውን በአግባቡ አለመሥራቱ ማኅበራዊ ሚዲያውን ከአማራጭ ሚዲያነት ይልቅ ወደ ዋነኛ የመረጃ ምንጭነት እንዲቀየር አድርጎታል፡፡ ስለሆነም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎችን በዋነኛው ሚዲያ ከማጣራት ይልቅ፣ በተቃራኒው  በፖለቲካ እና ጠንካር ባሉ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በዋነኛው ሚዲያ በኦፊሴል ለሚነገረው ማጣሪያ እና የጉዳዩን አንድምታ የመወያያ መድረክ እየሆነው ነው፡፡
  
የመንግስት ስጋት…

"የአረብ ፀደይ" ተብሎ የተሰየመው በአረብ አገራት የተደረገው ፖለቲካዊ እቅስቃሴ እና የመንግሥታት ለውጥ የማኅበራዊ ሚዲያው ሚናው ከፍ ያለ ስለነበር በአረብ አገራት  የደረሰው እንዳይደርስበት አስቀድሞ ለመከላከል ከሚወስዳቸው እርምጃዎች አንዱ ማኅበራዊ ሚዲያውን ማውገዝ እና ማስወገዝ ሆኗል፡፡ እርግጥ ነው እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር 2001 በፍሊፒንስ ማኒላ በአጭር የስልክ መልዕክት ከተጠራው እና የፕሬዘዳንት ጆሰፍ እስትራዳን መንግሽት ከለውጠው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ጀምሮ በርካታ የመንሥግት እና የስርዓት ለውጦች በተለያዩ አገራት ቴክኖሎጂውን በመታገዝ በማኅበራዊ ሚዲያው የማስተባበር ሥራ ተሠርቶበታል፡፡ ከዚህም በመነሳት ሲንካ ሳሲ የተባለች የዘርፉ ተመራማሪ ከሚደረጉት የፖለቲካ እና የባሕል ለውጦች ጀርባ ያለው ኃይል አዲሱ ሚዲያ እንደ ሆነ ጽፋለች፡፡ ይህም የመንግሥት ስጋት ይመስለኛል፤ አፍጥጦ የመጣ… ይህ ሚዲያ ውጤቱ አዝጋሚ ቢሆንም በስተመጨረሻ ግን ወደ ዲሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ማምራቱ አይቀሬ እንደሆነ ዊሊያም የተባለ የዘርፉ ምሁር ያብራራል፡፡ ይህም እንዴት ሊሆን እንደሚችል የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲው ዮቺያ ቤንክለር ሲግልጸው "የማኅበራዊ ሚዲያው ከታች ወደ ላይ አጀንዳ በመቅረፅ፣ መረጃ ለሁሉም ተደራሽ በማድረግ እና ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት በመላቀቅ ለማኅበረሰቡ ነጻ መድረክ በመሆኑ ነው" ይላል፡፡ ባሮውል የተባለ ምሁር ይህን ሲያጠናክረው ኮምፒውተሮቻችን ከመንግሥታት አገዛዝ ነጻ አውጥተውናል ይላል፡፡
 
ሌላኛው የመንግሥት ስጋት ደግሞ ብቻውን የመናገሩን እና ብቻውን የመሰማቱን ነገር እንደቀረበት እርግጥ ከመሆኑ የመነጨ ይመስለኛል፡፡ የመንግሥት ጩኸት ደግሞ የመረጃ ምንጫችሁ እኔ ነኝ፤ እኔን ብቻ ስሙኝ፤ እኔን ብቻ እመኑኝ፤ እኔን ተከተሉኝ ነው፡፡  ለዚህም ማሳያ በኢብኮ የሚተላለለፉ ዜናዎች በሙሉ ምንጫቸው በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤቶች ናቸው፡፡ እነዚሁ በተለያየ መዋቅር የሚገኙ የመንግሥት ጉዳዮች ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤቶች ዋነኛ ሥራቸው ለመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ቢሆንም ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን ለሚወጡ ዜናዎች ብቸኛ ምንጮች ሆነዋል፡፡ በእነዚሁ ቢሮዎችም ተሠርተው የሚላኩ ዜናዎችም በሚዲያው ሪፖርተ ማጣራት ሳይደረግበት እንደ ወረደ ይቀርባል፡፡ ከመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ የሚወጡ ዜናዎችን ደግሞ የምናያቸው ናቸው፤ ሁልግዜ ለውጥ እና ዘወትር ሕዳሴ፡፡ ያለመደመጥ እና ያለ መታመን ስጋት
ማኅበራዊ ሚዲያው የተመራጭ የሆነበት ምክንያት የምንፈልገውን አስተሳብ እና አመለካከት በየዓይነቱ ማግኘት መቻላችን ብቻ አይደለም፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ ገበታው (ፕላት ፎርሙ) ሁሉንም ዓይነት የሚዲያ ውጤቶች ሬዲዮኑንም፣ ቴሌቭዥኑንም ፣ጋዜጣውንም እንደልብ በአንድ መስኮት ማግኘነት አስችሎናል፡፡ በሬዲዮቻችን እና በቴሌቭዥናችን መከታተል ያልቻለናቸውን  የተቃውሞ ድምፆች፣ በኢንተርኔት የሬድዮ እና የቴሌቭዥን ስርጭቶችን በቀላሉ ማግኘነት የሚያስችለን የመረጃ ገበታ በመሆኑም ነው፡፡
         
በማኅበራዊ ሚዲያ ብዛት ያላቸው የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ስለሚነሱ፣ ሰዎችም የሚፈልጉትን ጉዳይ እንዲለዩ እና ከመሰሎቻቸው ጋርም  እንዲጋሩ፤ በተጨማሪም ማንን ጓደኛ ማድረግ እና ማንን መከታተል እንዳለባቸው እንዲመርጡ ዕድሉን ሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የማኅበራዊ የሚዲያው ተጠቃሚዎች ሰፊ አማራጭ አላቸው፡፡ ከደጋፊ እስከ ነቃፊ፤ ከተቆርቋሪ እስከ ነቋሪ ድረስ ከሁሉም ወገን በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ እንደልብ ይገኛሉ፡፡ የተቃውሞው ጎራ በማኅበራዊ ሚዲያው ብቸኛው መድረኩ ስለሆነ ጎልቶ ይደመጣል እንጂ፣ የመንግሥት ደጋፊዎችም በተሻለ ቁሳቁስ እና ማበረታቻ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ እንቅስቃሴያቸው በጣም የጎላ ነው፡፡  በአንድ ወቅት ከመንግሥት ወገን ከሆነ ወዳጄ ጋር ስናወጋ ይህንኑ አዲስ ሚዲያ የሚቆጣጠር (የኦንላይን ሞኒተሪንግ) ክፍል በኢቲቪ ውስጥ እንዳለ እና ይኸው ክፍል  በሚያቀርበው ግምገማ መሠረት በማኅበራዊ ሚዲያም ይሁን በሌሎች ዌብሳይቶች ለተነሱ ጉዳዮች እንደ አስፈላጊነቱ  በዋነኛው የቴሌቭዥን ጣቢያ ምላሽ እንደሚሠሩ እና ይህንንም ለሚያደርጉበት የተሻለ አቅም ያለው ኮምፒዩተር እና የተሸለ የኢተርኔት መሥመር ያለ አንዳች ክልከላ እንዳላቸው አጫውቶኛል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ያለው ዘመቻ የቃላት ብቻ አይደለም፡፡ ከቃላት ጦርነቱ በዘለለ የተመረጡ ዌብሳይቶችን መዝጋት፣ ሰላይ ሶፍተዌሮችን በመጠቀም በተጠቃሚዎች ላይ ስለላ ማካሔድን ይጨምራል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁሉ ቁጥጥር እና ተፅዕኖ ውስጥ ባለው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማነንታቸው ባልታወቁ ሰዎች የሚለቀቁ መረጃዎች አጥፊ ናቸው፤ ከምን የመጣ ስጋት ነው? ካለማዳመጥ ስጋት ነው ወይስ ከለውጥ እንቅስቃሴው? ሌለው ደግሞ የዚህ አስረጅ በመሆን የቀረቡት ምሁራን እና ባለሙያዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ትንታኔ ትኩረት ግንጥል የሆነውስ ለምንድነው?

No comments:

Post a Comment